የሀበሻ አረቄ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ኮሮና ቫይረስን ይከላከላል በሚል የተሳሳተ አመለካካት ተጠቃሚ በመጨመሩ በከፍተኛ መጠን እየተሸጠ መሆኑ ታወቀ። ይህንም ተከትሎ ከወረርሽኙ በፊት አንድ ሊትር 120 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሊትር የ30 ብር ልዩነት በማሳየት 150 ብር ከፍ ማለቱንም ለማወቅ ተችሏል።
ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ በደብረ ብርሀን ከተማ የሚገኙ የአረቄ መሸጫ ቤት ባለቤቶች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የሀበሻ አረቄ ተጠቃሚ በመጨመሩ ምክንያ የዋጋ ጭማሪዉ መከሰቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነጋደዎቹ እንደገለጹት የሀበሻ አረቄ ተጠቃሚ የመጨመሩ ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ አረቄ ለኮረና ቫይረስ መከላከል ያገለግላል በሚል መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ህብረተሰቡ የጤና ሚኒስቴር ወይም የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚሰጣቸው መረጃዎች ውጭ በግለሰቦች የሚነገሩ የቫይረሱ መድሃኒት ናቸው በማለት የተለያዩ ነገሮች እንደሚሰራጩ ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡ አረቄን እንደ ኮሮና ቫይረስ መከላከያነት መጠቀሙ ትክክል እንዳልሆነና መሰረት የሌለው የሀሰት መረጃ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም እስካሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ለቫይረሱ እውቅና የተሰጠውና በአለም ጤና ድርጅትም ሆነ በሌሎች ተቋማት የተገኘና ትክክለኛ ክትባት ስለመገኘቱ የተረጋገጠ ነገር ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ከኮረና ቫይረስ ለማምለጥ ያለው ብቸኛ መድኃኒት በጤና ሚኒስትር የሚሰጡ መመሪያዎችን መተግበር እንደሆነ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ በአንድ የፌደራል መስሪያ ቤት የሚሰሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ የሀበሻ አረቄ ኮረናን ለመከላከል ይረዳል በሚለው መላ ምት የተስማሙ የስራ ባልደረቦቻቸው ጭምር የደብረ ብርሀን አረቄ በመባል የሚታወቅ አረቄ ከደብረብርሀን እያስመጡ እንደሚጠቀሙ ጠቁመውናል። የአዲስ ማለዳ ምንጭ አክለውም ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ደብረ ብርሀን ከተማ ባቀኑበት ለዚሁ አላማ እንዲያመጡላቸው እንደጠየቋቸው እና ከኹለት ጊዜ በላይ ደብረ ብርሀን ከተማ ተጉዘው ለስራ ባልደረቦቻቸው አንድ ሊትር አረቄ በ150 ገዝተው እንዳመጡላቸው እና አሁንም የሚጠይቋቸው እንዳሉ ጠቁመዋል።
የደብረ ብርሃን አረቄ ከዚህ በፊትም በአዲስ አበባና በተለያዩ ቦታዎች ተፈላጊ መሆኑን አስታውሶ በአሁኑ ወቅት ግን የተጠቃሚ መበራከት እና የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን የሰሜን ሽዋ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ጽሕፈት ቤቱ የአረቄ ዋጋ የጨመረበትን ዋጋ ከአልኮል መጠጦች ዋጋ ጭማሪ ጋር የተያያዘ የመጣ ነው ብሏል። ነገር ግን የአካባቢው የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደነገሩን የሀበሻ አረቄ ዋጋ ጭማሪ ከሌሎች በቅርቡ ከተሻሻለው የአልኮል መጠጦች ዋጋ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል።
ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ የጤና ባለሙያዎች ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች ትዕዛዝ ውጭ በራሱ መንገድ የተለያዩ ተለምዷዊ ነገሮችን እንደመድኃኒትነት መጠቀሙ ተገቢ እንዳልሆነና ሌላ ተጨማሪ የጎንዮሽ ችግር ሲለሚያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሰጣቸውን አቅጣጫዎች በመከተልና ስለ ኮረና ቫይረስ የሚተላላፉ መረጃዎችን ትክክለኛነትና የተገኙበትን ምንጭ ሳያረጋግጡ መቀበል በህብረተሰቡ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉ ህብረተሰቡ መረጃዎችን ከታማኝ ምንጮች ብቻ መውሰድ እንደሚስፈልግ የጤና ሚኒስቴር አሳስቧል።
ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012



