ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች በመጪው የግንቦት ወር የጎርፍ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል ተገለጸ

0
645

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በመጪው የግንቦት ወር በኢትዮጵያ ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል አስታወቀ።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይከሰታል ተብሎ በሚታሰበው የጎርፍ አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና መከላከል ዙሪያ መግለጫ የሰጠ ሲሆን የጎርፍና የመሬት መንሸራተት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስቧል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳመና ዳሮታ እንዳሉት፤ በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት መከሰቱን አስታውቀዋል ።

”በድሬደዋ ከተማ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 4 ሰዎች ሞተዋል፤ 53 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል፤ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ቤተሰቦች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል” እንዲሁም በተመሳሳይ በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልና በሶማሌ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ ከባድ ዝናብና ጎርፍ በመሰረተ ልማትና እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በድሬደዋ፣ ሶማሌ ክልል ሸንሌ ዞን፣ ደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት 219 ሺህ 698 ሰዎች መጎዳታቸውን በተጨማሪም ከ108 ሺህ በላይ ሰዎችም መፈናቀላቸውን አቶ ዳመና ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ባገኘው መረጃ መሰረት አደጋው ቀጣይነት እንደሚኖረውና በግንቦት ወር ብቻ ከ 21 ሺህ በላይ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ስጋት መኖሩንም ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

ከእነዚህ ጉዳት ከሚደርስባቸው ሰዎች መካከል ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉም ጨምረው ጠቁመዋል።

በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች በመደበኛና ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ቅጽበታዊ የጎርፍ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አብራርተዋል።

በተጨማሪም በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ሃድያ፣ ባስኬቶ፣ ጋሞ፤ በአፋር ክልል ዞን አንድና ዞን ሁለት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

”ኅብረተሰቡም ንቁ በመሆን የሚደርሰውን አደጋ መከላከልና መቀነስ እንዲችል የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ ማድረግና የጎርፍ መከላከያ መንገዶችን ማጠናከር ይገባል” ማለታቸውንም ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here