የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን ወደ መጠለያ የማስገባት ሒደቱ እንደታሰበው እየተከናወነ አይደለም

0
1388

አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የክልል ከተሞች ላይ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን በኮቪድ 19 እንዳይጠቁ በሚል እና ወረርሽኙንም ለመግታት ሕጻናትን ከጎዳና ላይ በማንሳት ወደ መጠለያ የማስገባት ሂደቱ በተጀመረበት ፍጥነት እየሄደ እንደልሆነ ተገለፀ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት የጎዳና ተዳዳሪዎች 78 በመቶ የሚሆኑት የጎዳና ተዳዳሪዎች ሕጻናት ሲሆኑ እስካሁን ባለው ወደ መጠለያ የማስገባት ሂደት ግን ግማሽ ያህል በተለያዩ መክንያቶች አለመሰብሰቡ የኢፌዲሪ የሴቶች እና ህፃናት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ለአተገባበሩ እንደታሰበው አለመሔድ እንደ ችግር ያስቀመጠው በጎዳና ላይ የሚገኙት ሕጻናት ወደ መጠለያ ለመግባት ፍላጎት ስለሌላቸው እና በተለያዩ ስፍራዎች ስለሚደበቁ ነው ሲል አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪም ወደ መጠለያ ከገቡ በኋላ አምልጠው መውጣታቸው ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ከዛም በተጨማሪ ጎዳና ተዳዳሪ ህፃናቶችን ከማንሳት ባሻገርም በጎዳና ላይ ያሉ አዛውንቶችን እና ሴቶችን ማንሳት መጀመሩም ተገልፀዋል።

እንደ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ገለጻ ከሆነ አሁን ላይ የጎዳና ተዳዳሪ ታዳጊዎች ቤተሰብ እንዳላቸው በመታወቁ በአሁኑ ሰዓት የማጥናት ስራ እየተሰራ ወደ ቤተሰባቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እየተተገበረ ነው ሲልም ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አድነው አበራ ሲገልጹ አንድ ጥቅም ይኖረዋል ተብሎ የታሰበበት ምክንያት ወደ ማእከል በሚገቡበት ጊዜ የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ታዳጊዎቹ ከመግባታቸው ባሻገር የተቋሙ የአቅም ውስንነት መኖሩ ችግሩን ስለሚያባብሰው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተገቢ እርምጃ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታውቀዋል ።

የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመሰብሰቡ ስራ በዋነኛን እየሰራ የሚገኘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲሆን ኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ለመግታት ይህ ተግባር መታሰቡን ገልፀው ስራቸው ግን በተለያየ ምክንያት ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

ነገር ግን አድነው ይህን ይበሉ እንጂ ከተለያዩ አካላት ለሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ‹‹ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19›› ወረርሺኝ ወደ ኢትዮጲያ ከገባ በኋላ ጎዳና ላይ ለሚገኙ ታዳጊዎች (ዜጎች ) የሚውል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ›› አንስተዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዠ እንደሚታወቀው አዲስ ማለዳ በ 74 እትሟ እንደወጣው መረጃ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ 52 ሺሕ ለሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች በቋሚነት መጠለያ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ ማስታወቁን ፤ ሚኒስቴሩ ጨምሮ እንደገለጸው፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ እየተሠራ ቢሆንም፣ ከወረርሽኙ ባለፈ ግን በዘላቂነት በመጠለያ የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነ መግለፁ የሚታወስ ነው።

ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ እንደተናገሩት የጎዳና ተዳዳሪዎችን እጅ በማስታጠብ እና አልፎ አልፎ በመጎብኘት ዘላቂ ውጤት ማምጣት አይቻልም። ይልቁንም መፍትሄው ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ አማካኝ ምን ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ የሚለውን ከተለየ በኋላ ለእነርሱ የሚሆን መጠለያ ማዘጋጀት ቀዳሚ ነው ብለዋል።
ይህን ሥራ ለይተን ጨርሰናል የሚሉት ኃላፊው፣ ካሉት 52 ሺሕ የጎዳና ተዳዳሪዎች 12 ሺሕ የሚሆኑት አዋቂዎች ሲሆኑ የተቀሩት ታዳጊዎች መሆናቸው ታውቋል ብለዋል። በጎዳና ላይ የሚገኙትን ሰዎች ወደሚዘጋጅላቸው መጠለያ እንዲገቡ ማድረግ፤ የበሽታውን ስርጭት እንዲቀንስ የማድረጉን ሥራ እንደሚያጠናክርም መግለፃቸው ሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here