የገቢዎች ሚኒስቴር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ183 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

0
883

የገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ አፈፃፀሙን በመከታተል በዘጠኝ ወራት 190 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 183 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል።
አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወይም የ25 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማሳየቱን የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባካሄደበት ወቅት ገልጿል።
የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው በውይይቱ ወቅት፣ ተቋሙ የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ የቆየ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ይህንን አፈፃፀም ለማስመዝገብ ያስችለው ዘንድ ባለፉት ዓመታት ከተገኙ ስኬቶችና ከታዩ ክፍተቶች አንፃር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ቆርጦ ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል።
አክለውም ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ የነበረውን የላቀ አፈፃፀም በማስቀጠል በቀሪው ወራት አፈፃፀሙን ከፍ ለማድረግ ከመንግሥት የተሰጠውን እቅድ ለማሳካት የነበረው የዝግጅት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የገቢ አሰባሰቡን ሥራ ለማሳካት ለባለድርሻ አካላትና ለግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ እውቅና የመስጠት፣ ግብር ከፋዮችንና ሠራተኞችን አወያይቶ የማዘጋጀት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የስትራቴጂክ እቅድ ፕላንና ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክተር ፍቃዱ ታደሰ በበኩላቸው፣ በአገራችን ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ በተፈለገው ሁኔታ እንዳልተሳካና አፈፃፀሙ እንደ ከዚህ በፊቱ ከዕቅድ በላይ ለመሰብሰብ እንቅፋት እንደሆነ አንስተዋል።
ፍቃዱ እንደተናገሩት፣ ከገቢ ድርሻ አንጻር በዘጠኝ ወራት የአገር ውስጥ ታክስ 100 ቢሊዮን ብር፣ የጉምሩክ ኮምሽን 82 ቢሊዮን ብር ድርሻ የነበራቸው ሲሆን፣ ከብሔራዊ ሎተሪ ደግሞ 139 ሚሊዮን ብር ድርሻ አለው። ይህም በአጠቃላይ ሲታይ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 183 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል።
የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 270 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here