አዲስ አበባን – ‹ምድራዊ ገነት› የማድረግ ጉዞ

0
1537

የከተማ ግብርና ባልተለመደባቸው አካባቢዎች ቃሉ ራሱ አሻሚ ይመስላል። ከተሜነትን ከግብርና መላቀቅ ተደርጎ በሚታሰብበት ሁኔታም ‹የከተማ ግብርና› አበባን ወይም ለጊቢ ውበት ዛፍን ከመትከል የዘለለ አድርጎ ማሰብ የሚችል ጥቂት አይደለም። በእርግጥ በአዲስ አበባ የጓሮ አትክልት የብዙ ቤተሰብን የምግብ ፍጆታ በተወሰነ መልኩ ይሸፍንና አልፎም ለገበያ ይቀርብ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ተገፍቶ ወጥቷል። ይህንንም ጉዳዩን የሚከታተሉ የዘርፉ ባለሞያዎች የሚናገሩት ነው።

በከተማ አርሰው አደሮች
ከሰባት ዓመት በፊት ነበር፣ የ40 ዓመቱ አረጋ ማሞ ኹለት ሔክታር መሬትን ከአዲስ አበባ ሃና ማርያም አካባቢ በ50 ሺሕ ብር የተከራዩት። ከዛን ጊዜ ጀምሮም አሁን ድረስ ፍራፍሬና አትክልቶችን በማምረት ለሱቆች እና ለሱፐርማርኬቶች እያቀረቡ ይገኛሉ።
ታድያ የአረጋ ጓደኞች ‹መሃል ከተማ ላይ ግብርና እንዴት ይታሰባል?› ሲሉ ተደንቀው ነበር። ምክንያቱም በከተማዋ እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ የተለመደ ወይም ከነአካቴው ያለ አይደለም። ነገር ግን አረጋ በተመሳሳይ መሬት በገጠር ሆኖ ከሚያርሰው አርሶ አደር የበለጠ ትርፍን በጥቂት ዓመታት ውስጥ በዛው ውስን መሬት ማግኘት ችለዋል።

ለአዲስ ማለዳም እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጡ፣ ‹‹ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋጠው አዲስ አበባ ድረስ ምርታቸውን ለመሸጥ ከሚመጡት በላይ ስኬታማ መሆን ችያለሁ››

ቁጥሮችም ለዚህ የአረጋ ሐሳብ ምስክር ሆነዋል። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በአማካይ በአንድ ሔክታር 36 እስከ 40 ኩንታል ቲማቲም ያመርታሉ። አረጋ ግን በአንድ ሔክታር እስከ 80 ኩንታል ቲማቲም በማምረት እጥፍ ማድረግ ችለዋል። ሲናገሩም አሉ፤ ‹በዓመት ሦስት ጊዜ አመርታለሁ። በዚህም በዓመት እስከ 400 ሺሕ ብር አገኛለሁ››

አረጋ እንደሚሉት ዘርፉ ሊያስገኝ ከሚችለው ጥቅም አንጻር በቂ ትኩረት አላገኘም። በዘርፉ የተሰማሩ አንዳንዶች እንደውም በፍርሃትና በሕጉ አስፈጻሚ ሰዎች ከዛሬ ነገ ተዘጋብን በሚል ስጋት ውስጥ ሆነው እንደሚሠሩ ነው ያነሱት። ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው መርካቶ ሦስት በሦስት በሆነች ክፍል ውስጥ በዶሮ እርባታ የተሠማሩት የሰሎሞን አይሳ ታሪክ ነው።

ሰለሞን መቶ ዶሮዎችን በማርባት እንቁላለችን ያመርታሉ። ታድያ በአካባቢው በሚሠሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ተደጋጋሚ ቅጣት ተቀጥተዋል። ‹እንዘጋብሃለን› የሚል ማስፈራሪያም በየጊዜው እንደሚደርሳቸው ያወሳሉ። ‹‹ዶሮና እንቁላል ስለማመርት ብቻ ነው የተቀጣሁት›› ብለው ሁኔታውን ገልጸውታል።

አዲስ አበባ
ባለፉት ዐስርት ዓመታት ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የፈለሱ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደል። አዲስ አበባም ከመቀበል ቦዝና አታውቅም። ከ13 ዓመት በፊት በተደረገ የሕዝብና ቤት ቆጠራም አምስት ሚሊዮን የነበረው ሕዝቧ አሁን በብዙ ርቀት ላይ እንደሚገኝ እሙን ነው። የከተማዋ ነዋሪዎችም ብዙውን ከከተማዋ ውጪ በሚመጡ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ የሆኑ ይመስላል። ይህም ነው ለዋጋ ንረትና ግሽበት እንዲሁም በፖለቲካ ግጭቶች ወቅት ነዋሪዎቿ የተለያዩ ምርቶችን ፍለጋ ለእንግልት የሚዳረጉት።

እስካለፈው ዐስር ዓመት ድረስም አዲስ አበባ ራሷን የቻለችበት ምርት ቢኖር ወተት ነበር። በኋላ ግን በአነስተኛ ደረጃ ሆነው በግለሰብ ደረጃም የወተት ምርት ላይ የሚሠሩት ከንግድ ውጪ እንዲሆኑ ተገፍተዋል። ይህንንም ያደረገው አንድም የከተማነት መስፋፋት ነው። እናም አሁን ከተማዋ ብዙ የወተት ምርትን በዙሪያ ካሉ ከተሞች ነው እየተቀበለች የምትገኘው። በአንጻሩ ደግሞ የአዲስ አበባ አባወራ ቁጥር ባለፈው አምስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሬ አሳይቷል።

የወተት ምርቱን ማሳያ ተጠቀሰ እንጂ በድምሩ የከተማ ገበሬዎች ቁጥር ባለፉት ዓመታት በእጅጉ ቀንሷል። ይህ የቁጥራቸው መቀነስ ቀጥሎ አሁን ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 86 ሺሕ የሚጠጉ በአነስተኛ ደረጃ የሚያርሱ ገበሬዎች በአዲስ አበባ ይገኛሉ። ከሰባት ወራት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ኮሚሽን መመሥረቱን ተከትሎ ጥሩ ተስፋ የታየ ሲሆን፣ ቢያንስ ቁልቁል እየወረደ የነበረው የከተማ ገበሬዎች ቁጥር መቀነስን ፍጥነት አርግቦታል።

በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ለአዲስ አበባ የግብርና ቢሮ ባለመኖሩ ምክንያት የከተማዋን የግብርና ውጤት፣ ምርት፣ የገበያ ሁኔታ፣ ፋይናንስና ግብዓት፣ ሥልጠና እና የግብር እፎይታን በተመለከተ የሚያስተባብርና የሚከታተል አካል እንዳይኖር አድርጓል። በዚህም ምክንያት የከተማ ግብርናን በቢዝነስ መልክ ለመሥራት ፍላጎቱን ቀንሷል።

ከላይ እንደተገለጸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ሁኔታው የተቀየረ ይመስላል። ይህም የሆነው በተለይም ምርት፣ የገበያ አቅርቦትና ለሥልጠና አስፈላጊው ግብዓት የማሟላት እንቅስቃሴ ስለተጀመረ ነው።

በጸጋዬ ደምሴ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በግብርና ላይ ያልተሰማሩና አትክልቶች የማያመርቱ አባወራዎች ብዛት በአዲስ አበባ 99.7 በመቶ ሲሆን በአንጻሩ በአፋር 94.9 በመቶ እንዲሁም በድሬዳዋ 94.2 ነው። በተመሳሳይ ፍራፍሬ የማያመርቱት ሲታይ፣ አዲስ አበባ መቶ በመቶ ፍራፍሬ አይመረትም። በድሬዳዋ 95.3 በመቶ እንዲሁም በአፋር 92.9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) እንዲሁም በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ዝቅተኛውን መስፈርት እንኳ አታሟላም። ይህም የሆነው አዲስ አበባ የከተማ ግብርና ፖሊሲን ዋጋ እንደሌለው ትታ በመቆየቷ ነው።

የከተማ ግብርና እና ገጽታው
የከተማ ግብርና ከተለያየ አንጻር ሊታይ ይችላል። አንደኛው አረንጓዴ የሆነ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር ነው። ይህም የሥነ ምኅዳር ስርዓትን ሚዛን ከመጠበቅ፣ ዘመናዊ ከተማን ከመገንባት፣ የሥራ እድል ከመፍጠርና በምግብ ራስን ከመቻል ጋር ግንኙነት አለው። በ2019 በተሠራና ‹Urban Agriculture: Another way to feed cities› ወይም ‹የከተማ ግብርና፡ ከተሞችን የመመገብ ሌላው አማራጭ› በሚል ርዕስ የተደረገ ጥናት እንደሚያስረዳው፣ ከ70 በመቶ በላይ አትክልት፣ ከ50 በመቶ በላይ የሰብል ምርት እንዲሁም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ካለ የእርሻ መሬት መካከል 24 በመቶ የሚሆነው የጠፋው ከ2006 እስከ 2011 ባሉ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው።

ጥናቱ ላይ የተጠቀሰው እንዲህ በሚል መንገድ ነው፤ ‹‹ትክክለኛ በሆነ የፖሊሲና የአሠራር እቅድ ማጣት ምክንያት የሕዝብ ብዛት መጨመር ምርታማ የነበረ የእርሻ መሬት እንዲታጣና አረንጓዴ አካባቢዎችም የሥነ ምኅዳር ሚዛንን ለመጠበቅ ያላቸውን ሚና እያሳጣቸው ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪም በ2035 ዘጠኝ ሚሊዮን ይደርሳል በሚለው ግምት መሠረት፣ በከተማ መስፋፋትና በኢንዱስትሪ ልማት ምክንያት አሁንም የእርሻ መሬቶች መጠን ይበልጥ መቀነሱ አይቀርም።››

ይህ በአግድም እረሻ (Horizontal Farming) የሚደረግ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወደ ላይ የሚመሠረት የከተማ ግብርናም ትኩረት አላገኘም። ይህ ወደ ላይ የሚደርግ ግብርና ወይም ሽቅብ እርሻ (Vertical Farming) አሁን አሁን እየሰፋና እየታወቀ የመጣ አሠራር ነው። ይህም የሰውን ልጅ ዘመናዊነትን እንዲሁም ከተፈጥሮ አለመነጠልን ማጣት ካለመፈለጉ የተወለደ ነው። የከተማ ግብርና ውስጥ ከሚካተቱት የእንስሳ እርባታ፣ የንብ ማነብ፣ የደን ልማትና መሰል እንቅስቃሴዎች በተጓዳኝ፣ ይህ ሽቅብ እርሻ የግብርና ዓይነት በሕንጻዎች ላይ ወይም ወደ ላይ በሚደረግ ግንባታ የሚደረግ አሠራር ነው።

ሽቅብ ማረስ (Vertical farming)
ሽቅብ እርሻ በኢትዮጵያ የተለመደ ባይሆንም ሕንጻ ባለባቸው አካባቢዎች ሊከናወን የሚችል ነው። በዚህ አስተራረስ የሚመረቱ ምርቶችና የሚተከሉ የዘር ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው። ይህም ፍጆታ፣ የምርት ውጤት፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ አየር ጸባይን የመቋቋም አቅም፣ የሥነ ምኅዳር ሚዛን እና ሌሎችንም ነጥቦችን ከግምት የሚያስገባ ነው።

በዚህም መሠረት ከተማ መሬት ከገጠሩ አንጻር 15 እጥፍ የበለጠ ምርታማ ሊሆን ይችላል። ይህም የሚሆነው በከተማ መሬት በዓመት በአንድ ስኩዌር ሜትር ላይ 20 ኪሎግራም ምግብ ማምረት ስለሚችል ነው። ይህም የምግብና ግብርና ድርጅት ያስቀመጠው መጠን ሲሆን፣ ድርጅቱ በዚህ አሠራር ከተሞች ፖሊሲያቸውን የከተማ መሬትን ለመጠቀም በሚያስችል መንገድ እንዲቀርጹ መነሻ ይሆናቸዋል ብሎ አስቀምጧል። ይህም የሥራ እድል ከመፍጠር ጀምሮ ትርፉ ቀላል የሚባል አይደለም።

በዓለም ዙሪያም ከተሞች ይህን ሽቅብ ማረስ ዘዴ ይጠቀማሉ። በዚህም ራሳቸውን በምግብ የቻሉ ሲሆን አልፎም ለውጪ ገበያ በመቅረብ ገቢ በማግኘት ላይ ናቸው። እንደ ቱርክ፣ ኩባ፣ ሕንድ፣ ፈረንሳይ፣ ኮርያ፣ ቻይና እና ሲንጋፖር ለዚህ ተጠቃሽ ምሳሌ ናቸው።
አዲስ አበባ እንደውም ከእነዚህ ከተሞች ፍራፍሬዎችን ታስገባለች።

በአዲስ አበባ ከገጠር የሚደረግ ፍልሰት እና ሥራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ የሚስተዋል ነው። ምንም እንኳ ከፍተኛ የሚባል አቅም ቢኖርም፣ በአዲስ አበባ ምንም ምግብ አይመረትም ማለት ይቻላል። ትኩስና የተፈጥሮ አትክልት እንዲሁም ፍራፍሬዎች ፍላጎት ግን በአንጻሩ ከፍተኛ ነው። ይልቁንም ቢያንስ በአዲሰ አበባ የሚገኙ ቻይናውያን የሚፈልጓቸው አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን በቀላሉ በአዲስ አበባ ሊመረቱ የሚችሉ ነበሩ።
ይሁንና ኢትዮጵያ የከተማ ግብርና ፖሊሲ የላትም። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከተወሰኑ አረንጓዱ ስፍራዎች በቀር፣ ይህን የከተማ ግብርና በይፋ እውቅና የሰጠው አይደለም።

እስከአሁን ባለው ሁኔታ፣ ደብረዘይትና ሆለታ እንዲሁም መልካሳ ያሉ የጥናትና ምርምር ማእከላት ብቻ ናቸው ለከተማ ግብርና አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት። እንደማሳያ ይጠቀስ ከተባለ ቢሾፍቱ ‹መቶ ዶሮ› በሚል ፕሮግራም የዶሮ እርባታ መናኽሪያ ሆናለች። ምንም እንኳ የከተማነት መገለጫ የሚባሉ የሕንጻ ግንባታዎች በብዛት ባይታዩባታም፣ ከተማዋ ለከተማ ግብርና አረአያ ሆና የምትጠቀስ ናት። በተለይም የሰብል ምርት እና እንስሳት አርባታ ላይ ቀዳሚ ሆናለች።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ቢሮ ኃላፊ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ለምግብ ፍጆታዋ ክልሎች ላይ ጥገኛ መሆኗን ጠቅሰዋል። ነገር ግን አዲስ አበባ ራሷን ለመመገብ አቅም አላት ብለዋል። አያይዘውም የከተማ ግብርና እንደውም የተፈጥሮ የሆነና ንጹህ ነገር ለመመገብ ይረዳል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ከችግር መንቃት
መለሰ ቶላ የሥራ ፈጣሪና በምሥራቅ ፖሊቴክኒክ የእንጨት ሥራ አሠልጣኝ ናቸው። እርሳቸውም በሽቅብ እርሻ የሚያገለግል ዘመናዊ የእንጨት ሥራን ሠርተዋል። ይህም ተንቀሳቃሽና በአንድ ጊዜ ሃምሳ የሚሆኑ ተክሎችን መያዝ የሚችል ነው። ‹‹የቦታና የቴክኖሎጂ እጥረት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ትልቁ ችግር የተሳሳተ አመለካከትና አዲስ ሐሳብ የማምጣት ችግር ነው። እንደ አዲስ አበባ ላሉ ብዙ ሕዝብ በሚገኝባቸው ከተሞች፣ ቦታ ትልቁ ፈተና ነው። እኛ እየሠራናቸው/እየፈጠርናቸው ያሉ ቴክኖሎጂዎች ለማንኛውም ዓይነት የከተማ ግብርና የሚያገለግሉና፣ ቦታን፣ ውሃን፣ አፈርን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው›› ብለዋል። ነገር ግን የሠሩትን የቴክኖሎጂ ውጤት ተቀብሎ በብዛት ለገበያ እንዲውል ለማስቻል የሚያመርት ኢንዱስትሪ አላገኙም።

የሮተር ንብ ማነብና የእንጨት ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ይድነቃቸው ዓለም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ‹‹ለከተማ ግብርና ቴክኖሎጂ ያለው ፍላጎት አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች እና ክልሎች ደንበኞቻችን እየሆኑ ነው። ለከተማ ንብ ማነብ ሥራ የተለያየ ዲዛይን ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች እያቀረብን ነው›› ብለዋል።

ይህን ያለውን አቅም በመቀስቀስ አኳያ ታድያ ከላይ እንደተጠቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ኮሚሽንን አቋቁሟል። ይህ ኮሚሽንም የተመሠረተበት ዓላማ በአንድ ወገን በአዲስ አበባ የከተማ መስፋፋት ምክንያት የተጎዱ ገበሬዎችን ድጋሚ ለማቋቋም ሲሆን በተያያዘም ከተማዋ በክልሎች ላይ ያላትን ጥገኝነት እንድትቀንስ ለማስቻል ነው።

ኮሚሽኑና እቅዱ
ኮሚሽኑ እንደ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ያሉ የከተማ ግብርና ፓርኮችን የመገንባት እቅዶች አሉት። እነዚህም ፓርኮችም ከ50 ሺሕ በላይ አዳዲስ የሥራ እድሎችን በየዓመቱ እንዲፈጥሩ ታልሟል። ኮሚሽኑም ሁሉንም አረንጓዴ አካባቢ፣ ክፍት ስፍራ፣ የሕንጻ ጣሪያ፣ ሬስቶራንቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጋራ መኖሪያ ኮንዶሚንየሞች፣ መንገዶችና የመንገድ ዳር፣ የመንገድ አካፋዮች፣ የወንዝ ዳር አካባቢና በተገኘው የአግድም እንዲሁም ሽቅብ እርሻ መንገዶች ተጠቅሞ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን የማምረት ሐሳብ አንግቧል።

ዘርፉን ለመቀላቀል ለሚፈልጉም ለሥልጠና እና ብድር የሚውል ተዘዋወሪ ፈንድ የማይዘነጋ ጉዳይ ነው ተብሏል። በዚህም አዲስ የሆነ የከተማ ግብርና መስፋፋቱ አይቀሬ ነው።

የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ፈትያ መሐመድ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹እንደ ካንሰር እና ስኳር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአንድ በኩል ተፈጥሮአዊ ያልሆኑና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ለምግብነት በመጠቀም ነው የሚከሰቱት። እነዚህም በከተማ ግብርና አማካኝነት ጤናማ በሆኑ ምርቶች ሊተኩ ይችላሉ›› ያሉ ሲሆን፣ አያይዘውም ‹‹ሁኔታዎቹ እንደሚያስረዱን ከሆነ ራሷን በምግብ የማትችል ከተማ መሆን የሚያዋጣን አይደለም›› ብለዋል።

እንደ ፈትያ ገለጻ፣ ኮሚሽኑ አዲስ አበባን ምድራዊ ገነት የማድረግ ሐሳብ ነው ያለው። አዲስ አበባ 27 ወንዞች አሏት፣ ይህም በሸገር ፓርክ ፕሮጀክት የሚጸዳ ይሆናል። ከዚያም በኋላ ከየቤቱ የሚወጣውን በስባሽ ቆሻሻ በማዳበሪያነት በመጠቀም በከተማ ግብርና ተያያዥ ጥቅሞችን መፍጠር ይቻላል፣ እንደ ፈትያ ገለጻ።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተርና የጥናት ባለሞያ ደሬሳ ተሾመ፣ በከተሞች ራስን መመገብ መቻል የከተማ ግብርና ያለውን ጠቀሜታ አጥብቀው ያነሳሉ። ‹‹በከተማና በገጠር መካከል ያለው መከፋፈል/ልዩነት አሁን እያበቃ ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ከተማና ገጠር የሚል የተለያየ ጽንፍ ሳይሆን፣ ግብርና ያለባቸው ከተሞችና የሠለጠኑ ገጠራማ አካባቢዎች ነው። እኛም በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና እና ከኦሮሚያ ክልልም ጋር በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን ግብርና ስለማልማት አብረን እየሠራን ነው›› ብለዋል።

ደሬሳ እንዳሉት፣ የከተማ ግብርና ክትትል የሚደረግበት ከሆነ በገጠር ካለው ግብርና 180 በመቶ በላይ ምርት ያስገኛል። ይህንን ትርፍ በማጤንም የሚሠሩበት የግብርና ምርምር ተቋም በአዲስ አበባ ሐሳቦችን ከመመዘንና ከመደገፍ ጀምሮ ግዙፍ የግብርና ቢዝነሶችን በጀት የሚያደርግ ማእከል የማቋቋም ሐሳብ አለው ብለዋል።

ይህም ማእከል ምርመራ የሚደግርባቸው ቤተሙከራዎች፣ የሥልጠና ግብዓት የተሟላለት፣ የብድርና የድጋፍ አገልግሎትን ያካተተ ይደረጋል ብለዋል። የሥልጠና ማእከላትን አስፈላጊነት ነጥለው በማንሳትም፣ ‹‹ተግባራዊ የሆኑ የሥልጠና ማእከላት ሳይኖሩ፣ የከተማ ግብርና፣ ጽንሰ ሐሳብ ብቻ ነው የሚሆነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም በግብርና ሚኒስቴር የከተማ ግብርና ሥራ ክፍል እንዲቋቋም አግዟል። ይህንንም ተከትሎ ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለኮሚሽን ሥራ የሚያግዙ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ ላይ ናቸው። እንደመነሻም በቦሌ ክፍለ ከተማ ያለውን አቅም በማጥናት ላይ ይገኛሉ።
‹‹የአዲስ አበባ ሙሉ አቅም ሳይታወቅ ፖሊሲ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ነው። የከተማ ግብርና በፖሊሲ የማይሰበሰብ ከሆነም፣ በዘላቂነት ውጤት የሚያመጣ አይሆንም። አንድ ጊዜ ያለው አቅም ከተለየ በኋላ ግን የከተማ ግብርና ወደ ተቀናጀ ንግድ ይቀየራል›› ደረሰ እንዳሉት ነው። አሁንም ያሉትን የከተማ ግብርና ሥራዎች እውቅና መስጠትና በቴክኖሎጂ፣ በገበያ ትስስርና መሰል መንገድ ማገዝ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል ባይ ናቸው።

ጌድዮን አድነው በወሰን አርክቴክትስ ቴክኒካል ማናጀር ናቸው። የከተማ ግብርና በአዲስ አበባ ጥቅም ላይ ያልዋለ አቅም ነው ይላሉ። ‹‹ሁሉም ማለት ይቻላል የአዲስ አበባ ሕንጻዎች ጣሪያቸው ባዶ/ገላጣ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርናን ከሕንጻ አርክቴክት ሥራ እና ግንባታ ጋር ለማያያዝ መመሪያም ሆነ ማበረታቻ ስለሌላቸው ነው›› ብለዋል።

ጌድዮን በቻይና የነበራቸውን ጉዞና ቆይታ በማስታወስ፣ በቻይና የሕንጻ ጣሪያዎች ተክሎች የሚታባቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የከተማ ግብርና ይህን ያህል የተወሳሰበ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ እንዳይደለ አጥብቀው ይገልጻሉ።

የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ከሆነችው ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው የተወሰደና፣ በአሸናፊ እንዳለ ተዘጋጅቶ በሊድያ ተስፋዬ የተተረጎመ፤

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here