የልደቱ መነጋገሪያነት እንደገና

0
571

ሰሞነኛ የማኅበራዊ ትስስር መነጋገሪያ ሆነው ከወጡት ጉዳዮች መካከል የልደቱ አያሌው ጉዳይ ይገኝበታል። የንትርኩ መነሻ ልደቱ ለሚዲያና ይመለከታቸዋል ላሉት አካላት የበተኑት ምክረ ሐሳብ ነው። ልደቱ ኢትዮጵያ ከመስከረም 2013 በኋላ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ውስጥ ትገባለች የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ሲሆን ይህንንም አመለካከታቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ላይ በመቅረብ ገልጸል።

ከዚህ መአት አገሪቱን ጎትቶ የሚያወጣው ብቸኛ መንገድ ሁሉንም የፖለቲካ ተዋናዮች የሚያካትት የኹለት ዓመት ቆይታ የሚኖረው የሽግግር መንግሥት ነው በማለት ዝርዝር አፈጻፀሙን በሚመለከተ ዳጎስ ያለ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከቀድሞ አክቲቪስት እና ከአሁኑ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል ከሆነው ጃዋር መሐመድ ጋር በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው መወያየታቸውም አንዳንዶችን አላስደሰተም፤ ድርጊታቸው ድጋፍንም ተቃውሞንም አስተናግዷል።

በርግጥ የልደቱ አከራካሪነት አሁን የጀመረ አይደለም፤ ከምርጫ 97 በኋላ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ወቅት ጠብቆ የሚነሳ ነው። ብዙዎች በተቃዋሚ ጎራ ያሉትን ጨምሮ ልደቱን ከምርጫ 97 እና ቅንጅት ክሽፈት ጋር በተያያዘ አንዱና ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው ብለው ጥርስ ነክሰውባቸዋል።

እንደ ፖለቲከኛ መሬት የወረደ ሥራ ሠርተው የጎላ ተጽዕኖም ፈጥረው አያውቁም የሚሏቸው ከሳሾቻቸው ከምርጫ 97 በኋላ ሕዝብን በማንቃት፣ በማደራጀት እና በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ በማድረስ በኩል ይሔ ነው የሚባል ሥራ መቼ ሠሩ ሲሉ ይጠይቃሉ። አፈ ጮማ ከመሆን ባሻገር በቀጥታ ምንም አስተዋጽዖ ባላደረጉባቸው አገራዊ (ፖለቲካዊ) እጥፋቶች በተፈጠሩ ቁጥር ራሳቸውን ከቀበሩበት ብቅ በማድረግ ደርሶ ተንታኝ እና ‘‘አዋቂነታቸውን’’ እንደመልካም አጋጣሚ ይጠቀሙበታል፤ ይሁንና ይህ አካሔድ እስካሁን ፍሬ አላፈራላቸውም ሲሉ ታዝበናል ያሉትን እንደመከራከሪያ ያቀርባሉ። ነቀፋው ጠንከር ሲል ቂመኛ፣ ግለኛ፣ እኔ ብቻ አዋቂ ነኝ ባይ ባስ ሲል ደግሞ ከሃዲ ሲሉም ይሰድቧቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ልደቱ የጦስ ዶሮ ሆኑ እንጂ ከሌሎች አቻዎቻቸው የተለየ ጥፋት አላጠፉም በማለት ሽንጣቸውን ገትረው የሚደግፏቸው አሉ። ልደቱ ላይ የሚደርስ አንደበተ ርዕቱ እንዲሁም ጥርት ያለ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ ያለው ፖለቲከኛ በኢትዮጵያ ምድር አልተፈጠረም ሲሉም ያንቆለጳጵሷቸዋል፤ ልደቱ ፅኑና የሐሳብ እና የመርኅ ሰው ናቸውም ሲሉ ያሞካሸዋቸዋል። ማንም መጣ ማንም ሔደ ከመርኀቸው ዝንፍ አይሉም የሚሉት ደጋፊዎቻቸው፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካና የሐሳብ እድገት ካስፈለገን እንደ ልደቱ ዓይነት ሰዎች ሊበዙልን ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ።

ሌላው በብዙ ፖለቲከኞቻችን የማናየው ነገር በዛ ያሉ መጽሐፍትን ማበርከታቸው በመጥቀስ ሰውየው ያላቸውን የፖለቲካ እውቀትና ልምድ በማካፈል አቻ የላቸውም ሲሉ ደጋፊዎቻቸው በልበ ሙሉነት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ያም ሆነ ይህ ልደቱ ሆኑ የሚያቀነቅኑት ሐሳብ የወቅቱ መነጋገሪያ መሆናቸውን ቀጥለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here