ኮቪድ 19 በምጣኔ ሀብት ላይ ያለው ተፅዕኖና መዉጫ መንገድ

0
615

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካመሳቀላቸው የሰው ልጅ ምድራዊ ስርዓቶች መካከል ቫይረሱ በማኅበራዊ ሕይወት የሚፈጥረውና የፈጠረው ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ አንዱና ተጠቃሹ ነው። ይህም በአንድ ጀንበር የሚገለጥ ሳይሆን እያደር የሚታይ ሲሆን፣ ከምጣኔ ሀብት ድቀት ጋርም ዝምድናው የጠነከረ ነው። በተለይም የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚደረጉ ከቤት ያለመውጣትና የእንቅስቃሴ ገደብ መመሪያዎች የብዙዎችን ሕይወት እንዳልነበር አድርገዋል።

አብርሐም ፀሐዬ ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግ በኡጋንዳ ካምፓላ የአንዲትን በወሲብ ንግድ የምትተዳደር ሴት ሕይወት በማሳያነት ያስቃኛሉ። እንዲህ ባለ ቀድሞም በተገለለ ሥራ እንዲሁም ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ ወረርሽኙ በተለየ የሚያደርሰውን ተጽእኖም ያስረዳሉ።

መተኪያ የሌለውን የሰው ልጅ ሕይወት ከመቅጠፍና ከፍተኛ ማኅበራዊ ምስቅልቅል ከማስከተሉም በላይ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ የዓለምን ምጣኔ ሀብት ወደ አዘቅት ውስጥ እየከተተው ይገኛል። እያስከተለ ያለው እና ወደ ፊት ከሚያስከትለው ማኅበራዊ ችግሮች አንፃር ወረርሽኙ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር የሚስተካከል እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶችና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሌላ በኩል ወረርሽኙ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከዐስር ዓመት በፊት ዓለምን ካቃወሰው የፋይናንስ ውጥንቅጥ (financial crisis) እና ተከተሎት ከመጣው የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ (recession) ቀስ በቀስ እያደገ በመምጣት በ1920ቹ ዓለም ገብታበት ከነበረው ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ውድመት (great depression) ጋር እየተስተካከለ ነው።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በተወሰዱ እርምጃዎች ምከንያት ዓለማቀፉ የገንዘብና መዋዕለ ነዋይ ዝውውሮች ተቋርጠዋል። የንግድ ትስስሮች ተበጣጥሰዋል የቱሪስቶች ዝውውር ተገቷል። የተባበሩት መንግሥትታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ እንዳሳወቀው ከግዙፎቹና በብዙ አገራት ከሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት (multilateral companies) መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት የሥራ መቀዛቀዝ ገጥሟቸዋል።

በተጨማሪም አምስት ሺሕ በብዙ አገራት የሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት ገቢ እስከ 2020 መጨረሻ በአማካይ በ30 በመቶ እንደሚቀንስ ተገምቷል። በዚህም የተነሳ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት በዓለም ላይ በ40 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል።

የዓለም ንግድ ድርጅት እንዳሳወቀው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዓለም ዐቀፍ ንግድ እስከ አሁን በ50 ቢሊየን ዶላር ቀንሷል። እስከ 2020 መጨረሻ ድረስ ዓለም ዐቀፍ ንግድ በ32 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል። በቅርቡ የዓለም ጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት እንደገለፀው፣ የቱሪስቶችና የተጓዦች እንቅስቃሴ በአብዛኛው ሰለሚገታ ዓለም ዐቀፍ የበረራ ዘርፉ እስከ 2.1 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ሊያጋጥመው ይችላል። ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዓለም የገንዘብ ተቋም በዚህ ዓመት ይመዘገባል ብሎ የገመተውን የእድገት መጠን ከ2.9 በመቶ ወደ 1.5 በመቆ ዝቅ አድርጐታል።
ወደ አፍሪካ ስንመጣም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። እንደ ናይጄሪያ አልጄሪያ እና አንጎላ ያሉ አገሮች ከነዳጅ ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ለጠቅላላው ዓመታዊ የውጭ ንግድ ገቢያቸው ከ90 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ አለው። ነገር ግን እነዚህ የነዳጅ ላኪ አፍረካ አገሮች አሁን ከተከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት መቃወስ ገጥሟቸዋል።

እንደ ቻይና ካሉ በወረርሽኙ በጣም የተጎዱ አገሮች ጋር የጠበቀ የንግድ ትስስር ያላቸው የአፍሪካ አገሮች በዓለም ገበያ ላይ በሚስተዋለው የግብርና እና ኢንዱስትሪ ውጤቶች ፍላጎት መቀነስ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዱ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ አንድ ሦስተኛው ዓመታዊ የውጭ ንግድ ገቢ የምታገኘው ቻይና ከሚላኩ እቃዎች ነው።

ሌሎች በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ የምጣኔ ሀብት ያላቸው እንደ ሲሸልስ ኬፕቨርዲ ሞሮኮ ሞርሸስ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። በቱሪዝም እና በበረራው ዘርፍ መቀዛቀዝ ኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ ሆናለች። በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳሳወቀው እስከ አሁን 190 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶበታል። በመሆኑም የዓለም የገንዘብ ተቋም በዚህ ዓመት በአፍሪካ ይመዘገባል ተብሎ የነበረውን 3.2 በመቶ እድገት ወደ 1.8 በመቶ ዝቅ አድርጐታል።

እንደዚህ አይነት የጠቅላላ አገራዊ ምርት (gross national product) እድገት መቀነስ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሲቆይ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ተፈጠረ ይባላል። በዚህ ጊዜ በተለይም ትናንሽ የንግድ ተቋማትና አምራቾች ሥራ ከማቆም በዘለለ ሠራተኞቻቸውን ለመበተን ይገደዳሉ። ይህም በአሁን ሰዓት ባደጉት አገሮች እንኳን ሳይቀር በስፋት ይስተዋላል።

ለምሳሌ በአሜሪካን 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ስዎች ሥራ አጥ ሆነዋል። እስከ 2020 መጨረሻ ይህ ቁጥር እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል። የዓለም የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ባወጣው ግምት መሰረት በአውሮፓ 50 ሚሊዮን በአፍሪካ ደግሞ 20 ሚሊዮን ሰዎች እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ሥራቸውን እንደሚያጡ ይጠበቃል። ከዚህም በዘለለ ወረርሽኙ ለተወሰኑ ወራት እንኳን በዚሁ ፍጥነት ከከቀጠለ 3.3 ቢሊዮን ከሚሆነው በዓለም ላይ ካለው የሥራ ቦታ ውሰጥ 81 በመቶ የሚሆነው አደጋ ውሰጥ እንደሚገኝ ድርጅቱ ያስረዳል። ይህ የሚያሳየው የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዙ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችልና ወደ የምጣኔ ሀብት ውድመት ሊሸጋገር እንደሚችል ነው።

ይህን ሊከሰት የሚችል የምጣኔ ሀብት ቀውስ ለመግታት የበለፀጉ አገሮች ከፍተኛ የሆነ በጀት ከአሁኑ እየመደቡ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ 2.2 ትሪሊዮን ዶላር ስትመድብ የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ አንድ ትሪሊዮን ዩሮ እንዳዘጋጀ ተናግሯል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሃ አገራት ግን የሚመጣውን አስከፊ አደጋ በባዶ እጅ ከመጋፈጥ ውጪ አማራጭ ያላቸው አይመስሉም።

ኢትዮጵያ ላለፉት ኻያ ዓመታት የተከተለችው የእድገት ጎዳና አይደለም ከእንደዚህ አይነት አደጋ ሕዝብን መታደግ ቀርቶ በደኅናውም ጊዜ እንኳን በቅጡ መሥራት አልቻለም። ይህን ለመገንዘብ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት እድገትና የተለያዩ ዘርፎችን አወቃቀር ማየት ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ነባራዊ ሁኔታና አወቃቀር
ባለፉቱ ኹለት ዐስርተ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎች ግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ ተመርኩዞ የመጨረሻ ግቡን ዓለም ዐቀፉ ንግድ እና ገበያን ያደረገ የእድገት አቅጣጫን (outward looking export based strategy) በመከተል ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሀብት እመርታ ለማስመዝገብ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በወፍ በረር ውጤቱን ስናየው አመርቂ ይመስላል። ባለፈው ዐስር ዓመት ኢትዮጵያ የኹለት አሃዝ ጠቅላላ አገራዊ ምርት እድገት አስመዝግባለች። ካለፉት ኹለት ዓመታት ጀምሮ በትንሹ ማሽቆልቆል ቢያሳይም፣ እድገቱ ኢትዮጵያን ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት እመርታ ካስመዘገቡ ጥቂት የዓለም አገራት ተርታ አሰልፏታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉቱ ኹለት ዐስርተ ዓመታት የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት አወቃቀር ይህ ነው የሚባል ሽግግር ሳያስመዘግብ ቆይቷል። እስከ አሁን ድረስ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በግብርና ይተዳደራል። ለጠቅላላው ዓመታዊ ምርት ያለው አስተዋፅኦ እየቀነሰ ቢመጣም፣ ምርትና ምርታማነት በግብርናው ዘርፍ በትንሹ ብቻ ነው ለማደግ የቻሉት።

ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለዓለም ገበያ የሚሆኑ የግብርና ውጤቶች እንዲያመርት ቢጠበቅም ዘርፉ ግን ይህን ሊያሳካ አልቻለም። ጥቂት ሰፋፊ እርሻዎች እዚህ ግባ የማይባል ምርት ያመርታሉ። ይባስ ብሎ አገሪቱ እንደ ስንዴ ያሉ መሰረታዊ አዘርቶች ከውጭ ቢሊዮኖችን በማውጣት ለማስገባት ተገዳለች።
ወደ ኢንዱስትሪው ስንገባ ከግንባታው ንዑስ ዘርፍ በስተቀር የጎላ እድገት አይስተዋልም። የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ የተዋቀረው በዋነኝነት የዓለም ገበያን ታሳቢ አድርጎ ነው። ይህንን ለማሳካት የኢንዱስትሪው ፖርኮችን ከመገንባት ጨምሮ በቢሊዮኖች የሚገመት ድጋፍ (incentives) በተለይም ለውጭ ባለሀብቶች ተሰጥቷል። ነገር ግን ልክ ከሃምሳ ዓመት በፊት እንደነበረው የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ለዓመታዊ ጠቅላላ የአገር ምርት ያለው አስተዋፅኦ ከአምስት በመቶ አልዘለለም።

በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክ ከፍተኛ እመርታ ለማምጣት ቢሞከርም ዘርፉ ከጠቅላላ ዓመታዊ የውጭ ንግድ ገቢ ያለው ድርሻም 10 በመቶ ለመዝለል አልቻለም። ይባስ ብሎ ከሃምሳ ዓመት በፊት ትላልቅ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የነበራት ኢትዮጵያ እንደ አሁን ያለ የጭንቅ ጊዜ ሲመጣ የጥራት መለኪያዎች የሚያሟሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች መታጣታቸው የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርም ጉዳይ ነው።
በተቃራኒው የተሻለ እድገትና መዋቅራዊ ሽግግር ያሳየው የአገልግሎት ዘርፍ ነው። ለዓመታዊ ጠቅላላ የአገር ምርት ያለው አስተዋፅኦ በዐስር ዓመት ውሰጥ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። እንደ ፋይናንስና የአገር ውሰጥ ንግድ ያሉ ንዑስ ዘርፎች ባለፈው ኻያ ዓመት አበረታች እመርታ አስመዝግበዋል። ይሁን እንጂ እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ የአገልግሎት ዘርፍም ለምጣኔ ሀብት መዋዠቅ ተጋላጭ ከመሆን አላመለጠም።

አይደለም ከባድ ዓለም ዐቀፉዊ አደጋን ይዞ ለሚመጣ እንደ ኮቪድ 19 ዓይነት ወረርሽኝ፣ በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በቀላሉ ሲሽመደመድ በተደጋጋሚ አይተናል። ስለዚህም ፖሊሲ አውጪወች አማራጭ አቅጣጫዎችን በማመንጨት መተግበር ይገባቸዋል።

እዚህ ላይ በጥልቀት ልንገነዘበው የሚገባው ነገር አማራጭ የእድገት አቅጣጫዎች ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በኮቪድ 19 ምክንያት አይደለም። ወረርሽኙ አስተሳሰባችንን እንድንፈትሽ እድል ብቻ ነው የሚሰጠን። ዋነኛው ምክንያት አሁን እየተከተልን ያለው የእድገት አቅጣጫ ለኻያ ዓመት ተሞክሮ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት ስላልቻለ ነው።

አማራጭ አቅጣጫ
እንደአለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ከተቀረው ዓለም እንደወረደ በመኮረጅ ለዓመታት ለውጥ ለማምጣት ስትባዝን ኖራለች። ከኅብረተሰባዊ ርዕዮት ዓለም ጀምሮ እስከ ገበያ መርና ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰቦች ድረስ ከውጭ በማምጣት ለመተግበር ተሞክሯል። ውጤት አላመጡም እንጂ። ለዚህ ምክንያት እነዚህ አስተሳሰቦች ስለማይሠሩ አይደለም። የተለያዩ አገሮች እነዚህን አስተሳሰቦች ተጠቅመው ሕዝባቸውን ከድህነት አላቀዋል።

ለምሳሌ የምእራብ አገሮች የገበያ መር አስተሳሰብ አመንጭተው በአግባቡ ስለተገበሩት ውጤታማ ሆነዋል። እንደ ደቡብ ኮርያ ያሉ የእስያ አገራት ደግሞ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብን ተንተርሰው ብልፅግናን አሳክተዋል። እነዚህ ውጤታማ አገሮች የተለያዩ አስተሳሰቦችን እንዳለ ሙሉ ለሙሉ ከመተግበር ይልቅ እንደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በማሻሻልና በመቀየር ወደ ከፍታ ተጠግተዋል።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆነው የኛ አገር ፖለቲከኞችም ጭምር የሚያሞኳሿት ቻይና ናት። ባለፈው ሠላሳ ዓመት ቻይና እንደ እዝ እና የገበያ መር ኢኮኖሚ ያሉ የተለያዩ የእድገት አስተሳሰቦችን አዋህዳ በመቀመርና ከሕዝቦቿ እውቀት አስተሳሰብ አኗኗር እና ፍልስፍና ጋር በማዛመድ የራሷ የሆነ አቅጣጫ አፍልቃ በመተግበር ከድህነት ለመላቀቅ ችላለች። የአገር ውሰጥ እውቀቶችን ከመጠቀም ባሻገር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን (experiments) ማእከል ያደረገ ትግበራ በመከተል ቻይና በአጭር ጊዜ ውሰጥ በምጣኔ ሀብት የዓለማችን ኹለተኛ ጠንካራ አገር ለመሆን በቅታለች።

ይህን ለማሳካት በአንድ ጊዜ ብዙ ማሻሻያዎችን ከማድረግ እና በሯን በአንድ ጊዜ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ከማድረግ ይልቅ ቀስ በቀስ ውጤታማነታቸው በማየት መተግበር በመቻሏ ነው። የቻይና ተሞክሮ የሚያሳየው የተለዩ የእድገት አስተሳሰቦች እንደወረዱ ከመተግበር ይልቅ እነሱን ከአገራዊ እውቀት፣ አስተሳሰብ፣ አኗኗር እና ፍልስፍናን ጋር ማጣመር ለስኬት እንደሚያበቃ ነው።

ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ውሰጥ የሚመለከት የእድገት አቅጣጫ (inward looking growth strategy) መከተል ይኖርባታል። ወደ ውሰጥ የሚመለከት አቅጣጫ መከተል ማለት መሉ ለሙሉ ከዓለም የመገለል አካሄድ ሳይሆን እስከሚቻል ድረስ አገሪቱን በሌሎች ኃያላን ላይ ያላትን የጥገኝነትን መጠን በሚቀንስና በራስ አቅምና ጉልበት ላይ መሰረት ያደረገ የእድገት ጎዳና መከተል ማለት ነው። ይህ አይነት አቅጣጫ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በሚኖርበት ጊዜ ፍቱን መድኃኒት ከመሆኑም ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሃ አገራት ከሚዳክሩበት የውጭ ምንዛሬ ችግር መፍተሔ ስለሆነም ጭምር ነው።

ወደ ውሰጥ የሚመለከት የእድገት አቅጣጫን ከአገራዊ እውቀቶች ጋር ሰፍቶ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በአጭር ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በመጀመሪያ የዘርፉን አደረጃጀት መቃኘት ይጠይቃል። በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ በዋናነት ትናንሽ መሬትን በሚያርሱ ገበሬዎች አማካኝነት የሚመራ ነው። በአንድ በኩል እነዚህ ገበሬዎች ባለፋት ሺሕ ዓመታት ከነበረው የአስተራረስ ዘዴ ያልተላቀቁ እንደ ሞፈርና ቀንበር እንዲሁም በበሬ የሚያርሱ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን እንደ ማዳበሪያ ምርጥ ዘርና የተባይ መከላከያ ኬሚካሎች እንደ ግብአት የሚጠቀሙ ናቸው።

የአፈር ለምነትን ለማጎልበት እና የአፈር መሸርሸርን ለማስቀረት የሚረዱ አገር በቀል እውቀቶችን አጎልብቶ ከመጠቀም ይልቅ ቢሊዮኖችን በማውጣት ከውጭ ስንገዛ፣ ከውጭ በሚመጣ እውቀት መታገዝ የሚገባው ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴያችን ግን ባለበት እንዲረግጥ ተፈርዶበታል። እንደዚህ ያሉ የተጣረሱ አሰራሮችን ለማስተካከል ለአገር በቀል እውቀቶች ቅድሚያ በመስጠትና በማጎልበት እንዲሁም በአገር ውሰጥ የሌሉትን እውቀቶች ከውጭ አምጥቶ በማስተሳሰር ላይ ትኩረት የሚሰጥ ወደ ውሰጥ የሚመለከት የእድገት አቅጣጫን መከተል ያሻል።

ሌላው ደግሞ ትናንሽ መሬትን ለሚያርሱ ገበሬዎች ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ የሆኑትን ወደ ሰፋፊ መሬት አልሚነት መቀየር ነው። ይህ አካሄድ አሁን ከሚተገበረውና ለውጭ አገር አልሚዎች ቅድሚያ ከሚሰጠው አቅጣጫ መላቀቅንና ወደ ውስጥ መመልከትን ይጠይቃል።

ከግብርናው በበለጠ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከአገር ውሰጥ ባለሀብት ይልቅ ለውጭ ቅድሚያ መስጠትን ማእከል ባደረገ አስተሳሰብ የተዋቀረ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ዘርፉ ከአገር ውሰጥ ገበያ ይልቅ የዓለምን ገበያ ታሳቢ ያደረገ ነው።

ያደጉት የምእራብ እና የእስያ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከውጭ በመጣ መዋዕለ ነዋይም ሆነ ባለሀብት ብቻ የሚመጣ እድገት የለም። በተቃራኒው እነቻይና ተአምር የሚባል እድገት ያስመዘገቡት በራሳቸው የግል ዘርፍ በተመራ ንቁ ተሳትፎ ነው። ይህ ግን በራችንን ለውጭ ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ ዝግ ማድረግ አለብን ማለት አይደለም። የተመረጡና የእውቀት ሽግግር በሚያስፈልግበት ቦታዎች የውጭ ባለሀብቶችን ማሳተፍ አስፈላጊ ነወ። ነገር ግን መንግሥት የአገር ውሰጥ ባለሀብቶች በከፍተኛ ደረጃ ሊያግዝ ይገባል።

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርቶች ዋነኛ መዳረሻ የአገር ውሰጥ ገበያ መሆን ይኖርበታል። በተለይም ባለን እውቀት በብዛት ከውጭ የምናስገባቸውን የሚተኩ ምርቶችን በብዛት ማምረት (mass production) ላይ ሊተኮር ይገባል። ይህም ቀስ በቀስ የምርቶችን ጥራት በማሳደግ ወደ ዓለም ገበያ ወደፊት በቀላሉ ሰብሮ ለመግባት ያስችላል። ይህን ከመተግበር ጎን ለጎን በተነፃፃሪነት ብልጫ (relative advantage) የምንወስድባቸውን ምርቶች ለዓለም ገበያ ማቅረብ ይገባል።

በወረርሽኙ ለተጎዱ የንግድ ተቋማትና አምራቾች የአጭር ጊዜ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣት ከአሁን ጀምሮ መሥራት ይገባል። ምንም እንኳን ከባድ ቢመስልም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ቻይና ተሞክሮ የሚያሳየው በጥቂት ዐስርተ ዓመታት ይህንን ማሳካት እንደሚቻል ነው።

ሳምሶን ኃይሉ የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት የሆነችው ʻኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪውʼ ምክትል መራሔ አሰናጅ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው ebr.magazine1@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here