የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎቱን ወደ ኹለት ጤና ጣቢያዎች አዛወረ

0
1382

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሙሉ ለሙሉ የኮቪድ 19 ህክምና እንዲሰጥ በጤና ሚስቴር መወሰኑን ተከትሎ ከዚህ በፊት ይስጣቸው የነበሩ የህክምና አገልግሎቶችን ወደ እንጦጦ ፋና ጤና ጣቢያና ወደ ሽሮ ሜዳ ጤና ጣቢያ ማዛወሩን አስታወቀ።

በመሆኑም በሆስፒታሉ ይሰጡ የነበሩ የክትትል ህክምና አገልግሎቶች ከሚያዚያ 13 ቀን 2012 ጀምሮ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች በሆስፒታሉ ሐኪሞችና ከፍተኛ ባለሞያዎች የሚሰጡ መሆኑን አሳውቋል። በዚህ መሠረት በየጤና ጣቢያዎቹ የሚሰጡ የክትትል ህክምና መርሀግብር መሠረት ታካሚዎች ህክምናዎቹን ማግኘት እንደሚችሉ ሆስፒታሉ ያሳውቃል። ሆስፒታሉ ካደረገው የአገልግሎት መስጫ አድራሻ ለውጥ ጋር ተያይዞ ከቲቢ ታማሚዎች ውጭ አዳዲስ ታካሚዎችን እንደማይቀበል አስታውቋል።

ነገር ግን ሆሲፒታሉ ይሰጠው የነበረው የቲቪ ህክምና አገልግሎት በልዩ ሁኔታ በሆስፒታሉ በተለየ ቦታ እንደሚሰጥ የሆሰፒታሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሽናፊ አምብሬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኃላፊው አክለውም ሆስፒታሉ በየጤና ጣቢያዎቹ የሚሰጠው አገልግሎት እስካሁን በሆስፒታሉ ህክምና ጀምረው ያልጨረሱ ታካሚዎችን መከታተል መሆኑን ስረድተዋል።

ሆሰፒታሉ በጤና ጣቢዎቹ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በቀናቶች ፈረቃ ሲሆን፣ በዚህም በእንጦጦ ፋና ጤና ጣቢያ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች የቀዶ ጥገና ህክምና ሰኞና ረቡዕ ጠቅላላ ቀዶ ጥገና፣ ማክሰኞ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና፣ ሐሙስ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና አርብ የአጥንት ቀዶ ህክምና መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሌሎች የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች ሰኞ የሽንትና የኩላሊት ቀዶ ህክምና፣ ማክሰኞ ስነ አዕምሮ( ሳይካትሪ)፣ ረቡዕ ሜዲካል ሪፈር፣ ሀሙስ የቆዳ ህክምና እና አርብ የአይን ህክምና እንዲሁም የህጻናት ህከምና ማክሰኞና ረቡዕ እንደሚሰጡ አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።

በሽሮ ሜዳ ጤና ጣቢያ የሚሰጡ አገልግሎቶች በሆስፒታሉ ሲሰጥ የነበረው የ ኤ አር ቲ ህክምና አገልግሎት እና ክትትል በሁሉም የስራ ቀናት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ሆስፒታሉ ከዚህ ብኋላ አድስ ታካሚዎችን ተቀብሎ እንደማያስተናግድ እና ከዚህ ቀደም ወደ ሆስፒታሉ በሪፈር የሚላኩ ታካሚዎች ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒል መላካቸውን እንደሚቆሙም ተጠቁሟል።

እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጻ ሆስፒታሉ ይሰጣቸው የነበሩ የህክምና አገልግሎቶች ወደ ጤና ጣቢያዎች መዘዋወራቸው በታካሚዎችና በህክምና ሂደቱ ላይ የሚደርሰው ተጽኖ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል። ነገር ግን አሁን ላይ በተመረጡት ጤና ጣቢያዎች የሚሰጠው ህክምና በቂ ካልሆነ ሌሎች ሶስት ጤና ጣቢዎችን ለመጠቀም የተቀመጠ አቅጣጫ እንዳለም አክለው አመላክተዋል።

በሆስፒታሉ ሲሰጥ የነበረው ክትባትና የቅድመ ወሊድ ክትትል እንዲሁም የወሊድ አገልግሎት በአቅራቢያ በሚገኝ ጤና ጣቢያ በሚቀጥሉት ጊዜያት እንዲሰጥ ሆስፒታሉ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነና ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል።

የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የተለያየ የግልና የመንግስት ተቋማት ህንጻዎች የኮሮና ቫይረስ ለተገኘባቸው ሰዎች የሕክምና ማዕከል እንዲሆን፣ እየተዘጋጁ ሲሆን ለኮሮና ወረርኝ ለይቶ ማቆያ ከተዘጋጁ ቦታዎች ውስጥ የሚሊኒየም አዳራሽን ጨምሮ የግለና የመንግስት ህንታች በዝግጅት ላይ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ትምህርት አቁመው የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችም በየክልሎቹ መበዘጋጀት ላይ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here