ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለማስመረቅ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ቅሬታ ቀረበ

0
529

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2012 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለማስመረቅ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ የተማሪዎችን ውጤታማነት ያላገናዘበ እና ትክክለኛ ውሳኔም አይደለም ሲሉ ተማሪዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በስልክ እንዳሳወቃቸው እና ከመጀመሪያ ዲግሪ መደበኛ ተማሪዎች ውጪ ትምህርቱ እንደሚቀጥል መረጃው እንደደረሳቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዩኒቨርሲቲው የማታ እና የኹለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አስታውቀዋል። የዩኒቨርሲቲው ዋናው ጊቢ የተማሪዎች ተወካይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ ትምህርቱ ለኹለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች እና ለማታ ተማሪዎች ነው የሚቀጥለው። ለመደበኛ እና ዘንድሮ ተመራቂ ለሆኑ ተማሪዎች ግን በድረ-ገፅ እንደሚያዘጋጁላቸው እና በዛም አማካኝነት እንዲያነቡ እንደተመቻቸላቸው እንደተነገራቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።

እንደ ተማሪዎች ተወካይዋ ገለጻ ከሆነ፣ ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠውን የመማር ማስተማር ማስኬጃ ምርጫዎች በማንሳት ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊሄድ የማይችል ብሎም ውጤታማነቱ ተጠንቶ ያልተወሰነ ውሳኔ ነው በማለት ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የ2012 የኹለተኛ ዲግሪ ተመራቂ የሆነው የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደገለፀው፣ ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ካለመሆኑም በላይ ውሳኔው እንደገና ሊጤን ይገባል። የመመረቂያ ጽሑፉን ቤት ውስጥ ለመጨረስ እንደሚከብድ እና የኹሉም ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ በአንድ ዓይነት መልኩ ሊሄድ የማይችል በመሆኑ ከባድ ውሳኔ ነው የሆነብንም ብሏል።

ከዛም በተጨማሪ ‹‹የሚቀርበውን የመመረቂያ ወረቀት በምን መስፈርት መዝነው ሊያሳልፉት እንደሚችሉ ግልፅ አይደለም። የተጣራ ሥራ ለማቅረብ ጊዜው አይፈቅድም።›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የማታና የርቀት ትምህርት የቅድመ-ምረቃና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች የኮቪድ-19ን ስርጭት ከመከላከል ጎን ለጎን የማታ ሥራዎች መቀጠላቸውን መግለፁ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበላይ አመራር ከኮሌጆች ዲኖች እና ከኢንስቲትዩቶች ዳይሬክተሮች ጋር በሚያዚያ 14/2012 ባደረገው የቪዲዮ ኮንፈረንስ የኮቪድ-19ን ስርጭት ከመከላከል ጎን ለጎን የመማር ማስተማር እና የመመረቂያ ጽሑፍ የማማከር ሥራዎችን ማካሄድ እንዴት ይቻላል በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ውይይት አድርጓል። ከውይይቱም በኋላ የማታና የርቀት ትምህርት ፕሮግራሞች የማስተማርና የማማከር ተግባራት በኢሜልና የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም የመማር ማስተማር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጿል።

የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በማታና በርቀት ትምህርታችውን ለሚከታተሉ የቅድመ-ምረቃና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች በየትምህርት ክፍሎቹ ከተመደቡላቸው አስተማሪዎች እና አማካሪዎች ጋር አማራጭ የመገናኛ መንገዶችን በመጠቀም ግንኙነት በማድረግ ትምህርት እንዲከታተሉ እና የመመረቂያ ጽሑፍ ሥራዎችን እንዲያዘጋጁ የተከታታይና ርቀት ትምህርት ቢሮ መግለጹ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዘንድ መረበሽ መፍጠሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማታ ተማሪ እና ዘንድሮ ዓመት ተመራቂ የሆነች የአዲስ ማለዳ ምንጭ ተናግራለች።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት እና ትብብር ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ትብብር ዳይሬክተር ደመቀ አቺሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓመት በማታ መርሃ ግብር እና በኹለተኛ ዲግሪ የሚማሩት ተመራቂዎችን ነው ሐምሌ 4/2012 ለማስመረቅ ውሳኔ የተላለፈው ብለዋል።

ከተማሪዎች ለተነሳው ጥያቄ ደመቀ ምላሽ ሲሰጡ፣ መብራት እና የኢንተርኔት አገልግሎት በማስመረቅም ሆነ በማስተማር ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው እና ይህንም ዩኒቨርሲቲው የሚገነዘበው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሁን ባለው ሁኔታ አስቦ የወሰነው ውሳኔ ማስተርስ እና የማታ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ አካባቢ›› ይሆናሉ በሚል እሳቤ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዛም በተጨማሪ እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ በተለያዩ ስፍራዎች የሚኖሩ ከሆኑ ረጅም ጊዜ ሥራቸው እንዳይስተጓጎል በማሰብ ስለሆነ፣ ለተወሰነ ጊዜ ጥሩ የኢንተርኔት አገልግሎት ወዳለበት በመሆን ማከናወን እንዲችሉ ታስቦ ነውም ብለዋል።

ተማሪዎች ከዚህ ቀደም የነበረው ያህል አቅም እና ውጤት መጠበቅ ባይቻልም በነበረው አመዛዝኖ የሚኬድበት ሁኔታ እንደሚኖርም አስታውቀዋል።
እንደ ደመቀ ገለፃ ይህን መረጃ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ተወያይቶበት ነው የተወሰነበት ያሉ ሲሆን፣ አያይዘውም ‹‹የመመረቂያ ጽሑፍም ለማዘጋጀት ቢሆንም እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ ይገባ ነበር። የመመረቂያ ጽሑፉ ሲዘጋጅ መረጃ ለመሰብሰብ የተለያዩ ቦታዎች ጋር እንቅስቃሴ ሊኖር ይገባል። ነገር ግን እዛ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያጋጥማቸው ይገመታል።›› ብለዋል።

ነገር ግን ተመራቂ ተማሪዎች ኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ከመግባቱ ቀደም ብለው ይሄን አብዛኞቹ ማለፋቸውን ገልጸው፣ ቀሪው የመጨረሻው የጥናታዊ ጽሑፍ ክፍል ቤታቸው ሆነው መጨረስ ይችላሉ በማለት እንደሆነ ገልፀዋል። ይሁንና ዳይሬክተሩ አክለው፣ ‹‹እስከ አሁን ያልተመለሱ ጥያቄዎች በእኛም በኩል አሉ›› ቢሉም፣ ውሳኔው ግን ተማሪዎችን ለመጥቀም እና መመረቅ የሚችሉ ተማሪዎችን ወደ ሚቀጥለው እንዳይተላለፍባቸው ከማድረግ አንፃር ታስቦ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here