በአማራ ክልል የወባ መድኃኒት በወቅቱ አለመሰራጨቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትል ተፈርቷል

0
584

በየዓመቱ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተውን የወባ በሽታ ለመከላከል የሚረዳ መድኃኒት በወቅቱ ባለመሰራጨቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት አስታወቀ።

መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ለወቅቱ የሚያስፈልገውን የወባ በሽታ መከላከያ ግብዐት እንዳላገኘ እና የመከላከያ ግብአቶች ለሚያስፈልጋቸው ለተለዩ አካባቢዎች ማቅረብ እንዳልቻለ አስታውቋል።

በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት የወባ በሽታ ቡድን መሪ ማስተዋል ወርቁ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ሰዓት መድኃኒቶች ተከፋፍለው አልቀው በክልሉ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ተደርጎ 25 በመቶ የሚሆን መጠባበቂያ የሚቀመጥበት ወቅት እንደሆነና ይህም እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

ማስተዋል አክለውም የግብዐት አቅርቦት በቂ ካለመሆኑ ባሻገር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የመድኃኒት ዓይነቶች ሙሉ በሙሉ እንደሌሉ ተናግረዋል። እንደ ማስተዋል ገለፃ በክልሉ በሚገኙ የመድኃኒት ማከማቻ ቦታዎች ላይ የሌሉ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ መድኃኒቶች መሆናቸው አሳሳቢ ነው።

ለወቅቱ የሚያስፈልገው የወባ መከላከያ ግብዐት ክልሉ ላይ በበቂ ሁኔታ አይኑር እንጂ፣ ከማእከላዊ ቦታው እንዳለ መረጃው እንደላቸው እና ችግሩ ከማእከሉ ወደ ክልሎች የማሰራጨት መሆኑን ቡድን መሪዋ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ የሚከሰትባቸው ኹለት ወቅቶች እንዳሉ የገለጹት ማስተዋል፣ አንደኛው የወባ በሽታ የሚከሰትበት ወቅት የበለግ ዝናብን ተከትሎ ሲሆን፣ የሚከሰትበት ወቅትም ከግንቦት እስከ ሰኔ ወር መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት የወባ መተላለፍያ ጊዜ እንደሚጨምር እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ኹለተኛው የመተላለፊያ ወቅት ደግሞ የክረምት ዝናብን ተከትሎ የሚከሰት ሲሆን፣ ይሄም ከመስከረም አስከ ታኅሳስ ባሉት ወራቶች ነው። ይህ ወቅት የወባ በሽታ በስፋት የሚተላለፍበት ወቅት መሆኑንም ማስተዋል ጠቅሰዋል።

በክልሉ በሚገኙ የመድኃኒት ማከማቻ ቦታዎች ውስጥ በአንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ የሌሉ መድኃኒቶች ውስጥ የወባ በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ የሚያገለግል መድኃኒት በክልሉ ከሚገኙ መድኃኒት ማከማቻዎች ውስጥ እንደሌሉ ማስተዋል የተናገሩ ሲሆን፣ ሌላኛው አንድ ሰው በበሽታው ተይዞ በተወሳሰበ ደረጃ ላይ ማለትም መብላት፣ መጠጣትና መቀመጥ የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ በመርፌ የሚሰጥ መድኃኒት አለመኖሩን ማስተዋል አስታውቀዋል።

ቡድን መሪዋ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት ከሰጠው ማስጠንቀቂያ እና ወቅቱ የወባ በሽታ የሚከሰትበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን፣ መደረግ የነበረበት ዝግጅት አለመደረጉ አሳሳቢ ስለሆነ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል። በተጨማሪም በክልሉ ባለፈው መስከረም ወር ላይ የግብዓት አቅርቦት እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ማስተዋል አስታውሰዋል።

በክልሉ የወባ በሽታ ያጠቃቸዋል ተብለው የተለዩ ወረዳዎች 149 ናቸው።
በኢትዮጵያ የወባ በሽታ የሚከሰትባቸው ወቅቶች ውስጥ አንደኛው በሚቀጥሉት ወራት መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የወባ በሽታ ከዚህ በፊት ከነበረው በእጥፍ ሊጨምረው እንደሚችልና ጥንቃቄ እንዲደረግ የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የወባ በሽታ መድኃኒት (ክትባት) የሆነውን ክሎሮኪንን ለኮሮና ቫይረስ ፈዋሽ እንደሆነ በማመን ከየመድኃኒት ቤቶች እንደተገዙ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ነገር ግን ኅብረተሰቡ ከዚህ አመለካከት መውጣት እንዳለበት የጤና ባለሙያዎች አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው መድኃኒቶችን ወደ ክልሎች የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ እንደሆነና በቂ ክምችትም እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። ይህንንም ተከትሎ ሚያዚያ 22/2012 አጎበር የማሰራጨት ሥራ እንደሚሠራም አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here