የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለማችን ከተከሰተና ሥርጭቱን በአራቱም ማዕዘናት ካስፋፋ በኋላ ኢትዮጵያንም ዘግየት ብሎም ቢሆን ጎብኝቷታል። ወረርሽኙ በአገራችን የተፈራውን ያክል አስጊ ደረጃ ላይ ባይደርስም እስካሁን ከ11,669 በላይ ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ 117ቱ ቫይረሱ እንደያዛቸው፣ ሦስቱ ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ 87ቱ የሕክምና እርዳታ ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ሲሆን 25ቱ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ወረርሽኙ ሳይከሰት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ጀመሮ የነበር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የተለያዩ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች እና የጸጥታ አካላት የተካተቱበት ግብረ ኀይል ማቋቋሙ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።
ወረርሽኙን ለመከላከል መንግሥት በቀጥታ ከመደበው 5 ቢሊዮን ብር ጎን ለጎን ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ የጉዳት ደረጃ ለመቀነስ ወይም ለመከላከል የሀብት ማሰባሰብ እና ማከማቸት ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ በመሥራት ላይ ይገኛል። ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው!
በወረርሽኙ የተጠቁም ሆኑ የተጠረጠሩ ሰዎችን ለይቶ ለማቆየት እና አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ለማድረግ የሚረዱ ቦታዎችን ማዘጋጀትን በተመለከተ በመንግሥት ሥር ካሉ የሕክምና ተቋማት ባሻገር የተለያዩ ቦታዎችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። ትልልቅ አዳራሾች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲቀየሩ እና የሕክምና ክትትል እንዲደረግባቸው ከፍተኛ ሥራዎች ተሰርተዋል። በዚህ ረገድ የሚሊኒየም አዳራሽ አንዱ ነው። ከዚህ ቀደም የተለያዩ ትዕይንቶችን በማስተናገድ የሚታወቀው አዳራሽ ወደ ሕክምና ማዕከልነት ተለውጧል። በማዕከሉ አንድ ሺሕ አልጋዎች የተዘጋጁ ሲሆን ስምንት መቶ የሕክምና ባለሙያዎችም በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ ባሻገር በየክልሉም የኮቪድ 19 ምርመራ በሰፊው በዜጎች ላይ ለማካሔድ እንዲረዱ የመመርመሪያ ማዕከላት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። በዚህ ረገድም 20 የምርመራ ማዕከላት በሁሉም ክልሎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በቀጣይነት የማዕከላቱ ቁጥር እንደሚጨምር የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የመንግሥትን ጥረት ለመደገፍ እንዲሁም የዜግነታቸውን የውዴታ ግዴታ ለማበርከት የብዙዎች እጅ መዘርጋቱ በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ የተገኘ መልካም አጋጣሚ (blessing in disguise) ፈጥሯል። ሕዝብና መንግሥትንም ከመቼውም የተሻለ መደማመጥ ላይ ያደረሰ ሁኔታም የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ይህም ይበል ያሰኛል!
ጎን ለጎን አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም ተቋማት ቤታቸውን፣ የሕክምና ተቋማቸውን፣ ሕንጻዎቻቸውን በደግነት አበርክተዋል። እንደነዚህ ዓይነት እገዛዎች በአርዓያነት ታይተው ሌሎችም እንዲሁ አጠናክረው ሊገፉበት ይገባል። እነዚህ ልገሳዎች ወረርሽኙ ብርቱ ክንዱን ቢያሳርፍ ለመቋቋም ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ይሁንና በፍጥነት ሊሟሉላቸው የሚገቡ ግብዓቶችን እንዲሁም ባለሙያዎችን ማዘጋጀት ላይ በርትቶ ሊሠራ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
የሕክምና ማዕከላትን ከማስፋትና ከማጠናከር በዘለለ ወረርሽኙ በአጠቃላይ ንግድ እንቅስቃሴዎች፣ ምርታማነት፣ ሌሎች መደበኛና ኢመደበኛ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች እንዲቀዘቅዙ አድርጓል። ይህም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና የዕለት ጉረሳቸውን በመሥራት ደፋ ቀና የሚሉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ኅልውና ላይ አደጋ ጋርጧል። ከወረርሽኙም ባሻገር ይህ ሊፈጥር የሚችለው ማኅበራዊ ችግር ወይም ቀውስ ምናልባትም ወረርሽኙ ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ ያልተናነሰ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
በርግጥ የፌደራል መንግሥቱ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር እና ክልሎች በራሳቸው ይህንን ማኅበራዊ ቀውስ ለመከላከል ከሚሠሩት ሥራ በተጨማሪ በተለይ አቅም ያላቸው ዜጎች እና ተቋማት እርዳታ እንዲለግሱ ሳይውሉ ሳያድሩ ጥሪ አቅርበዋል። በምላሹም በከፍተኛ ደረጃ ሊያስመሰግን በሚችል ደረጃ ግለሰቦች እና ተቋማት በዓይነት ምግቦችንና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ምላሽ ሰጥተዋል። በመስጠትም ላይ ይገኛሉ። በጥሬ ገንዘብም በመቶ ሚሊዮኖች መሰብሰብ ተችሏል። ይሁንና ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አንድ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ወረርሽኙ በከፋ ሁኔታ ከተከሰተ ማኅበራዊ ቀውሱን ለመቋቋም 96 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል መባሉ እስካሁን በልግስና በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ የሰጡትን እጀ ሰባራ እንዳያደርግ ያሰጋል። በመሆኑም አዲስ ማለዳ የዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ልገሳው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ስትል በአጽንኦት ታሳስባለች።
እርዳታ ከማሰባሰቡ ጎን ለጎን መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት በአንክሮ ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ የተሰበሰበው እርዳታ በቀጥታ ለታለመለት ዓላማ ውሎ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እንዲሁም አገርን ከማኅበራዊ ቀውስ ለመጠበቅ ይውል ዘንድ ግልጽና ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋትን ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የእስከዛሬው ልፋት ውሃ ሊበላው ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል። አሠራሩም ለሕዝብ ይፋ የሆነ እና ግልጽ ሆኖ ሰዎች ይበልጥ እንዲረዱ የሚገፋፋ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወረርሽኙን ተከትሎ የሚፈራው ማኅበራዊ ቀውስ ላለመድረሱ ምንም ማስተማመኛ የለም።
ይህንን ስጋት አዲስ ማለዳ በፋሲካ ዋዜማ መሬት ላይ የታዘበችውን የእርዳታ አሰጣጥ ለአብነት በማንሳት ማስረገጥ ትፈልጋለች። ቀኑ የፋሲካ ዋዜማ ጠዋት ወደ ሦስት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ቦታው ደግሞ አዲስ አበባ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ መንደር በሚያስገባ አስፓልት ዳር የተከሰተ ነው። በዛ ያሉ የተጎሳቆሉ የሚመስሉ ሴቶች እንዲሁም ጥቂት ጎልማሳ ወንዶች አካባቢው ላይ ተከማችተዋል። እርዳታ የሚጠብቁ መሆናቸውን ያስተዋለችው አዲስ ማለዳ፣ የእርዳታ አሠጣጡ ግልጽነት ማጣት፣ ስርዓት አለመኖርና ጉልበታም ሰዎች በተደጋጋሚ የእርዳታው ተቋዳሽ መሆናቸውን ታዝባለች። ስርዓት አስከባሪ የደንብ ልብስ የለበሱ የፖሊስ አባላት ቢኖሩም ያን ያክል ስርዓት ለማስከበር ያደረጉት የጎላ ሚና አለመኖሩንም አስተውላለች፡፡ ይህም የሚያሳየው የግልጽነት ጉድለት እና የአሠራር ብልሹነትን ነው።
ሌላው ስጋት ደግሞ በሥመ እርዳታ ማሳባሰብ የማይገባቸው ሰዎች የራሳቸውን ኪስ ለማደለብ የመጠቀማቸው አዝማሚያ እየተስተዋለ መሆኑ ነው።
ለወረርሽኙ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚሰጡ ስጦታዎችን በአንድ ማዕካላዊ ቋት በማሰባሰብ በአገሪቱ ዙሪያ በተገቢው መንገድ ለማከፋፈል ያስችላል ተብሎ የሚገመት መመሪያ 63 የተባለ ሰነድ በመንግሥት እንደተዘጋጀ በዚህ ሳምንት ሰምተናል፡፡ በዚህ አሠራርም መሠረት ክልሎች የሰበሰቡትን እርዳታ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት የሚልኩ ሲሆን መንግሥትም የወረርሽኙን ስርጭት ተመርኩዞ አስፈላጊውን እርዳታ ለክልሎች የሚያከፋፍል ይሆናል፡፡ ይህ አሠራር የተሰበሰበው እርዳታ መጠንን በግልጽ ለማወቅ የሚረዳ ከመሆኑም ባሻገር ባለሃብቶች እና ሌሎች ለጋሾች በየክልሉ ባላቸው እንቅስቃሴ ምክንያት በተደጋጋሚ መዋጮ እንዳይጠየቁም ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንም እንኳን የሚሰበሰበውን እርዳታ መጠን በግልጽ ማወቅ ከማከፋፈል በፊት ምን ያህል እርዳታ ለማን እና የት እንደሚከፋፈል ለማወቅ የሚረዳ ቢሆንም ከክልል ወደ ፌዴራል መንግሥት ከዚያም ተመልሶ ወደ ክልል መሔዱ ጊዜ የሚገድል ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ተመልሶ ክልሎች ጋር የሚደርሰው እርዳታ ለታለመው ተጎጂ ግለሰብ መድረሱን መመሪያው በግልጽ ያስቀምጣል ተብሎ እንደማይታሰብ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ይህንን አስተካክሎ ተረጂው ድረስ የሚዘልቅ ስርዓት መፍጠር ተገቢ ነው፡፡
ስለሆነም አዲስ ማለዳ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እርዳታ ማሰባሳቡ ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን የተሰበሰበው እርዳታ ለታለመበት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ ግልጽ የሆነ አሠራር መዘርጋት፣ ማስፈጸምና ተጠያቂነትን አብሮ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ስትል በአጽንኦት ታሳስባለች። ይህ የአሠራር ስርዓት በተጠና መልኩ ከወዲሁ ታስቦበት መዘርጋት ይገባዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ወረርሽኑ ሊያደርስ ከሚችለው በላይ እና በከፋ ሁኔታ ዜጎች ለማኅበራዊ ቀውስ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መሆኑም ይህ ጉዳይ በቸልታ ሊታለፍ አይገባም!
ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012


