ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ ውሳኔዎች ተላለፉ

0
760

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት ድቀት እንዳያስከትል ውሳኔዎች መተላለፋቸው ተገለጸ። የገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግሥት እና ኅብረተሰቡ ርብርብ እያደረገ ነው።

መንግሥት ቀደም ሲል ወረርሽኙ በምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በተለይ በውጭ ንግድ እና በአገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት፣ ባንኮች አስፈላጊውን የብድር ሽግሽግና ተጨማሪ ብድር እንዲያቀርቡ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በአሁኑ ጊዜም ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ ተቋማት ጉዳታቸው እየሰፋ እንዳይሄድ ተጨማሪ ኢኮኖሚ እርምጃዎች መውሰድ አስፈልጓል ተብሏል።

የኢኮኖሚው መቀዛቀዝንም ተከትሎ በቢዝነስ ተቋማት ላይ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለ 15 ነጥብ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ማሳለፉም ተገልጿል። በዚህም መሰረት የፌዴራል መንግሥት ከ1997 አስከ 2007 ውዝፍ የግብር እዳ ላለባቸው የቢዝነስ ተቋማት ስረዛ አድርጓል።
ግብር ከፍለው የኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ተቋማትም ውዝፍ ኦዲት ግኝታቸውን ውሳኔው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ፍሬ ግብሩን በሚቀጥለው የጊዜ ሰሌዳ ከፍለው እንዲጨርሱ መወሰኑ ተጠቅሷል። የፍሬ ግብራቸውን 25 በመቶ በመጀመሪያው በመክፈል ቀሪውን በተሰጣቸው ጊዜ ለሚከፍሉ ተቋማት የግብር ቅጣትና ወለድ ይነሳላቸዋልም ብለዋል።

ከዛም በተጨማሪ ሙሉ የፍሬ ግብሩን በአንድ ጊዜ ለሚከፍሉ ተቋማትም 10 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው የገለጹት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ውሳኔውን ለማስፈጸም ገንዘብ ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር ዝርዝር መመርያ እያዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ይሄን ውሳኔ የወሰነው በወረርሽኙ ምክንያት የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ለማነቃቃት ተቋማቱ ሠራተኞቻቸውን ሳይበትኑ ሥራቸውን መሥራት እንዲችሉ ለማገዝ እንደሆነም ኢዮብ መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here