የምጣኔ ሀብት ድቀት በኮቪድ-19 ሚዛን

0
1108

ዓለም አለኝ የምትለውና ስትዘረዝር የኖረችው ስርዓት ሁሉ በአንድ ቅንጣት በማይሞላ ተዋህስ ምክንያት ተመሳቅሏል። የሰዎች አኗኗርና ሕይወትም ተቀይሯል። ከወራት በፊት ዓለምን የተዋወቀው ኮቪድ 19 የሚል ሥያሜ የተሰጠው ኮሮና ቫይረስ፣ በዓለም ማኅበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅሰቃሴ ገብቶ ሚዛን አስቷል። በተመሳሳይ ሚዛን እየሳቱ ካሉና ወደ ቀደመ ነገራቸው ለመመለስ የማይገመት ጊዜና ገና የማይታወቅ መንገድ ለሚፈልጉ ኪሳራዎች ከተዳረጉ ዘርፎች መካከል ደግሞ አንዱ ምጣኔ ሀብቱ ነው።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ ድቀትን እያስተናገደ ነው። ይህም ከዛሬ ይልቅ ነገ ጎልቶ እንደሚታይ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ጥቂት አገራት ደግሞ ከከፋው ኪሳራ የዳኑ ይመስላል። ወረርሽኙና ተጽእኖው በምጣኔ ሀብታቸው ላይ ብዙም ጉዳት አያደርስባቸውም ማለት ግን ምንም አያርፍባቸውም ማለት እንዳይደለ ማሁራን ይናገራሉ። እንደውም የፖለሲ ለውጦችና የአሠራር መቀየሮችን የሚጠይቁ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ታድያ ኢትዮጵያስ እንዴት ትሆናለች? አሁንስ እንዴት ይዟታል? አሁን ያሉ መረጃዎች ምን ያመለክታሉ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ። የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ ይህን ሐሳብ በማንሳት የሚመለከታቸውን የምጣኔ ሀብት እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ የግብርና ባለሞያዎችን በማነጋገር፣ መዛግብትንም በማገላበጥ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

አገራት በተለያዩ ጊዜያት በነባራዊ ሁኔታዎች ተገፍተውም ሆነ ራሳቸውን እየተለዋወጠ ከሚመጣው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማስተካከል፣ በአንዳች ምክንያት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲያቸውን ሲያሻሽሉ ወይም ሲለዋውጡ ይስተዋላሉ። በተለይም ደግሞ አገራት የተለያዩ ክስተቶች ሲያጋጥሙ ጊዜያዊ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን አስቸኳይ እርምጃዎችን በምጣኔ ሀብት ፖሊሲያቸው ላይ ይወስዳሉ፤ በዚህም የተነሳ ቀጣይ የምጣኔ ሀብት አቅጣጫዎችን ቀጣይነት ባለው መንገድ እስከ ማስተካከል ድረስ ይደረሳሉ።

ለአንድ አገር የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ማለት በዛ አገር ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሴክተር በተናጠል በነጠላ በመውሰድና አንድ ተጨባጭ ግብ በማስቀመጥ፣ አጠቃላይ የኹሉም ሴክተሮች ድምር እንደ አገር ሊደረስበት ከሚፈለገው ስፍራ ላይ የሚያስቀምጥ አካሄድ ነው። ምጣኔ ሀብት የአንድ አገር ልዕለ ኃያልነት በመጀመሪያ ደረጃ በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በምጣኔ ሀብት የጎለበቱ አገራት በፖለቲካውም ሆነ በማኅበራዊ ዘርፍ በዓለማችን ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳዳሪ የሚባሉ አገራት ናቸው። እነዚህም የምጣኔ ሀብት ፖሊሲያቸው ወደፊት ሊደርሱበት ከሚፈልጉት ግብ አንጻር ከወዲሁ የሚተልሙት እና በምጣኔ ሀብቱ ዘርፍ የሚሠራውን ሥራ የሚተገብሩበት ዋነኛ መሣሪያም ነው።

በአንድ አገር ምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች ወይም ፖሊሲዎች ተግባራዊ የሚሆኑት የአገሩ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ታሳቢ ተደርጎ፣ መሥራት የሚችለውን የሰው ኃይል ተመርኩዞ የሚተገበር ሲሆን በአገር ውስጥ ያለውን ግብር ተመን፣ የሥራ እና ሠራተኞቻቸውን የገበያ ሁኔታ፣ የንግዶችን የባለቤትነት ጥያቄዎችን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ እና በመንግሥት ጥልቅ ውሳኔዎች የሚተገበሩ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች እንደሆኑ ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ የአንድ አገር መንግሥት ከአገር ውስጥ ያለውን የገቢ አለመመጣጠን በሀብታም እና በድሀው ኅብረተሰብ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማመጣጠን ለአገር ይበጃል ያለውን የሚቀይስበት አንደኛው እንቅስቃሴ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ነው።

ይሁን እንጂ በአገራት የተተለሙ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎች የታለመላቸውን ግብ የማይመቱበት አጋጣሚዎች እልፍ ናቸው። ከእነዚህ የተለያዩ ተግዳሮቶች መካከል የአፈጻጸም ችግር እንዲሁም አስገዳጅ ሁኔታዎች የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎች ተግባራዊነታቸው ሊታጠፍ እና ስኬታቸው ሊስተጓጎል የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። በተለይም ደግሞ በታዳጊ አገራት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ ማሻሻያ ሲደረግባቸው እና የተግባራዊነታቸው ጉዳይ ሲገመገም ይታያል።

አዳጊ አገራት ለረጅም ጊዜያት ረግቶ እና ጸንቶ ከማይቆመው ምጣኔ ሀብታቸው ጉዳይ አንጻር ተደጋጋሚ እና ፈጣን ለውጦችን በምጣኔ ሀብት ፖሊሲያቸው ላይ ይተገብራሉ። ይህም ደግሞ በዘርፉ ጠለቅ ያለ ምርምርና ልምድን ባካበቱ ምሁራን ዘንድ ትልቅ ትችት እና ውግዘት ሲያስከትልባቸው ይስተዋላል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ምሁራን በተደጋጋሚ በሚለዋወጠው የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ላይ ከዘላቂነቱ ይልቅ የፊት የፊት የእሳት ማጥፋት ሥራ እና ለችግሩ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ከመስጠት ውጭ የረጅም እና ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት ሥራ አይሠራም ሲሉ ይተቻሉ።

መንግሥታት ለሕዝባቸው የዕለት ጉርስ ለመስጠት ከመጣር ባለፈ ለዘላቂነት ቋሚ የሆነ ገቢ እንዲኖራቸው ማድረግ ከባድ እንደሚሆንባቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይተነትናሉ። በተለይ እንደዚህ በተዳከመ እና በርካታ ችግሮች ያሉበት ምጣኔ ሀብት በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ባጋጠሙ ጊዜ ደግሞ ችግሩን ተቋቁመው ማለፍ የሚያስችል ጥንካሬ ስለማይኖራቸው በአገራት ላይ የሚያሳድረው ጫና እጅጉን የሰፋ ይሆናል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ነው ለአጭር ጊዜ በሚቆይ ችግር እጅግ ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ በአንድ አገር ውስጥ ለከፋ ችግር ወይም ለአጣዳፊ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚጋለጠው።

እንደዚህ አይነት ችግር በሚከሰትባቸው አገራት ውስጥ በዋናነት ችግሩ የፊት ገፈት ቀማሽ የሚሆነው በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ኅብረተሰብ መሆኑ እና መንግሥትም ዜጎቹን ከመደገፍ አንጻር አመርቂ ሥራዎችን መሥራት ሳይችል ሲቀር በአገሩ ውስጥ ያለውን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ድክመት እና የአጭር ጊዜ መፍትሔ ብቻ እንደሚከትል አመላካች እንደሆነ በርካቶች በጥናታዊ ጽሑፎቻቸው ላይ አስቀምጠዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከችግሩ ማለፍ በኋላም ቢሆን አንድ ጊዜ የተመታውን እና ምህዋሩን የሳተውን ምጣኔ ሀብታቸውን እንዲያንሰራራ ለማድረግ ረጅም ዓመታትን መታገስ እና ተከታታይ እድገቶችን ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሁሉ መሀል ከለጋሽ አገራትና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በብድር መልክ ሊወስዱ ይችላሉ ማለት ነው።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎችን በማውጣት እና ለተግባራዊነቱም በመትጋት በርካታ እንቅስቃሴዎችን ስትተገብር ቆይታለች፤ አሁንም እየተገበረች ትገኛለች። ይልቁንም ኹለቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም በቀጣይ የሚመጣው የዐስር ዓመት ፖሊሲ እና ሦስት ዓመት ጊዜ ገደብ የተሰጠው የአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ፖሊሲ ተጠቃሾች ናቸው።

ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ተከስተው ከባድ ችግር ጥለዋት ማለፋቸው የሚታወስ ነው። ይህንንም ተከትሎ እንደ ሌሎች አገራት ኢትዮጵያም የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እና ተግባራዊ በማድረግ ሰፊ ሥራዎች እንደተሠሩ ይታመናል።

በአሁኑ ወቅት በተለይም ከዓለም ዐቀፉ ደረጃ ከተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ታይቷል። በዚህም መሰረት በመጋቢት ወር መጨረሻ ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ባወጣው ሪፖርት በዚህ ዓመት ይሆናል ተብሎ ከታሰበው የአገራት ምጣኔ ሀብት ዕድገት ከፍተኛ ልዩነት ያለው የመቀዛቀዝ እንደሚያሳይ ጠቁሟል። ሪፖርቱ እንዳሰፈረው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ስድስት በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ የተተነበየ ቢሆንም በቅርቡ ዓለምን በተቆጣጠረው ወረርሽኝ አማካኛነት ወደ ሦስት ነጥብ ኹለት በመቶ ዕድገቱ ዝቅ እንደሚል አስታውቋል።

‹ሴፈስ ካፒታል› የተሰኘው ዓለም ዐቀፋዊ የምጣኔ ሀብት አማካሪ እና አጥኚ ድርጅት በተለይም ደግሞ በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ቀናት ውስጥ ባወጣው ግኝት በዓለም ዐቀፍ ገበያ በተለይም ደግሞ በነዳጅ አምራች እና ሻጭ አገራት ላይ ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ እንደሚከሰት ጠቅሷል። ለዚህም ደግሞ እንደ ምክንያት አድርጎ ያስቀመጠው የነዳጅ ዋጋ በዓለም ዐቀፉ ገበያ ላይ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መቀነሱን ነው።

አጥኚ ድርጅቱ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የምታስገባውን ነዳጅ ምርት መጠን ብታስገባ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታስቀር አስታውቋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን በዚህ ረገድ ተጠቃሚ ቢያደርግም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ቀጥተኛ የውጭ ኦንቨስትመንት ግን ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ ሊያደርግ እንደሚችል ሪፖርቶች ያመላክታሉ። በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የሚሳበው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ኹለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ዝቅ እንደሚል በተባበሩት መንግሥታት ንግድና የልማት ድርጅት አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉትን አሠራሮች እና በመንግሥትም በኩል መደረግ ያለባቸውን የፖሊሲ ለውጦች በተመለከተ በርካታ የዘርፉ ምሁራን በጥናታዊ ጽሑፎቻቸው እንዲሁም በሚሰጧቸው አስተያየቶች ሲናገሩ ይስተዋላሉ። የተለያዩ ሴክተሮች የተለያዩ አይነት የድጋፍ እና ፖሊሲ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጋቸው እና በተለይም ደግሞ አንዳንዶች አፋጣኝ ምላሽ እና መንግሥታዊ ውሳኔ የሚሹ እንደሆኑ ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ በርካታ ጽሑፎችን ያሳተሙት ፐሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ በቅርቡ የተከሰተውን ዓለም ዐቀፋዊ ወረርሽኝ ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት ድቀት እንደሚከሰት አብዛኛውን ዘርፍ በመዳሰስ አስቀምጠዋል። ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ መስኩ ላይ የሚያሳድረው ጫና እና በመንግሥት መወሰድ የሚገባውን የፖሊሲ ለውጥ በተመለከተም ባሳተሙት ጽሑፍ በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል።

በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው በዋናነት የሚመገበው በአገር ውስጥ ተመርቶ ለፍጆታ በሚሆን የግብርና ምርት ላይ በመሆኑ የተከሰተውን ዓለም ዐቀፋዊ ወረርሽኝ ተከትሎ ከፍተኛ ሊባል በሚችል ሁኔታ አደጋ ውስጥ አትገባም፤ ከውጭ የሚገባው ምግብ ሰፊው ሕዝብ የሚመገበው አይደለም ሲሉ ይናገራሉ። ይሁን አንጂ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አብዱልመናን አሕመድ ምላሻቸውን ሲሰጡ ‹‹ምግብ በአገር ውስጥ ቢመረትም፣ በእርዳታና በግዢ ለምሳሌ ስንዴ በብዛት ከውጪ እናስገባለን። በዓለም ዐቀፍ ደረጀ የምግብ እጥረት ከተፈጠረ እኛንም በተወሰነ ደረጃ መንካቱ አይቀርም›› በሚል ያለውን ተመጋጋቢነት እና ከገቢ ንግድ ጥገኝነት አለመላቀቃችንን ያሳያሉ። አያይዘውም ከዓለም ዐቀፉ የምግብ ዕጥረት ዳፋ ኢትዮጵያም እንደማይቀርላት ያስረግጣሉ።

የግብርናው ዘርፍ
በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ የሆነው ኅብረተሰብ ክፍል በእርሻ ዘርፍ የተሰማራ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ የእርሻውን ዘርፍ እድገት ከመጣበት ጊዜ እና ከዘመነው ቴክኖሎጂ ዘመነኛነት አንጻር በማሳደግ በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንዳልሆነ እና እድገት እያስመዘገበ እንዳልሆነ ከዓመት ዓመት ከተረጂነት ያልተላቀቀው የአርሶ አደሩ ኑሮ ይመሰክራል። በተለይ ደግሞ አብዛኞች እንደሚስማሙት በገጠር የሚታየው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና እሱንም ተከትሎ የሚከሰተው የተበጣጠሰው የእርሻ መሬት ለምርታማነቱ ማነስ እንዲሁም አርሶ አደሩን መግቦ ለገበያ ከመትረፍም ባሻገር ለአምራች ዘርፍ ግብዓት ለመሆን እጅግ አናሳ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የምጣኔ ሀብት ምሁር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምጣኔ ሀብት መምህር አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚህም ግብርናው ከመጣበት አንጻር ወደ ፊት በማደግ እና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የግብርና ምርት እንደመተካት ፋንታ ራሳችንን ሳንመግብ ጭራሹኑ በየዓመቱ ከፍተኛ የወጭ ምንዛሬን ወጪ ተደርጎ የግብርና ምርት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ይናገራሉ።

‹‹ግብርናውን ለማጎልበት ኹለት መንገዶችን ማየት ይጠበቅብናል። አንደኛው የሰውን ምርታማነት መጨመር ሲሆን ሌላው ደግሞ የመሬቱን ምርታማነት መጨመር ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ። ይህን ሲያብራሩ፤ በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለውን የአምራች ኃይል በማጥናት አንድ ሰው ምን ያህል በግብርናው ዘርፍ ምርታማ መሆን ይችላል የሚለውን በመለየት ግብርናው ላይ በከፍተኛ ተሳትፎ እንዲሰማራ ማድረግ ነው። በዚህም ሂደት ታዲያ ገንዘብ፣ መሬት እንዲሁም የሌሎች የግብርና ግብኣቶቸ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ይላሉ። በተለይ ደግሞ ገበሬው በዋናነት የሚያጋጥመውን የመነሻ የገንዘብ አቅም መንግሥት ወይም በተዋረድ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሩን ምርታማነት በመጨመር ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል ያብራራሉ።

በመሬትም በኩል ቢሆን እንድ አርሶ አደር እንደ አንድ አባውራ ለእርሻ የሚኖረው የመሬት ስፋት ከአንድ ሔክታር በታች በአማካኝ ነው የሚሉት አጥላው፣ ይህንንም በተመለከተ መንግሥት ክላስተር በሚል የጀመረውን አሰራር ቢያጠናክርበት ምርታማነት ይጨምራል ሲሉ ይናገራሉ። ክላስተር አሰራር ትናንሽ የእርሻ መሬት ያላቸውን አርሶ አደሮች በአንድ ላይ በማድረግ የእርሻ መሬቱን በመጨመር የአርሶ አደሮችን ምርታማነት መጨመር እንደሚቻል አጥላው ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሚተርፈው ጊዜ ከእርሻው ባለፈ ወደ እርባታ ዞር በማድረግ ዘርፈ ብዙ የሆነ የግብርና ምርታማነትን በሰዎች ዘንድ መጨምር እንደሚቻል ይናገራሉ።

በእርሻው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ሌላኛው ግብዓት የእርሻ መሣሪያዎች ናቸው። ይህንንም በሚመለከት አጥላው ሲናገሩ ከውጭ ከምናስገባው የእርሻ ግብዓት ውስጥ አብዛኛውን በአገር ውስጥ በማምረት የገቢ ንግዱን መቀነስ እንዲቻል ማድረግ ነው የተሻለው አማራጭ ይላሉ። ‹‹ከ40 ዓመታት በፊት ማምረት ጀምረን የነበረው የትራክተር ማምረቻ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ሲገባው አልሆነም። ይህ ደግሞ ትክክለኛ የመንግሥትን አስተዳደራዊ ክህሎት የሚጠይቅ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በኹለተኛ ደረጃ ያስቀመጡት ደግሞ የእርሻ መሬቱን ምርታማነት መጨመር ሲሆን በዚህ ረገድ ደግሞ የመሬቱን ለምነት በጠበቀ መልኩ የሚዘሩ አዝዕርቶችን እና ጠቃሚ ማዳበሪያዎችን በመጠቀም ለምርታማነቱ መትጋት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ መጠንከርና ለግብርናው ዘርፍ ግብዓቶችን በማምረት ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ያስረዳሉ። ከዚህም ባለፈ በተለይ ከውጪ የሚገቡ እንደ ማጭድ እና ሌሎች የመሣሪያ ግብዓቶችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን ማትረፍ ይቻላል ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት በወረርሽኙ የተከሰተውን ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴ በተመለከተ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ምን ማድረግ ይኖርበታል? ለሚለው ጥያቄ አጥላው ምላሻቸውን ሲያስቀምጡ፣ ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ በርካታ የምግብ አይነቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን በዋናነትም በከተሞች የሚገኘው ነዋሪ እንደሚመገባቸው ያስቀምጣሉ። ‹‹የገባው እስኪያልቅ ነው እንጂ ከውጭ ያስገባነው የምግብ ዓይነት ሲያልቅ ከባድ ቀውስ ውስጥ አንገባለን። ከስንፍና የመጣ እና ምርቶችን ለአምራቹ ካለማቅረብ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ለሚፈጠረው ችግር ተያያዥ ምክንያቶች ናቸው›› ሲሉ ምሁሩ ይናገራሉ።

‹‹ለምሳሌ የታሸጉ ምግቦች እና ጭማቂዎችን እዚሁ በአገራችን ምርቶች እና ፍራፍሬዎች በማምረት ለገበያ ማቅረብ እየተቻለ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ ማስገባታችን ፋይዳው አይታየኝም። አንሠራም ወይም አምርተን አንሸጥም፤ ብቻ ከዓለም ባንክ ያገኘናትን ውጭ ምንዛሬ በአገር ውስጥ በሚተኩ ምርቶች እናጠፋው እና ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳረጋለን።›› አያይዘው ያሉት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የግብርና ምጣኔ ሀብት ምሁሩ ጫንያለው (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ሲሰጡ፣ በአጠቃላይ ግብርና የሚለውን ጉዳይ ለይተን እና ከፋፍለን ማየት ይኖርብናል ሲሉ ይጀምራሉ። እርሻ ማለት አንደኛው ግብርና ክፍል እንጂ በዋናነት ግብርና ማለት እርሻ ብቻ አይደለም በማለትም ያስረዳሉ። ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በሚገባ የግብርና ምርት እንዲሁም በግብርና ግብዓቶች ጋር በተያያዘ ግን በመጀመሪያ ደረጃ ማዳበሪያ፣ የእርሻ ማሽኖች፣ ምርጥ ዘር እና ሌሎችን በተመለከተ ይህን ያህል ከባድ ጉዳት በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ይደርሳል ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ።

ደምሴ አያይዘውም ‹‹እነዚህ ኹሉ ግብዓቶች በዛሬው የኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያላቸው ጠቀሜታ እጅግ አናሳ ነው። ምክንያቱም ደግሞ ከአጠቃላይ አርሶ አደር ማዳበሪያ ተጠቅሞ የሚያመርተው ከ30 በመቶ አይበልጥም። እንደገና ምርጥ ዘር ተጠቅሞ ምርታማነቱን ለመጨመር የሚተጋውም ከ10 እስከ 12 በመቶ ብቻ ነው። ሌላው እና አመዛኙ አርሶ አደር ግን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በሚገባ ግብዓት ቀጥተኛ ተሳትፎ ኖሮት ምርቱን የሚያከናውን አይደለም። ስለዚህ በወረርሽኙ በቀጥታ ግብርና ዘርፉ ጉዳት ይደርስበታል ማለት አይደለም። ነገር ግን ሰፋፊ እርሻዎችን እያረሱ የሚገኙ ግለሰቦች ላይ በዚህ ጉዳት ይደርሳል›› ይላሉ።

እንደ መፍትሔ ሐሳባቸውን ሲያካፍሉም፣ በቅርቡ በተለይም በቆላ አካባቢዎች እየተተገበረ የሚገኘው ስንዴን የማምረት ሂደት ስኬት እያሳየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል። ምክንያቱም ደግሞ በየዓመቱ ለስንዴ ግዢ የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማስቀረት ይቻላል። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜም ተጠቂነታችን እምብዛም አይሆንም ማለት ነው በማለት ይደመድማሉ።

አምራች ዘርፍ
በኢትዮጵያ ውስጥ በአምራቹ ዘርፍ ያለውን መነሳሳት እና ማቆጥቆጥ በተገቢው መንገድ እንዲሄድ ሊደረግ እና ከመንግሥትም ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ በርካቶች ይስማሙበታል። ይህም ማለት ለግብርናው የጀርባ አጥንት እንዲሆን እና ደጀንነቱን እንዲያረጋግጥ የአምራቹ ዘርፍ መጠናከር አይነተኛ ዘዴ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ። ‹‹በአገር ውስጥ ያሉትን የብረታ ብረት ማምረቻዎች አቅም በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሰፊ በማስቀረት እና ለሌሎች ዘርፎችም ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በዚሁ በአገር ውስጥ በማምረት ተመጋጋቢነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል›› ሲሉ ያብራራሉ፣ አጥላው።

በተለይም ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ከአቅም በታች የሚያመርቱትን ብረታ ብረት ፋብሪካዎች መንግሥት ድጋፍ በማድረግ እና ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ በማድረግ የአገር ውስጥ ፍጆታን በአገር ውስጥ ምርት በመሸፈን የንግድ አለመጣጣሙን ማስታገስ እንደሚችል ያስረግጣሉ።
በተመሳሳይም የምጣኔ ሀብቱ ምሁር አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም በገቢ ምርት ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት በተወሰነ መልኩ በማርገብ በአገር ውስጥ ምርት ፎጆታን ማርካት እንደሚገባ ያስቀምጣሉ። ‹‹እስከ አሁን የነበረው ፖሊሲ የወጪ ንግድን ማበረታታ ላይ ያተኮረ ነበር ማለት ይቻላል። የወጪውን ንግድ ማበረታታ እንዳለ ሆኖ ከውጪ የሚገቡ እቃዎችን በአገር ውስጥ የማምረት ስትራቴጂ ቢወጠን ጥሩ ነው። የቱን ምርት፣ የቱን ዘርፍ የሚለውን በሰፊ ማጥናት ያስፈልጋል›› ሲሉም አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

አምራች ዘርፉን ለመደገፍ በተለይም ደግሞ በዚህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብኣቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ እና ለተቀረው አምራች ዘርፍ በጠቅላላ ለመደገፍ በሚል መንግሥት የመቶ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ይህም ከዚህ ቀደም ከውጭ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገቡ የነበሩ እቃዎችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እየተደረገ እንደሆነም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስትር መላኩ አለበል አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የተመደበው ድጋፍ ለአምራች ዘርፉ ግብዓት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ማስገቢያ ሲሆን ይህም ደግሞ በአገር ውስጥ ጥሬ እቃው መኖሩ እየታወቀ ነገር ግን ጥራቱን ባለማስጠበቅ የተነሳ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ እንደሆነ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በቀጣይ በተለይም በሚመጡት ዓመታት በአገር ውስጥ ያሉ እንደ የድንጋይ ከሰል፣ ብረት እና የመሳሰሉትን በአገር ውስጥ በማምረት ለአምራቹ ዘርፍ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማስቀረት እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል።

የገቢ ምርት ከአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ደግሞ ከአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርት 6 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው የሚታወቅ ነው። በዚህም ረገድ ኮቪድ 19 ከዚህ በፊት በመንግሥት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ ዘርፎች እና ማሻሻያና ለውጥ የሚፈልጉ ፖሊሲዎችን መንግሥት ዞር ብሎ እንዲያስተውል እና ወደ ውስጥ እንዲመለከት እንዳደረገው ለማወቅ ተችሏል።
ሌላው እና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባው የምግብ ዘይት ሲሆን ይህን በሚመለከት በአንድ ቢበዛ በኹለት ወራት ውስጥ በአገር ውስጥ ምርት ዘጠኝ በመቶ ብቻ ይሸፈን የነበረውን ፍጆታ እስከ 80 በመቶ ከፍ ለማድረግ መንግሥት እንደሚሠራም መላኩ አስታውቀዋል። በዚህ ሦስት ከፍተኛ ምርት የሚያመርቱ የዘይት ፋብሪካዎች ወደ ሥራ የሚገቡ ሲሆን፣ በቀጣዩ በጀት ዓመት 2013 ሙሉ በሙሉ የዘይት ምርት በአገር ውስጥ የሚሸፈን እንደሚሆን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ 400 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዘይት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ንግድ እና ኢንዱስትሪ በ2011 በጀት ዓመት ያስጠናው ጥናት ያመላክታል።

የሥራ እድል ፈጠራ
ከምጣኔ ሀብቱ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የሠራተኛ ቅነሳ መደረጉ ወይም ሊደረግ እንደሚችል ይተነበያል። በተለይም ደግሞ በኢፌዴሪ የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤፍሬም ተክሌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በሦስት ወራት ውስጥ የወረርሽኙ የሚያሳየው ስርጭት ከጨመረ በንግድ እና በሌሎች ሴክተሮች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ እስከ ኹለት ሚሊዮን ሰዎች ከሥራቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ይህን በሚመለከት አጥላው እንደሚሉት፣ መንግሥት በዋናነት ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል አቅፈው የያዙትን ሴክተሮች በመደገፍ እና ሠራተኞቻቸውን ሳይበትኑ መቀጠል የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

በዚህ ብቻ ሳይበቃ በዘላቂነት እና በቋሚነት የሚኖረውን የዜጎችን የሥራ ደኅንነት ለማረጋገጥ የመንግሥት ሰፊ ጥናት እና ዳሰሳ ያስፈልገዋል ሲሉ ይናገራሉ። ገንዘቡን በተወሰኑ ሰዎች እጅ ውስጥ መሆኑ ለሥራ እድል ፈጠራው ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆን አጥላው ጨምረው ገልጸዋል። ስለዚህ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ የሚዘዋወረው ገንዘብ በብዙኀኑ ዘንድ ደርሶ ራሱን ደግፎ በዘላቂነት የሥራ ወይም የኑሮ ስጋት ሳይደርስበት መኖር የሚያስችል ፖሊሲ በመንግሥት በኩል መቀረጽ እንደሚኖርበት አስረግጠዋል።

በተመሳሳይም አብዱልመናን ሐሳባቸውን ሲገልጹ ከሚኖረው የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ የሥራ አጥ ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችል ያስረዳሉ። ‹‹የኢኮኖሚ በጣም መቀዛቀዝ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር እና የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ብዛት ሊጨምር ይችላል›› ይላሉ።

ከዚህ ኹሉ በኋላ ኢትዮጵያ እንደ አገር ምን ትማራለች ለሚለው ጥያቄም አብዱልመናን ሲመልሱ ‹‹እንዲህ አይነት ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ መንግሥት ትልቅ ሚና መጫወት አለበት። የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ፕላን በማውጣት ኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ የሚቻልበት ስትራቴጂ መንደፍ አለበት። ሰፊ የሆነ ግምገማ በማካሄድ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ቀውስ እንደዚሁም በጣም ሊጎዱ የሚችሉ የኢኮኖሚ ሴክተሮችና የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የሚረዱበትን ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል። መንግሽት የነገሮችን ተለዋዋጭነት ከግንዛቤ በማስገባት የተጀመሩ የኢኮኖሚ መደገፊያ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እና ወቅታዊ ምላሽ መስጠት አለበት።›› ሲሉ ይደመድማሉ።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ በቅርቡ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን ጉዳት በሦስት ከፋፍለው ያስቀምጡታል። በዚህም መሰረት ወረርሽኙ ከሐምሌ 2012 እስከ መስከረም 2014 የሚዘልቅ ከሆነ ምጣኔ ሀብቱ እምብዛም ሳይጎዳ ወደ ነበረበት ለመመለስ ይህን ያህል እንደማይቸገር አስቀምጠዋል። ቀጣይ ከጥቅምት እስከ ታኅሳስ ከቆየ መለስተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል እና ከዛም ከፍ ካለ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚመዘገብ በጽሑፋቸው ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም ዓለማየሁ ሲያስረዱ፣ ኮቪድ 19 በአጠቃላይ የአገር ውስጥ የምርት ዕድገት ላይ በ11 ነጥብ 1 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ይተነብያሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአምራች ዘርፉ ውስጥ እስከ 17 በመቶ የሚሆን ከፍተኛ መቀዛቀዝ ሊያሳይ እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ከዛም በመቀጠል በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍም ቀላል የማይባል እና 15 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ የሚችልበት አዝማሚያ መኖሩንም አስቀምጠዋል።
ዓለማየሁ አያይዘውም ከሴክተሮች ውስጥ እምብዛም ጉዳት የማይደርስበት የግብርናው ዘርፍ መሆኑን ተናግረው፣ ነገር ግን የ1 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የወጪ ንግዱንም በሚመለከት ዓለማየሁ በጽሑፋቸው ሲገልጹ የምጣኔ ሀብቱ አለመረጋጋት በቀጣዩ ዓመት ታኅሳስ ድረስ ካበቃ እስከ 16 በመቶ የሚሆን መቀዛቀዝ ሊያሳይ እንደሚችልና ከዛ በላይ ከቆየ ግን ሊከፋ እንደሚችል አበባ እና ፍራፍሬ እንዲሁም የቆዳ ወጪ ንግድን ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ። ይህም ደግሞ ከፍ ሲል ወይም በጣም በተዳከመው የምጣኔ ሀብት ወቅት የወጪ ንግድ ቅናሽ ሊያሳይ የሚችልበት እስከ 24 በመቶ እንደሚደርስም ይታሰባል።
በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ የሚደረገው የገቢ ምርትም እስከ 21 በመቶ መቀነስ ሊያጋጥመው እንደሚችል ይተነበያል። ስድስት በመቶ የሚሆን ቅናሽ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ምጣኔ ሀብቱ መሻሻል ካሳየ የሚያጋጥም ቅናሽ ሲሆን፣ ከፍ ብሎ እስከ ታህሳስ ከሄደ 16 በመቶ ቅናሹ ሊሆን ይቻላል ማለት ነው። ከዛ ከዘለለ 21 በመቶ የገቢ ንግድ ይቀንሳል ሲሉ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here