ልጅን ለብቻ ማሳደግ በዘመነ ኮሮና

0
648

ይህን ዘገባ ኒዮርክ ታይምስ አስነበበው። ስለ 35 ዓመቷ ሾሻና ቼርሶን እና የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስላደረሰባት ጫና ነው። ሾሻና ባለቤቷ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 መጀመሪያ አካባቢ ሕይወቱ አልፏል። ያኔ ልጇ ገና አንድ ዓመቷን መያዟ ነበር። ኑሮ ቀላል አልሆነላትም። ይሁንና ዓመት ሲያልፍ እርሷና አንድ ዓመት የሞላት ልጇ ነገሮችን ተላመዱ። በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ሥራ አግኝታ፣ በሥራ ቀን ልጇን ልጆች ማቆያ፣ በእረፍት ቀን ደግሞ ከጓደኞቿ ልጆች ጋር እንድትጫወት ጓደኞቿ ጋር ታቆያታለች።

በባሏ ሞት ምክንያት በአዲስ አኳኋን የጀመሩት ኑሮ ግን በወረርሽኙ ምክንያት ዳግም ተቃወሰ። ምግብ ቤቱ ተዘጋ፣ የልጆች ማቆያውም እንደዛው። ከጓደኖቿ ልጆች ጋር የእርሷን ልጅ መተውም የሚሆን አይደለም። ሾሻና የገነባቸው አዲስ የኑሮ መንገድ ፈረሰባት። ከባለቤቷ የሕይወት ኢንሹራንስ ያገኘችው ገንዘብ በተወሰነ ጊዜ የሚያልቅ ነው። ‹‹እንኳንና አካላዊና ማኅበራዊ ፈቀቅታ ኖሮ፣ ለብቻ ልጅን ማሳደግ ራሱ ብቸኝነት ስሜት ይፈጥራል›› ስትል በሐዘን ስሜት ተናግራለች።

በቫይረሱ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ ወይ ከእናት አልያም ከአባት ጋር ብቻ የሚኖሩት ሕጻናት ቁጥር ከጠቅላላው ሕጻናት ውስጥ አንድ አራተኛ ናቸው። ይህም በዓለም ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ልጆችን ለብቻ ከሚያሳድጉት ውስጥ ሴቶች የሚበዙ ሆነው፣ ከ425 ሺሕ በላይ ሕጻናትም በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ግዛት ብቻ በአንድ ወላጅ ብቻ የሚያድጉ ናቸው። እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ገለጻ፣ ቀድሞም ጫንቃቸው ብዙ ለተሸከመ ልጆቻቸውን ለብቻ ለሚሳድጉ እናቶች፣ ይህ የበለጠ ከባድ ጫና ያሳድራል።

ይህ የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ አሜሪካን ማእከል ያደረገ ነው። በአገራችን በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ስናይ፣ መለስ ብለን በ2007 የተደረገን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ግኝት እናስታውስ። በዛ ግኝት መሠረት ኹለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት እናታቸው ለብቻ የምታሳድጋው ሲሆኑ፣ 600 ሺሕ የሚሆኑ ደግሞ በአባት ብቻ ያድጋሉ። በዚህ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጊዜ ይህ ምን ያህል በወላጆችና በልጆች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር መገመት ቀላል ነው።
ይህም ለብቻ ልጃቸውን/ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች በብዛት ከመኖራቸው አንጻር ጠቀስን እንጂ፣ ቤተሰብን የሚያስተዳድሩ የነበሩ አባቶች ሥራ ከማጣታቸው ጋር በተገናኘ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየቤቱ የሚፈጠረው ቀውስ በቀላል የሚፈታ አይደለም።

ወደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ እንመለስ፣ ዘገባው ማሪና አሻዴ የተባሉ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል አባልን ይጠቅሳል። እኚህ ሴት በማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን የሴቶች ድረሻን አጥንተዋል። እንዲህ ኢኮኖሚ በሚደቅበት ጊዜ ከወንዶች በተሸለ ሥራቸው ላይ የሚገኙት ሴቶች ናቸው ይላል፤ የገቢው መጠን አነሰም በዛ። ይህም የሆነው የሚሠሩበት ስፍራ አገልግሎት ሰጪ በመሀኑ ነው።

አሁን ግን ያው ሁኔታ ተቀይሯል። አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከሥራ ውጪ ሆነዋል። ወንዶች በብዛት የተሰማሩባቸው ግን በአንጻሩ ሥራቸውን ቀጥለዋል። እናም በአሜሪካ ኒውዮርክ ግዛት ብቻ እንኳ በሥራ አጥነት ከተመዘገቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አሜሪካውያን ውስጥ ከግማሽ በላይ ሴቶች ናቸው። ታድያ ማሪና ለኒውዮርክ ታይምስ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፤ ‹‹ዝቅተኛ ደሞዝ ያለውና በርካታ ሴቶችን ቀጥሮ የነበሩ የሥራ መስኮች እየተዘጉ ነው። በሥራዎቹ ላይ የነበሩ ሴቶች ከሥራ ስለተቀነሱበት ካሳም ሆነ ኢንሹራንስ አያገኙም። እውነት ለመናገር ለብቻቸው ልጆቻውን ከሚያሳድጉ ሴቶች መካከል ምን ያህሉ ቤት ውስጥ ሆነውም መሥራት የሚችሉት ሥራ እንዳላቸው አላውቅም!››
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here