የአዲስ አበባ ሆቴሎች ከባንክ ያለባቸው ብድር እንዲራዘምላቸው ጠየቁ

0
852

በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ገበያቸው በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዙን ተከትሎ ከባንክ የወሰዱትን ብድር ከእነ ወለዱ የመክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘምና ለአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ እንዲያገኙ መጠየቃቸው ተገለፀ።

የአዲስ አበባ ባለሆቴሎች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን ይዘው ለመቀጠል እና ምንም ዓይነት የደሞዝ ቅናሽ ሳያደርጉ ይህን ፈታኝ እና አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ከሚወሰዱት አማራጮች መካከል የሆነው ከባንኮች ያለባቸውን ብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው መጠየቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ሆቴሎች ባለቤቶች ማኅበር ፕሬዘዳንት ቢኒያም ብስራት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ወቅቱ ሆቴሎች በከፍተኛ የገቢ መቀነስ ያጋጠመበት ወቅት እንደመሆኑ ብዛት ያሏቸውን ሠራተኞች ባሉበት ሁኔታ ይዘው መቀጠል ይከብዳቸዋል ብለዋል። ነገር ግን ከዛም በተጨማሪ በባንኮች ላይ ያለባቸው ብድር ለመክፈል የሚያስችል ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ እንደ ቢኒያም ገለፃ በማኅበሩ ውስጥ የሚገኙ አባላት ለባንክ የሚከፍሉትን ብድር ወለዱን ጨምሮ መክፈያ ጊዜያቸው ለአንድ ዓመት እንዲገፋላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። አክለውም ጥያቄው በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ አጥጋቢ እና መልካም ምላሽ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁ ተስፋቸውን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ውስጥ 180 ባለኮኮብ ሆቴሎች ያሉ ሲሆን፣ በማኅበሩ ውስጥ የሚገኙ ግን ከ130 በላይ መሆናቸው እና ኹሉም በአንድነት የተስማሙበት ጉዳይ እንደሆነም ቢኒያም ጨምው ጠቀሰዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሠራተኞችን በሚመለከት የወጣውን ፕሮቶኮል ተከትሎ ለማስኬድ ሌሎች አማራጮችን መከተል እንደሚገባ እና ይህንም አንደኛው አማራጭ እንደሆነ አውስተዋል።

በመጋቢት 2012 የአዲስ አበባ ሆቴሎች ባለቤቶች ማኅበር ያስጠናው ጥናት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አትቷል። በዚህ ጥናት ላይ እንደተቀመጠውም 88 በመቶ የሚሆኑት በማኅበሩ ስር የሚገኙ ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሥራ ለማቆም እንደወሰኑም ይገልጻል። እእንደጥናቱ ከሆነ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱትም፣ በከተማው ውስጥ ካሉ ሆቴሎች ውስጥ ከኹለት በመቶ በታች ክፍሎች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ታውቋል።

ሆቴሎች ከሚሰጡት የማደሪያ፣ ምግብና መጠጥ እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶች መቀዛቀዝ የተነሳ በወር እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡ ተገልጿል። ይሁን እንጂ ይህን በ130 ሆቴሎች ውስጥ ከ15 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ተቀጥረው እንደሚሠሩ ጥናቱ ያመላክታል።

በቀጣይ በሙሉ እና በከፊል አገልግሎት መስጠት ለማቆም ከወሰኑት 88 በመቶ ሆቴሎች ባለፈ ቀሪዎቹ 12 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ በአስገድዶ ማቆያ ለ14 ቀናት እንዲቆይ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ሰዎች ከፍለው ራሳቸውን አግልለው የሚያቆዩባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገልግሎት መስጠት እንዳላቆሙ ታውቋል። ይሁን እንጂ ቢኒያም እንደገለጹት ከ88 በመቶ ሆቴሎች ውስጥ 32 በመቶ የሚሆኑት በከፊል ሥራ ለማቆም የወሰኑ እና ቀሪዎቹ 56 በመቶ ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ለማቆም የወሰኑ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

በማኅበሩ ውስጥ በሚገኙት 130 ሆቴሎች ውስጥ በድምሩ ከስምንት ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ሆቴሎችም በአብዛኛው ባለ ሦስት እና ባለ አራት ኮኮብ ሆቴሎች መሆናቸው በጥናቱ ተገልጿል። በቀጣይ አሁን ያለውን ፈጣን የገቢ መቀዛቀዝ ተከትሎ ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት እና የሚዘጉበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

ይህንንም ተከትሎ የሆቴል ባለቤቶች ተጨማሪ በጀት ወደ ሆቴል ንግዱ ካልበጀቱ በቀረ ለሠራተኞች ወርሃዊ ደሞዝ ለመክፈል ብቻ ሳይሆን የሆቴሉን የኦፕሬሽን ወጪ እንኳን መሸፈን የሚያቅትበት ደረጃ ላይ እንደሚደረሱ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here