የአምራች ዘርፉን ለመደገፍ መንግስት 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

በኢትዮጵያ ውስጥ በአምራች ዘርፉ ላይ እየታየ ያለውን መዳከም እና ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ዕጥረት ለቅረፍ መንግሥት 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቁ ተገለጸ። ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተጋረጡበትን ችግር እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን መዳከም ለመቅረፍ መንግሥት ለአምራች ዘርፉ 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲያደርግ የኢፌዲሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል።

የኢፌዲሪ ንግድና ኢንስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር መላኩ አለበል ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት አምራቹ ዘርፍ እየተጋፈጠው ያለውን ችግር በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ እና አቅፎ የያዛቸውን ሰራተኞች ይዞ እንዲቀጥል በሚል ከመንግሥት ድጋፍ እንዲደረግለት ጥያቄ እንደቀረበለት ጠቁመዋል። ከዚህም ባለፈ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ዕቃዎች ውስጥ በአመዛኙ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ጥሬ ዕቃ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ለአምራች ዘርፉ ሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች በጥሩ ሁኔታ በአገር ውስጥ እየተመረቱ እንደሚገኙ የጠቀሱት መላኩ ነገር ግን የሚፈለገውን ጥራት ባለማስጠበቃችን ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ አገር ከውጪ ተመሳሳይ ግብዓቶችን እንደምታስገባ ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በድንጋይ ክሰል እና በብረት እንዲሁም መደበኛ ማዕድናት የሆኑትን በአገር ውስጥ በማምረት ረገድ ከፍ ያለ መሻሻል እየታየ እንደሚገኝ ገልጸው በውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና በአገር ውስጥ ባለሃብቶች ተነሳሽነት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት ከአምራች ዘርፉ ጋር ንግድ ሚኒስቴር በቅርበት በመስራት ከውጪ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በማምረት በከፍተኛ ሁኔታ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት እንዲቻል በትኩር እየተሰራበት እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ከአምራቾችም የተገኘው ምላሽ አበረታች እንደሆነና በተለይም ደግሞ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ከተሳለጠ በተለይም የብረት ማእድንን አፈሩን በማምጣት በአገር ውስጥ ግብዓቶችን ማምረት ምርጫቸው እንደሆነ ማስታወቃቸውን መላኩ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ከ18ሽሕ 8 መቶ ባለይ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት መላኩ የመስሪያ ቦታ፣ የግብዓት አቅቦት፣ የገንዘብ እና መሰል ልዩ ድጋፎች እንደሚያስፈልጋቸውም አስታውቀዋል። መላኩ አያይዘውም በተለይም ደግሞ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በአገር ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ላይ የሚገኙ እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ላይ ድጋፍ እንደሚደረግ ጨምረው ገልጸዋል። በዚህም ረገድ የዕጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር፣ የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ ለሕክምና ባለሙያዎች በስራ ላይ ሲሆኑ የሚያደርጓቸው አልባሳት እና የሚጫሟቸውን ጫማዎች የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች እንደሆኑ ተጠቅሷል።

የገቢ ምርት ከአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ደግሞ ከአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርት 6 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው የሚታወቅ ነው። በዚህም ረገድ ኮቪድ 19 ከዚህ በፊት በመንግስት እምብዛም ትኩረት ባልተሰጠባቸው ሴከተሮች እና ፖሊሲዎች ላይ ትልቅ እንደ መንግስት ዞር ብሎ እንዲያስተውል እና ወደ ውስጥ እንዲመለከት እንዳደረገው ለማወቅ ተችሏል። በዚሁ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽ ተከትሎም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት በተመለከተ መላኩ ሲገልጹ በነዳጅ ምርት ላይ የታየው ዋጋ ማሽቆልቆል ኢትዮጵያ እንደ መልካም አጋጣሚ እንደምትጠቀምበትና ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የነዳጅ ምርት መጠን በመጨመር የማከማቸት ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ በአገር ውስጥ የሚገኙ የነዳጅ ሻጭ ድርጅቶችም ክምችት መጠናቸውን እንዲጨምሩ መልዕክት መተላለፉን አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here