ለኮቪድ 19 የሚደረገውን ድጋፍ ወደ አንድ ቋት እንዲገባ የሚያደርግ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር ከግለሰቦች እና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የሚገኘውን ድጋፍ ወደ አንድ ቋት እንዲገባ የሚያደርግ መመሪያ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እተዘጋጀ እንደሆነ ታወቀ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት መመሪያ 63 የተባለው ይኸው መመሪያ ከተለያዩ አካላት የሚደረጉ ድጋፎችን በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ ወደ አንድ ቋት እና አካውንት ተመዝግበው እንዲገቡ የሚያደርግ እንደሆነም ተጠቅሷል።

አዲስ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው መመሪያ 63፤ ዘጠኝ መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ሲሆን በርካታ ጉዳዮችን እና ግልጽነት የጎደላቸውን የእርዳታ አሰባሰቦችን ይቀርፋል ተብሏል። ምንጮች እንደገለፁት ወረርሽኙን ለመግታት ባለሃብቶች በተለያዩ የመንግሥት አካላት ተደጋጋሚ ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው እና ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳረጉም ተጠቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ስፍራዎች ሰዎች እንዲሁም ባለሃበቶች ብሎም ለጋሽ ድርጅቶች ምንም አይነት ሕጋዊ ሰውነት በሌላቸው አካላት እርዳት እንደሚጠየቁ እና የተለገሰው እርዳታም ለሕዝብ ሳይደርስ እንደሚቀር መንግስት ስለደረሰበት ይህንም ለመቆጣጠር መመሪያው ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቅሷል። በአንዳንድ ስፍራዎች ዕርዳታ እናሰባስባለን የሚሉ ሰዎች እንደ አዲስ የንግድ አይነት በመጠቀም ገቢ እየሰበሰቡ እንደሚገኙም ተደርሶበታል ሲሉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ በታላላቅ ባለሃብቶች ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍ ያለ ሲሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚያለሙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ንግዳቸው እና መኖሪያቸው ባሉበት አካባቢ ኹሉ ዕርዳታ እንዲያደርጉ እንደሚጠየቁ እና አዲሱ መመሪያም ይህን እንደሚያስቀር ታውቋል። በአዲስ አበባ በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በክፍለ ከተማ ለአንድ አይነት ዓላማ ተደጋጋሚ የእርዳታ ጥያቄ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንደሚቀርብላቸው የታወቀ ሲሆን በክልሎችም አንድን ባለሃብት ከኹለትና ከዛ በላይ ክልሎች ላይ ዕርዳታ ሊጠየቅ እንደሚችልም ለማወቅ ተችሏል። ይህ ደግሞ ያለአግባብ ገንዘብ ከግለሰቦች በመውሰድ እና በአግባቡ ባለመጠቀም ለጋሾች ዘንድ የገንዘብ ችግር እንዲፈተር እና ትክክለኛው እና ዕርዳታው በሚያስፈልግበት ወቅት አስፈላጊ ዕርዳታን ለማግኘት ሊያስቸግር እንደሚችል ተጠቁሟል።
በመመሪያ 63 መሰረት የትኛውም አይነት ዕርዳታ ወደ መንግስት ቋት በመግባት ከዛም እንደ አስፈላጊነቱ እና በተጠና እንዲሁም በተመጣጠነ መንገድ ለክልሎች እንደሚከፋፈል ታውቋል። ይህም ማለት ክልሎች በተለያየ መንገድ ከለጋሾች የሰበሰቡትን ድጋፍ ወደ ማእከላዊ ቋት በመላክ በአንድ ስፍራ እንዲከማች ማድረግ እንጂ በራሳቸው አሰራር ለሕዝብ ማከፋፈል እንደማይችሉ በመመሪያው ላይ እንደሚካተት ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ከክልችም ባለፈ በውጭ አገራት የሚደረጉ መዋጮዎች እና ድጋፎች ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት በትክክለኛው መንገድ ተመዝግበው እና አስፈላጊው ቅደም ተከተሎች ተከናውነው ወደ ቋቱ እንደሚገቡ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለአንድ ለተወሰነ አካባቢ የሚደረገው ድጋፍም በመንግስት በኩል ማለፍ እንደሚኖርበት ከወዲሁ መመሪያው ላይ ተቀምጧል።

የጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሬታሪ ንጉሱ ጥላሁን በቅርቡ የኮቪድ 19 ተከትሎ ከአገር ውስጥ ለጋሽ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ በማዕከል ደረጃ የታወቀ ሲሆን ከዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ደግሞ 1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ይፋ አድርገዋል። በመግለጫው መንግሥት የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመግታት በዋናነት ሀብት ማሰባሰብን እንደ ግንባር ቀደም አማራጭ አድርጎ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ለመድረስ አስቦ እሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል። በዚህም በመግለቻው እንደተጠቀሰው መንግስት ከውጭ አገራት ወደ አገር ቤት ገብተው በለይቶ ማቆያዎች ከፍለው ለመቆየት የማይችሉ ስድስት ሽ የሚሆኑ ሰዎችን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዳኖራቸው ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here