የኮሮና ቫይረስን ለመመርመር የተቋቋሙ ቤተ ሙከራዎች በአገር ዐቀፍ ደረጃ 22 መድረሳቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚያዚያ 22/2012 ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት በጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፣ የቤተሙከራዎቹ ቁጥር መጨመር ብዛት ያለውን ሰው ለመመርመር እንደሚያስችልና በዚህም በቀን ከ5 ሺሕ በላይ ሰዎችን ለመመርመር የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በተለያየ ምክንያት በአሁኑ ወቅት 15ቱ ብቻ ሙሉ በሙሉ የሚሠሩ ሲሆን፣ በአማካኝ በቀን አንድ ሺሕ ሰዎች ላይ ምርመራ እያካሄዱ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ሰዎች ለለይቶ ማቆያ ማእከላት የተዛባ አመለካከት አላቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ማእከላቱ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መስፈርት መነሻ በማድረግ የተቋቋሙና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችንና መሣሪያዎችን ያሟሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሰዎች ከውጪ በአውሮፕላንም ሆነ በየብስ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ እንዲሁም በአሰሳ እና ከኮሮና ተጠቂ ጋር ባላቸው ንክኪ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል፣ ቫይረሱ የሚገኝባቸውም ወደ ለይቶ ሕክምና ይወሰዳሉ ብለዋል።
ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ድረስ በአገር ዐቀፍ ደረጃ 17,842 ሰዎች የተመረመሩ ሲሆን፣ 131 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። 58 ሰዎች አገግመዋል፣ 3 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። 67 ሰዎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ 3,093 በክልሎች ደግሞ 10,490 በአጠቃላይ 13,583 ሰዎች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉም ነው የተባለው።
ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012



