መነሻ ገጽአምዶችሕግና-ፍትህ”ለማን አቤት ይባላል?” ለፍርድ ቤት! አዲሱ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እጅ ከምን

”ለማን አቤት ይባላል?” ለፍርድ ቤት! አዲሱ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እጅ ከምን

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መንግሥት በርካታ የፖለቲካ እና ሌሎች የማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስድ የቆየ ቢሆንም መዋቅራዊ እና ስር ነቀል ለውጥ አምጥተዋል የሚባሉት እርምጃዎች ውስን መሆናቸው ይነገራል። ከእነዚህም ውስን እርምጃዎች ውስጥ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤን በማቋቋም በሕግና ፍትህ ዙሪያ የሚደረጉ ማሻሻያዎች በገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲመራ መደረጉ በዋነኝነት ይጠቀሳል። አባድር መሐመድ እና ሚኒሊክ አሰፋ ይህን ነጥብ በማንሳት፤ በአማካሪ ጉባኤው ዳግም አነሳሽነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ መፅደቁ፤ አዋጁ ባለመኖሩ ምክንያት ከሕግ እና ከፍርድ ቤት የቁጥጥር ውጪ የነበሩትን የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት ለሕግ ተግዢ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የሚኖረውን ሚና ይዘረዝራሉ/ለማሳየት ይሞክራሉ።

የኢትዮጵያ የሕግና የፖለቲካ ታሪክ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሰላም እና የጦርነት፣ የመደጋገፍ እና የብዝበዛ እንዲሁም የአንድነት እና የክፍፍል ታሪኮቻችንን ወደ ጎን ትተን በሕግ ታሪካችን ላይ ብቻ ትኩረት ብናደርግ እንኳ አምባገነነናዊነት እና ገደብ የለሽ የሥልጣን ጥም የፍትህን እሴት በውስጣቸው ካነገቡ ባህሎቻችን ጋር ተዳብለው ለዘመናት አብረው እንደኖሩ እናስተውላለን። በአንድ በኩል ሥልጣንን ለአንድ ግለሰብ/ቤተሰብ/ቡድን ሲሰጥ የቆየው ነባሩ የሕግ ሥርዓታችን በአገራችን ታሪክ የጭቆና ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ እንዳገለገለ ብናውቅም በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ፍትሐ ነገሥት ያሉ የሕግ ሰነዶች የነገሥታቱን ፍርድ አሰጣጥ በፍትሕ በርትዕ ሊገሩ እንደሞከሩ እንረዳለን።

በኢትዮጵያን የሕግ እና የመንግሥት ታሪክ ውስጥ ከዘፈቀዳዊ ስርዓት ውጪ በሕግ እና ሕጋዊነት የሚገዛ በፖለቲካ ሥልጣን እንዳልነበረ እሙን ቢሆንም፣ እንደ ‹‹ሕግ ያደፈውን የደሀ ልብስ እና ያማረውን የባለጸጋ ልብስ አንድ ላይ ያስራል››፣ ‹‹በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ ያለፍርድ የሄደች ጭብጦዬ!”፣ ‹‹Akka harri hin gogne akka rachis hin dune (ኩሬውም እንዳይደርቅ እንቁራሪቷም እንዳትሞት አድርገህ ፍረድ)›› “በሕግ አምላክ ሲባል እንኳን ሰው ወራጅ ውሃ ይቆማል›፣ ‹‹Gar iyo geeri loo siman›› (ፍትህና ሞት አያዳሉም) እንዲሁም Mari’atan malee maraatan biyya hin bulchan (በመመካከር እንጂ በእብደት አገር አትመራም) የሚሉት ምሳሌያዊ አነጋሮች የፍትሕ እና የርትዕ መርሆች በባህላችን ውስጥ ትልቅ ሥፍራ እንዳላቸው ያሳዩናል።

በዛሬው አገረ መንግሥት ውስጥ በፍትህ ጽንሰ ሐሳብ እና እውነታው መካከል ያለው ተቃርኖ ፍሬው የተዘራው ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በአጼ ምኒልክ እና በአጼ ኃይለሥላሴ መመሥረት በጀመረችበት ጊዜ ነው። እጅግ የተወሳሰበው እና ለተጠያቂነት በማያመች ሥርዓት ውስጥ የተዋቀረው የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ የመቶ ዓመት እድሜ እንኳን ያላስቆጠረ መሆኑን ማመን ሊከብድ ይችላል። አሁን የተለያየ ሥም እና ቅርፅ ይዘው የምናገኛቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አብዛኞቹ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተመሰረቱ እንደሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የአስተዳደር ተቋማት ቁጥር እና ውስብስብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም ተቋማቱ በሕግ እና ሥርዓት አንዲመሩ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ሳይዘረጋ መቆየቱ የተቃርኖው አንዱ ማሳያ ነው። የአስተዳደር ተቋማቶቻችን ከሦስት ያላነሰ የፖለቲካ ለውጥን ያሳለፉ ቢሆኑም ለውጡን ተከትሎ የሚመጣው ርዕዮት ዓለሞ ጥገኛ እየሆኑ “ወደ ነፈሰበት ከመዞር” ባለፈ ከሃምሳ ዓመት በፊት ከነበሩበት ሁኔታ በመሰረታዊነት ተለውጠዋል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል በደርግ ጊዜ የነበረው “ማትሪክና ቀበሌ የሚሠሩትን አያውቁም” የሚለው ቀልድ አዘል አባባል የፍትህ ያለህ የሚል ጥሪ እና ከብዙ ምሬት የመነጨ ተስፋ መቁረጥን የሚያንጸባርቅ ነበር።

የቅርብ ጊዜ ትውስታችን የሆነው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በሚሰጠው ተስፋና በተግባር የአስተዳደር ስርዓቱ በፈጠረው ጥርነፋ መካከል ያለውን ተቃርኖ የሚያሳይ ምፀታዊ ጽንሰ-ሐሳብ ሆኖ ቆይቷል። የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት በሕግ እና ሥርዓት ከመመራት ይልቅ የባለሥልጣናት እና የገዢው ፓርቲ የግል ፈቃድ ማስፈፀሚያ እና የፓርቲው መዋቅራዊ ተዋረድ ነፀብራቅ ከመሆን ባለፈ ሙያዊነት (professionalism) የራቃቸው ሆነው ቆይተዋል።

የአስተዳደር ተቋሞቻችን በሁሉም ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ ሙስና ስር የሰደደባቸው እና ቅጥ ያጣ አቅም ማነስ የሰፈነባቸው እንዲሁም ዜጎች ላይ ለሚፈፅሙት በደል ማንም ተጠያቂ የማያደርጋቸው ሀይ ባይ ያጡ ሆነው ዘልቀዋል። በአንድ ታዋቂ የሕገ መንግሥት መምህርና ጸሐፊ አገላለጽ ኢትዮጵያ ከሕግ የበላይነት (rule of law) ይልቅ የሕግ አስገዢነት (rule by law) ከሚረጋገጥባቸው (ሕግ የፖለቲካ የበላይነት ለማስቀጠል ጥቅም ላይ ከሚውልባቸው) አገራት መካከል ቀዳሚ ምሳሌ ነች።

በተለይም ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም በፍርድ ሊወሰን የሚችል ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሊያገኝ እንደሚገባ ቢደነግግም፤ የአስተዳደር ተቋማት ከሥልጣናቸው ውጪ እና ሕገወጥ በሆነ መልኩ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች እንዲሁም የሚያወጧቸው መመሪያዎች በፍርድ ቤት ቀርበው ሕጋዊነታቸው ሊጣራበት/ሊከለስበት የሚያስችል የሕግ ሥርዓት (judicial review) አለመኖሩ ባለሥልጣናት እና የአስተዳደር ተቋማት ያለማንም ከልካይ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።

የአስተዳደር ተቋማት በፍርድ ቤት ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የሚያስችል ጠቅላላ የክለሳ ሥርዓት (judicial review) አለመኖሩ የሚያሳፍር የሕግ ሥርዓታችን ጎዶሎ/ክፍተት ሆኖ ሳለ፤ ጭራሹኑ አንዳንድ የአስተዳደር ተቋማት የሚወስኑት ውሳኔ በፍርድ ቤቶች እንዳይታይ/እንዳይከለስ የሚደነግጉ አዋጆች እና ደንቦች በሥራ ላይ ቆይተዋል። በአስተዳደራዊ ውሳኔዎች መብታቸው ተጥሶ ‹የፍትሕ ያለህ› ብለው ወደ ፍርድ ቤት ጎራ ያሉ ዜጎችም ‹አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማየት ሕጋዊ ሥልጣን የለንም› በሚሉ ፍርድ ቤቶች ምክንያት አንገታቸውን ደፍተው ያለመፍትሔ ተመልሰዋል። በዚህም ዜጎች የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደል በተመለከተ ‹ለማን አቤት ይባላል?› የሚል መልስ አልባ ጥያቄን ራሳቸው ጠይቀው ራሳቸው ከመመለስ በቀር ተስፋ አልነበራቸውም።

የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት በሕግ እና በሥርዓት እንዲመሩ፤ አለፍ ሲልም ለሚሠሩት ሥራ በፍርድ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሥርዓት የሚመለከተው የሕግ ዘርፍ ‹የአስተዳደር ሕግ› በመባል ይታወቃል። በዚህ ሰፊ የሕግ ዘርፍ ውስጥ የአስተዳደር ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን ሲተገብሩ የዜጎችን መብት እንዳይጥሱ ሥልጣናቸውን በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች የሚገራው የተለየ የሕግ ማዕቀፍ ደግሞ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ይባላል። በኢትዮጰያም ላለፉት በርካታ ዓመታት የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ሳይኖር መቆየቱ የአስተዳደር ተቋማት ገደብ የለሽ ሥልጣን እያካበቱ ለመሄዳቸው እና ቢሮክራሲው ላለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዋነኛ መንስኤ መሆኑ ይታመናል።

የንጉሡን መንግሥት ጨምሮ በኢትዮጵያ የተፈራረቁት ሁሉም ዘመናዊ መንግሥታት የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ የማውጣት እድል ነበራቸው። አብዛኞቹ የአገራችን ዋና ዋና ሕጎች በረቀቁበት የሀምሳዎቹ መጨረሻና የስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ረቂቁ ሳይፀድቅ እንደቀረ ጥናቶች ያመለክታሉ። ምንም እንኳ የአስተደደር ሕግ እጦት አሁን ያለው መንግሥት ከቀዳሚዎቹ መንግሥታት የወረሰው ችግር ቢሆንም፤ በአንፃራዊነት የተሻለ ነጻነት ይሰጣል ተብሎ የሚታመነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ከወጣ በኋላ የመንግሥት አስተዳደር በሕግና በዴሞክራሲያዊ መርሆች ይመራል የሚል ተስፋን ጭሮ ነበር።

ይሁንና ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግን ረቂቅን ለማፅደቅ የተደረገው ጥረት ሕጉ፣ የመንግሥትን እንደፈለገ የመወሰን ፍላጎት የሚገድብ ወይም “አሳሪ ነው” በሚል ምክንያት ተቀባይነትን ሲያጣ ተስፋው መልሶ ጨልሟል።

በቀድሞው አጠራሩ የፌዴራል ፍትህ እና ሕግ ስርአት ምርምር ኢንስቲትዩት በ1999 የአስተዳደር ሥነ-ሥርአት ሕግ የማዘጋጀቱን ሂደት ዳግም ቢያነሳሳም ወቅቱ ምርጫ 97ን ተከትሎ መንግሥት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብን በአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ በማስረፅ ሥራ የተጠመደበት ነበር። በመሆኑም ረቂቁ እንዲፀድቅ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።

ከዚህ በኋላም የቀድሞ ፍትሕ ሚኒስቴር፤ የፌዴራል ፍትህ እና ሕግ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት እና ዕምባ ጠባቂ ተቋም በተለያየ ጊዜ የተሳተፉበት የአስተዳደር ሥነ-ሥርአት ረቅቅ አዋጅ ዝግጅት ቢጀመርም በተገቢው ጊዜ ሳይጠናቀቅ ቆይቶ በ‹ደካማ አፈፃፀም› ምክንያት የወቅቱ ፍትህ ሚኒስትር ብርሓን ኃይሉ ከሥልጣናቸው ሲነሱ ከተጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ እስከመሆን ደርሷል

በእነዚህ ሂደቶች የተዘጋጁት ረቂቆች እና ረቂቆቹን ለማዘጋጀት የተከናወኑ ዳሰሳዊ ጥናቶች እጅግ ብዙ ጠንካራ ጎኖች ያሏቸው እና የብዙ ባለሙያዎችን ጥረት የጠየቁ ቢሆኑም፤ ከዚያም አለፍ ሲል “ጸረመንግሥት የሆኑ ወገኖች” እና “የመንግሥት እና የሕዝብ ጥቅም” የሚሉ ግልጽ ያልሆኑ ጽንሰ ሐሳቦች የተካተቱባቸው ከመሆናቸው አንፃር በተወሰነ ደረጃ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖሊሲ ተፅእኖ የሚታይባቸው ሆነው ተገኝተዋል።

በሚያዝያ 2010 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች መወሰዳቸው የማይካድ እውነታ ነው። አብዛኞቹ የለውጥ እርምጃዎች ጉልህ ታሪካዊ ክስተቶች ቢሆኑም በሕግና ፍትህ ዐይን ሲታዩ ግን የሥርዓት ለውጥ መነሻዎች እንጂ ሥር ነቀል የሆኑ ማሻሻያዎች ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በዚህ ሂደት ከተወሰዱ እርምጃዎች ውስጥ ምናልባት ቁልፍ ሊባል የሚችለው በሕግና ፍትህ ዘርፍ ተቋማዊ እና መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥን ለመተግበር እንዲያስችል በሚል ዓላማ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ መቋቋም ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ጉባዔው ገለልተኛ የሆነና የሰብዓዊ መብት፤ የዴሞክራሲ የሕግ የበላይነትና ተያያዥ ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የማማከርና ሙያዊ ድጋፍ የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶት ተቋቁሟል። ከዛም በኋላ በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ባልተለመደ መልኩ ከፖለቲካዊ ፍላጎትና ግፊት ነፃ ሆኖ ሙያዊነትን፣ ሙያዊ ስነ-ምግባርንና የአባላቱን ልምድና ሕሊና መሠረት በማድረግ ሳይንሳዊ ሊባል በሚችል ደረጃ ርትዕና ጥናት ላይ የተመሰረተ የሕግ ለውጥ ሥራን ሲመራ ቆይቷል።

ይኸው ጉባዔ የሕግ እና ፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ዕቅድ ውስጥ በማካተት እንቅስቃሴ ካደረገባቸው ቀዳሚ ጉዳዮች ውስጥ በረቂቅ ደረጃ ላይ የነበረውን የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ዝግጅት ሂደትን እንደ አዲስ ማስጀመር ነበር። ለዚሁ ዓላማ የሚሆን የሥራ ቡድን ተዋቅሮ በርካታ አካላትን ያሳተፈ እና አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ከፈጀ የዝግጅት ሂደት ታልፎ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን በአገራችን የመጀመሪያ የሆነው የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ መጋቢት 29 ቀን በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ወጥቷል።

አዋጁ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያ የሚያወጡበትን እና ውሳኔ የሚሰጡበትን ሥነ-ሥርዓት በዝርዝር የደነገገ ሲሆን በዋናነት ግን እነዚህ መመሪያዎችና ውሳኔዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበት ሥርዓት (judicial review) በአገራችን የሕግ ሥርዓት ውስጥ ወጥ በሆነ እና በተሟላ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጀመር የሚያስችል ይሆናል። በመሆኑም በፌዴራል የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔ እና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ የፍርድ ውሳኔ የሚያገኝበት ሥርዓት በይፋ ተዘርግቷል።

በአዋጁ መሰረት የአስተዳደር ጉዳዪች ለክለሳ የሚቀርቡት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው። ሆኖም መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ውሳኔ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰበር የሚቀርብበት አካሄድ የተጠበቀ ነው። መመሪያዎች ላይ የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ ደግሞ በማንኛውም ሰው መቅረብ የሚችል ሲሆን፣ በአስተዳደር ውሳኔዎች ላይ የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ ግን በውሳኔው ጥቅሙ በተነካበት ሰው ብቻ የሚቀርብ ይሆናል።

አዋጁ እንደሚደነግገው ከሆነ የአስተዳደር ጉዳዮች ለፍርድ ቤት ክለሳ እንዲቀርቡ የሚያደርጉ ምክንያቶች ውስን ናቸው። የአስተዳደር ተቋማት የሚያወጡት መመሪያ በፍርድ ቤት የሚከለሰው መመሪያ አወጣጥን የተመለከቱትን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል የወጣ ከሆነ ወይም መመሪያው ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ በሆነ መልኩ ከወጣ ወይም በማናቸውም መልኩ ሕግን የሚጥስ ሆኖ ሲገኝ ነው።

የአስተዳደር ውሳኔዎች በፍርድ ቤት ሊከለሱ የሚችሉት ደግሞ ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ በአዋጁ የተደነገጉ መርሆች የተጣሱ እንደሆነ ነው። መርሆቹ የአስተዳደር ውሳኔዎች የአስተዳደር ተቋሙን የሥልጣን ወሰን ሊያልፉ እንደማይገባቸው፤ አግባብነት ያለውን ጉዳይ ከግምት ያስገቡ እና በምክንያት የተመሰረቱ ሊሆኑ እንደሚገባ የሚደነግጉ ናቸው። የአስተዳደር ውሳኔዎች የሕዝብን እኩልነት ያከበሩ፤ በተገልጋዮች ጥቅም እና ተቋሙ በሚያስፈፅመው ሕዝባዊ ዓላማ መካከል ሚዛናዊነትን መጠበቅም የሚገባቸው እንደሆነ ተደንግጓል።

የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ግልጽ የሆነ ሂደትን የሚከተል እና የዜጎችን የመሰማት መብት የሚጠብቅ እንዲሆንም ይጠበቅበታል። ስለሆነም ከእነዚህ መርሆዎች አንዱንም እንኳ ሳይከተል የተሰጠ ውሳኔ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሊሰጥበት ይችላል።

ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ የአስተዳደር መመሪያዎች እና ውሳኔዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበት ሁኔታ የሌለ ቢሆንም በሌሎች ልዩ ሕጎች የአስተዳደር ተቋማት እና አስተዳደራዊ የዳኝነት አካላት የሰጧቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች ወደ ተለያዩ የፍርድ ቤት እርከኖች በይግባኝ የሚቀርቡበት አካሄድ እንደተጠበቀ ነው። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን መመሪያ ወይም የአስተዳደር ውሳኔ የማፅናት፣ በሙሉ ወይም በከፊል መሻር የሚችል ሲሆን የአስተዳደር ውሳኔዎችን ተክቶ የራሱን ውሳኔ የመስጠትም ሆነ የማሻሻል ሥልጣን ግን አይኖረውም።

- ይከተሉን -Social Media

በመሆኑም የአስተዳደር መመሪያም ሆነ ውሳኔ በሙሉ ወይም በከፊል በፍርድ ቤት በሚሻርበት ወቅት የአስተዳደር ተቋማቱ ራሳቸው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተጠቆሙ ግድፈቶችን የማስተካከል እና የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች ተከትለው እንደገና የመሥራት ግዴታ ይኖርባቸዋል።

የአስተዳደር ውሳኔዎች እና መመሪያዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበት ሥርዓት በሕግ ሥርዓታችን ውስጥ መዘርጋቱ አስተዳደራዊ ፍትሕን ከማስፈን ባለፈ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነትን በመገንባት ረገድ ይህ ነው የማይባል ሚና ይኖረዋል። በአስተዳደር ተቋማት የ”አቦ ሰጥ” ውሳኔ፣ በባለሥልጣናት ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ፣ እንዲሁም በአዋጅ የተሰጠን መብት ያለአግባብ በሚገድቡ መመሪያዎች ምክንያት መብታቸው የተጣሰባቸው ዜጎች አሁን አቤት የሚሉበት አላቸው – ፍርድ ቤት!

እነሆ ከዚህ በኋላ ጥያቄው ‹‹በአስተዳደር ተቋማት የሚገባውን አገልግሎት ለማግኘት ለዘመናት ኢ-መደበኛ መንገዶችን ሲጠቀም የነበረው የማኅበረሰብ ክፍል አዲሱን አዋጅ ተከትሎ የአስተዳደር በደሉን ይዞ ለፍርድ ቤቶች ‹አቤት› ይላል? ወይስ በለመደው አሰራር ይቀጥላል?››፤ ‹‹ዐስርት ዓመታትን ያስቆጠረ የተዓማኒነት ችግር ያለባቸው ፍርድ ቤቶችስ የዜጎችን የአስተዳደራዊ ፍትሕ ጥማት በምን ያህል ደረጃ ያረካሉ?›› የሚለው ነው።

እነዚህ ጥያቄዎች በመጪው ጊዜ ፍትህ እየጨመረ የሚመጣበት እንዲሆን የማድረግ ግዴታ በሁሉም ላይ የሚወድቅ ይሆናል። መንግሥት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔን በማቋቋም የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ከዘመናት በኋላ እንዲጸድቅ በማድረጉ ምስጋና የሚቸረው ቢሆንም የሕጉ መፅደቅ የሚኖረው ፋይዳ በአገራችን አስተዳደራዊ ፍትሕን ለማስፈን ከሚደረግው ረጅም ጉዞ ላይ ግማሹን መንገድ ማቃለል ብቻ ነው።

በመሆኑም መንግሥት አዋጁን የሚመጥን ተቋማዊ ለውጥና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ሕጉ ቀጣይነት ባለው መልኩ በተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ ይኖርበታል። እንዲሁም በአስተዳደር ተቋማት ውስጥ ያሉ ነባር እና አዲስ ተቀጣሪዎች፣ ሹመኞች፣ ዳኞች እና የሕግ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች በቀጣይነት ሕጉን እያወቁ ተግባር ላይ ማዋል እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዜጎች በአዋጁ የተረጋገጠላቸውን መጠየቅ እንዲችሉ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ዜጎችን በመወከል አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በፍርድ ቤት ክርክር የሕዝብ ጥቅምን የሚያስከብርበት መንገዶችን (public interest litigation እና legal aid services) ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል። በአዋጁ መሰረት የአስተዳደር ጉዳይ ችሎት እንዲያቋቁም የሚጠበቀው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ላይ የተሻለ እውቀት እና ግንዛቤ ያላቸውን ዳኞችን ማሠልጠን ይጠበቅበታል።

ከሁሉም በላይ ግን የዚህ ሕግ እና የጠቅላላ ፍትሕና የሕግ ስርዓቱ ለውጥ ስኬት የሚረጋገጠው ዜጎች የወጡትን አዋጆች ተገን አድርገው ለመብታቸው ዘብ ሲቆሙ እና የመብት ጥሰቶች ሲያጋጥሙም በተለይም የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ በሚደነግገው መሰረት ጉዳያቸውን በቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ጭምር ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ነው።

አባድር መሐመድ (በሕግ ሳይንስ ዶክቶሬት/J.S.D.)፣ የሰብዓዊ መብት ጠበቃ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሴንት ቶማስ ዩኒቨርሲቲ ሰብአዊ መብቶች መምህር እና በሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።
ሚኒሊከ አሰፋ በተ.መ.ድ የስደተኞች ተቋም ተባባሪ የሕግ ባለሙያ እና ተመራማሪ ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች