ኢትዮጵያ በአንበጣ መንጋ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማጣቷን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ ሚያዚያ 20/2012 በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፣ ካለፈው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ የተከሰተው መንጋ በ198 ሺሕ በሚደርስ መሬት ላይ የበቀለ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል።
በስድስት ክልሎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር 170 ወረዳዎች የነበረ የበቆሎ፣ የማሽላና የስንዴ ሰብል በመንጋው ጉዳት እንደደረሰበት አስረድተዋል። መንጋውን በ260 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ኬሚካል በመርጨት መከላከል እንደተቻለም ሳኒ አመልክተዋል። ለዚህም የየአካባቢውን የሰው ኃይል በማንቀሳቀስና ለጋሽ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር ለመፍታትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ለማጠናከር ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ እንደሚያውሉና ከዓለም ባንክም 63 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማግኘት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩም በአካባቢያቸው መንጋው ሲከሰት ሪፖርት በማድረግና ማሳቸውን ከመንጋው እንዲከላከሉ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል። መንጋው እስከ ጥቅምት 2013 እንደሚኖር ትንበያዎች እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና አፋር አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ያደረሰውን ጉዳትና በቀጣይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ከአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በመቀናጀት ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በግብርና ሚኒስቴር ባገኘችው መረጃ መሰረት የበረሃ አንበጣው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተከማችቶ እየተራባ መሆኑን መዘገቧ ይታወሳል።
ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012



