ሃይማኖትና ተቋማቱ በ‹ማዕበሉ› መካከል

0
948

ዘመናዊት ዓለም ሃይማኖትን ወደ ዳር አድርጋለች። በሴኩላሪዝም ሰበብም አጥሩ በሩቅ ታጥሮ፣ ሃይማኖትና መንግሥት ‹አትምጣብኝ አልመጣብህም› የሚባባሉ ደባሎች ሆነዋል። ይህም የሆነው የሃይማኖት ተቋማት በቀደመው ዘመን የነበራቸውን ኃይልና ሥልጣን በአግባቡ ስላልተጠቀሙ ነው የሚል ሙግት የሚያነሱ አሉ።

ለዚህም ማሳያ የሚሉትን ሲያነሱ ሃይማኖት በዓለም ለተነሱ በርካታ ግጭቶችና እልቂቶች መነሻ ሆኖ ያውቃል በማለት ይጠቅሳሉ። እናም ዓለም ሃይማኖትን ዳር ካላስያዘች በቀር ፈላጭ ቆራች ብታደርጋቸው፣ እርስ በእርስ በመገፋፋት ብዙ ጥፋት ያደርሳሉ የሚል ሐሳብም ያነሳሉ። አማኞች ግን አሁንም አሉ። እንዲህ ከባድ ወረርሽኞች በሚከሰቱባቸው ጊዜያትም መጽናናትና መበርታት ከመንግሥት በኩል የሚገኝ ባለመሆኑ የሃይማኖት ተቋማት እንዲበረቱ ይጠየቃሉ።

የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወረርሽኝ ኮቪድ 19ም መንግሥትና ሃይማኖት እንዲነጋገሩ አድርጓል። መንግሥት በሮቹን ለተቋማቱ ሲከፍት፣ ተቋማቱም ሳይወቅሱ ሳይከሱ ምዕመናንን እያጽናኑ ይታያሉ። ይህም ከጣልቃ ገብነት የሚቆጠር ነው የሚሉ ሲኖሩ፣ በአንጻሩ ‹በዚህ ወረርሽኝ ሰዓት ሴኩላሪዝምን እንዴት ታስባላችሁ?› ባዮች ተሰምተዋል።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት የሃይማኖት ተቋማት በወረርሽኞች ጊዜ ያደረጉትን አስተዋጽኦ፣ የነበራቸውን ድርሻ፣ አሁን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራትና የደረሰባቸውን ተጽእኖ በሚመለከት፣ መዛግብትን በማገላበጥና የሚመለከታቸውን በማናገር የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ባለፈው አንድ ወር በየእለቱ ምሽት ሦስት ሰዓትን በጉጉት ነበር የምትጠብቀው፣ ሶጃት አሊ። በቴሊቭዥን የሚታየውን የትምህርትና የጸሎት መርሃ ግብርም ከቤተሰብ ጋር ተሰብስበው እንደሚከፊሉ አንስታለች። ‹መስጂድ እንደመሄድ፣ በኅብረት ሆኖ ዱአ እንደማድረግ አይደለም። ግን ይህም አማራጭ ሆኖ ከቤተሰብ ጋር ሊያሰባስበን ስለቻለ በጣም ደስተኛ ነበርኩ› ስትል ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን ሰጥታለች።

ብዙዎች የእናቶችና የአባቶችን፣ የቤተሰባቸውን ሁኔታ በምስል አስቀርተው በማኅበራዊ ድረ ገጽ አጋርተዋል። ከቴሌቭዥን መስኮት ፊት ለፊት ቆመው፣ ነጠላቸውን አጣፍተው፣ ምንጣፋቸውን አንጥፈው፣ ሻርፓቸውን እንደ ደንቡ አስተካክለው ጸሎት፣ ዱአ ያደረጉ ጥቂት አይደሉም። በመምህራኖቻቸው የሚሰጡ ትምህርቶችንም ሥራዬ ብለው ጆሮ ሰጥተው የተከታተሉም እንደዛው።

በተመሳሳይ ጊዜ ስጋት የገባቸውም አሉ። መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ ወይም ሊገባ ማሳያው ይሆን የሚሉም አልታጡም። በአንጻሩ በወረርሽኙ ምክንያት እንጂ እንዲያ ያለ ስጋት ውሃ አያነሳም በሚል የሚሞግቱ መደበኛ ባልሆነው የሕዝብ መገናኛ ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ ተስተውሏል።

ምልሰት 1
ከአንድ ወር በፊት መጋቢት 28 ቀን 2012 በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 44፣ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ደግሞ ኹለት ነበሩ። በዚህም እለት ነው ቀደም ብሎ የታወጀ አገር ዐቀፍ የጸሎትና ምህላ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት የተከናወነው። በቤተመንግሥት በተካሄደው በዚህ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የሃይማኖት አባቶች ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ባለሥልጣናትም የተገኙ ሲሆን፣ ሥነ ስርዓቱ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት የመንግሥት በሚባሉ መገናኛ ብዙኀን ቀጥታ ተላልፏል።

ጸሎትና ምህላው በአገር ዐቀፍ ደረጃ እንዲከናወን ተነሳሽቱን ወስዶ ሐሳቡን ለመንግሥት ያቀረበው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነበር። የጉባኤው ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ዓለምን ሰቅዞ የያዘው ኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ አደገኛና ዓለም ዐቀፍ፣ የሰውን ዘር ቀለም ብሔር፣ ጾታና መደብ፣ ወሰንና ድንበር የማይለይ በሽታ መሆኑን በእለቱ ባደረጉት ንግግር አነሱ።

ታላላቅ አገራትን ጨምሮ የሠለጠኑ ሀብታም ነን ያሉትን በእኩል ደረጃ የሚያጠቃ ወረርሽኝ መሆኑን ካወሱ በኋላ፣ የጥንቃቄ ምክሮችን ከመተግበር ጎን ለጎን አማኞች ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠብቁ የሚያደርግና በጸሎት ትጋት የሚፈለግበት ጊዜ መሆኑንም አያይዘው አሳሰቡ።

ከዛም በተጨማሪ ክዋኔው በቴሌቭዥን መስኮት መቅረቡ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሃይማኖት ተቋማት በሮች የተዘጉ በመሆናቸው፣ በጸሎት ከመትጋት ጎን ለጎን አማኞች በቤት ውስጥ ሆነው ያንን እንዲከታተሉ ለማስቻል ነው ሲሉ አስታወቁ።

ከዚህ በኋላም በእለቱ የሃይማኖት አባቶች ምዕመኑን ይቅርታ ጠይቀው በየስርዓታቸው ጸሎትና ዱአቸውን ቀጠሉ። ይህ ክዋኔ በተመሳሳይ ያህል በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ በዋልታ፣ በፋና እንዲሁም በአዲስ ሚድያ ኔትወርክ ለአንድ ወር ሲካሄድ ቆይቶ፣ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 27/2012 መዝገያ መርሃ ግብር በጋራ ተከናውኗል።

አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ ለመሥራት የተለየ የዳሰሳ ጥናት ባታደርግም፣ በማኅበራዊ ሚድያ ስርጭቱን ቀጥታ ይከታተሉ የነበሩ ተጠቃሚዎች ከስር የሰጡት አስተያየት እንደሚያመላክተው ግን የሐሳቡና የክዋኔው ደጋፊ ጥቂት እንዳልሆነ ነው።

ከእነዚህ መካከል ፍቅርተ አንደኛዋ ናቸው። የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት ፍቅርተ፣ የጸሎትና ትምህርት መርሃ ግብር በቴሌቭዥን በመታየቱ ደስ መሰኘታቸውንና፣ ይህ በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ሆነም አልሆነም ለእርሳቸው ልዩነት እንደሌለው ገልጸዋል። ‹‹የሃይማኖት ተቋማት የራሳቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ አላቸው። ቀጥታ ስርጭት እንዳያስተላልፉ የአቅም ጉዳይ ስላለባቸው ይሆናል እንጂ በራሳቸውም ሊያስተላልፉት የሚችሉት ነው።›› ብለዋል።

የመንግሥትን ድጋፍና ተሳትፎም በተመለከተ ሲያነሱ፣ መንግሥት የሕዝቡን ሃይማኖት እንዳከበረና እውቅና እንደሰጠ ነው የምቆጥረው ብለዋል። ‹‹በቫይረሱ ምክንያት እንደ በፊቱ ቤተ እምነቶች መሄድ አለመቻላችን እና ቤት ውስጥ ሆነን አገልግሎቱን እንድናገኝ መፈለጉን ያሳየበት ነው። ለዚህም መንግሥትን እንዲሁም ያስተላለፉትን ጣቢያዎች አመሰግናለሁ።›› ሲሉ የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።

ምልሰት 2
ዓለም ከዚህ ቀደም አስከፊና ብዙ ሰዎቿን የቀጠፉ ወረርሽኞችን አስተናግዳለች። የሰዎች በአካል መቀራረብ ለመስፋፋት ምክንያት ለሆናቸው ወረርሽኞች ደግሞ የአካል መራራቅ ሰዎች እንዲለያዩ፣ እንዳይጠያየቁና እንዳይደጋገፉ አድርጓል። በተለይም እንደ አሁን የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ያልተስፋፉባቸው ጊዜያት፣ ዘመድ ያለው እንደሌለው፣ ቤተሰብ ያለው እንደ ብቸኛ ተትተው፣ ተለያይተው አልቀዋል።

በእነዚህም ጊዜያት የሃይማኖት ተቋማት አማኝ ምዕመናንን ለማጽናናትና ለማበርታት በየፈርጃቸው ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ታሪክ ያስረዳል። ይልቁንም እንደዛሬ የኢንተርኔት አገልግሎት ያልነበረበትና በአንድ የቴሌቭዥን መስኮት በየቤቱ የማይደረስበት ጊዜ ላይ በተከሰቱት ወረርሽኞች፣ አገልጋይ የሚባሉ መምህራን የየእምነቱ አባቶች ለራሳቸው ጤና ሳይሳሱ በየምዕመኑ ቤት በመሄድ ያስተምሩ፣ ጸሎት ያደርጉ እንደነበርም ታሪክ ይነግረናል።

በአዲስ አበባ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼሕ አሊ መሐመድ ሺፋ ከማስተማርና ከማጽናናት አልፎ የመፍትሔ ሐሳብና መንገድ በማጣትም ከዚህ ቀደም ሃይማኖቶች ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ያነሳሉ። ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደጠቀሱት፣ እምነት ዓላማው የእምነትን ባለቤት መጉዳት ሳይሆን መጥቀም ነው።

እናም እንዲህ አሉ፣ ‹‹ወረርሽኝ ሁልጊዜ ይከሰታል። አንድ ጊዜ ሶርያ ላይ ተከስቶ ነበር። ይህም ብዙ ሰው ያለቀበት ነው። በተለይም የነብዩ ተከታዮች 30 ሺሕ በጣም ታዋቂ ታዋቂ የሆኑትም በወቅቱ አልቀዋል። በዚህ ምክንያት ሲያልቁ የነበሩት መሪ ከመዲና የሄዱት አብደላ ሙጀራ ይባሉ ነበር። አብደላ ሙጀራ ይህን በሽታ መቋቋም አልቻሉም። ስላልቻሉም በሽታው በጣም ብዙ ሰው ፈጅቶባቸዋል፣ ጨርሶባቸዋል። እርሳቸውም በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ሞቱ።››

ታሪኩን ቀጠሉ፣ ከአብደላ ሙጀራ በኋላ የመጡት ሞአዝ ሙጀበል ሲሆኑ፣ እርሳቸውም በዛው ወረርሽኝ ምክንያት ሞቱ። ሦስተኛ የተተኩት አምል ሙልአስ የሚባሉ መሪ ግን የበሽታውን ጸባይ ተረድተው፣ ዱአ ከማድረግና አምላክን ከመለማመን ጎን ለጎን ሰዎች በአካል በመራራቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳሰቡ።
ሼሕ አሊ እንዲህ ጠቅሰውታል፤ ‹‹እርሳቸው ሲተኩ ግን ሁኔታውንና ማኅበረሰቡን ተመለከቱ። ማኅበረሰቡ በአንድ ላይ ነው የሚሰግደው፣ በአንድ ላይ ነው የሚሄደው፣ ርቀቱን አይጠብቅም፣ ይነካካል። እናም ‹ይህ በሽታ እሳት ነው፤ ማገዶው ማን ነው?› አሉ። እሳት በባህሪው ደግሞ ጨርቅም ይሁን እንጨት ወይም ላስቲክ፣ ያገኘውን ነገር የመብላት እድል ስላለው ይህን እሳት በምንድን ነው ማጥፋት የምችለው ብለው አሰቡት። እሳት ሊጠፋ የሚችለው በውሃ ነው። ስለዚህ እርሳቸው የወሰዱት አማራጭ፣ ማገዶው የሰው ልጅ ነው ብለው በመነሳትና እሳቱ ወረርሽኙ ነው በማለት፣ የሰው ልጆች መቀራረብ የለባቸውም፣ መገናኘት የለባቸውም፣ በአንድ ላይ መሄድ የለባቸውም፣ መራራቅ አለባቸው የሚል ውሳኔ ወሰኑ።››
ከዚህም በኋላ ሰዎች በተራራ ላይ ርቀታቸውን ጠብቀው ቆዩ። ወረርሽኙንም በዛ መቆጣጠር እንደተቻለ ያወሳሉ።

በተመሳሳይ የሃይማኖት አባቶች ከምዕመናኑ ጋር አብረው መከራን በመጋፈጥና በማስታመምም ጭምር የሚነሱባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። እነዚህ አባቶች ምዕመናን ለሆኑ በጎቻቸው እንደ ጠባቂ እረኛ ይቆጠራሉናም እንደ ግለሰብ የሸሹ አይደሉም። ‹የቆጵሮስ ወረርሽኝ› ለዚህ ተጠቃሽ ነው። በዚህ በ250-262 በሮም ተከሰተ በሚባል አስከፊ ወረርሽኝ ጊዜ የሃይማኖት አባቶች አስታማሚ ሆነው አገልግለዋል።

በኢትዮጵያም የመንፈሳዊና የሃይማኖት ሰዎች አገልግሎት ላይ ያለውን ሁኔታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹የኻያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ› የሚል ርዕስ ባለው፣ ከ1896 እስከ 1922 በኢትዮጵያ ታሪክ ካየሁትና ከሰማሁት ብለው ባስነበቡት መጽሐፍ አንስተዋል።

ቃል በቃል እንዲህ አስፍረውታል፤ ‹‹በዚያ ወራት በአዲስ አበባ የነበረው ጭንቀት በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቻለሁ። የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሃ ሲያድሉ ሰነበቱ። …በሌላም ስፍራ የዚህን ዓይነት ትሩፋት የሠሩ መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሙሴ ሴደርኩዊስት የተባሉ ሽማግሌ (የስዊድን ሚሲዮን አስተማሪ) በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሃ፣ መድኃኒትም በመስጠት ትሩፋት መሥራታቸውን ሰምቻለሁ። እኒህ ሽማግሌ ሚስዮናዊ ከጥቂት ቀን በኋላ በዚህ በሽታ ታመሙና ሞተው ተቀብረዋል።››

የሃይማኖት ተቋማት በኮቪድ 19
የሃይማኖት ተቋማት ለምዕመናኑ በራቸውን ከመዝጋታቸው አስቀድሞ አገልግሎቶቻቸውን ሰዎች በጥንቃቄ እንዲሳተፉ ለማድረግ ሞክረዋል። ያም ሆኖ ቫይረሱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ በሮቻቸውን እንዲዘጉ አድርጓል፤ አስገድዷል።

ይህም ታድያ ቀላል ውሳኔ አልነበረም። ምዕመናንም በእምነትና በጥንቃቄ መካከል ሆነው ስጋት የገባቸው ጊዜ ነበር። ብዙ እማኞችም እምነት እንዲሁም መፍራትና ጥንቃቄ ማድረግ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ይሰማቸው ስለነበርም፣ ጥንቃቄ ማድረግ ከእምነት ማጣት የሚመነጭ አይደለም የሚለውን ርዕስ የየሃይማኖቱ መምህራን ደጋግመው ሲያስተምሩት የነበረ ርዕሰ ጉዳይ ነው።

እናም ተቋማቱ ዘመናዊ የሆኑ የኢንተርኔትና መሰል አገልግሎቶችን ለመጠቀም ተገደዱ። በሮም የትንሣኤ በዓል ሰሞነ ሕማማትም በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ይተላለፋል ተባለ። ይህም በወረርሽኙ ምክንያት ነው። በወረርሽኙ ምክንያት የሃይማኖት ተቋማት መዝጊያዎቻቸውን ከረቸሙ። በአዲስ አበባም በተዘጉ የሃይማኖት ተቋማት በሮች ላይ ወታደሮች ቆመው እንዲጠብቁ ሆነ።

በታሪክ ሆኖ የማያውቅ ክስተት በኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሆነ። ቅድስትና ቅዱስ የተባሉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቁ ከተሞች ቤተመቅደሶቻቸውን፣ መስጂዶቻቸውን ዘጉ። ለአምልኮና ለጸሎት የሚታደምም ሆነ ለጉብኝት የሚሄድባቸው ሁሉ ራቃቸው። ዓለም ያገኘችው ለበሽታው የሚሆን መፍትሔ አካላዊ መራራቅና ፈቀቅታ በመሆኑ ውሳኔውም ከረር ያለ እንዲሆን ግድ አለ።

ይህ የሃይማኖት ተቋማትን ውሳኔ ዓለም ሳታደንቅ አልቀረችም። ምንም እንኳ ብዙ የጎደለባቸውና በቤት ሆኖ ጸሎትና አምልኮ ማድረስ በቤተ እምነት መገኘትን እንደማይተካ የሚያምኑ ብዙዎች ቢሆኑም፣ ወረርሽኙ ለመግታት ግን በተቋማቱ መሪዎች የቀረበውን ‹ቤታችሁ ሁኑ› አማራጭ እየመረራቸው ውጠውታል። ይህ የሃይማኖት ተቋማት ውሳኔም ሰውን ለማዳን ቅድሚያ እንደሰጡ ማሳያ እንደሆነ ብዙዎች አምነውበታል።

የመፍትሔ ‹ለምድ› የለበሱ
አዲስ ማለዳ ከዲያቆን ዶክተር አቤል ኃይሉ ጋር ከዚህ ቀደም ባደረገችው ቆይታ ሳይንስና እምነት ስላላቸው ግንኙነት አንስተው ነበር። ‹‹ሳይንስና እምነት የሚስማሙበትም የሚለያዩበትም መንገድ አለ።›› ያሉት አቤል፣ ይህም ልዩነታቸው መነሻው የሚመለከቱበት መነጽር ነው ባይ ናቸው።

በእይታቸውም መሠረት ሳይንስ ሕይወት ላይ ትርጉም ከመፈለግ ይልቅ የሆነውን ነገር ማብራራት ይቀናዋል ይላሉ። አንድ ወረርሽኝ የመጣበትን ምክንያት ሌላ ከምንም ሳይሆን ከምንጩ ያጠናሉ። መነሻ ምክንያቱን፣ ከእንስሳት ነው ከሰው፣ ማን ወደማን አስተላለፈ፣ ምን ዓይት ባህሪ ያለው ተዋህስ ነው በማለት ያጠናሉ።
ሃይማኖት ደግሞ በሽታው በምንም ምክንያት የተነሳ ይሁን፣ እንደዛም ሊሆን የቻለው በፈጣሪ ቁጣና በሰው ልጆች ኃጢአት በማዘኑ ምክንያት ነው ብሎ ያምናል። ከዛም በኋላ ነው የሳይንሱ ዝርዝር ነጥቦች የሚከተሉት።

አቤል እንዲህ አሉ፣ ‹‹ሳይንሱ የተለወጠ ቫይረስ ነው የበሽታው መምጫ ይላል። ሳይንሱ ውሸት አይደለም፣ በቫይረስ እንደሚተላለፍ ደርሰውበታል። ሰዎች በተለያየ ምክንያት ወደሞት ሊጠሩ ይችላሉ። ሳይንስ በሰዎች መከራና ድካም ላይ ምንም ዓይነት ትርጉም አይፈልግም፤ የጥናቱ አካልም ሆነ አቅጣጫ አይደለም። ሃይማኖት ከሳይንስ የሚለየው እሱ ነው። ሃይማኖት በሰዎች ድካም፣ ስቃይና መከራ ውስጥ ትርጉም ነው የሚፈልገው።››

አንዳንዴ ታድያ በኹለቱ መካከል ግጭት ወይም አለመስማማት ሲፈጠር ይታያል። ይህም ብዙ ጊዜ በሃይማኖቶች ወይም በሳይንስ ባለ አስተሳሰብ ምክንያት ሳይሆን፣ ያንን በሚቀበሉ ሰዎችና ትክክል ባልሆነ አካሄዳቸው ምክንያት የሚሆን ነው። በዚህም ሰበብ የሳይንስ ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ የጤና ባለሞያዎችም ተቃውሞ ያሰሙበት ጊዜ ጥቂት አይደለም።

ለምሳሌ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ እንደተከሰተ ሰሞን፣ ወር ሳይሞላ ይጠፋል የሚል ‹ትንቢት› የተናገረ አንድ የሃይማኖት ‹አስተማሪ› ውግዘት ደርሶበታል። እንደዛው ሁሉ ሲያሳስቱ የነበሩ አልታጡም። ታድያ በጥቂት ጊዜ ቫይረሱ ይጠፋል ያለው ሰው ባለው ጊዜ ወረርሽ ጭራሽ ዓለምን ከዳር እዳር አዳርሶ ስለተገኘ፣ ትምህርቱን የሚከታተሉ የነበሩ ምዕመናን ‹ምነው ያልከው ሳይሆን ቀረ?› ብለው መጠየቃቸው አልቀረም። እርሱም መልስ አላጣም፣ ‹ጭራሽ ይጠፋል ማለቴ አልነበረም። እናንተ አልተረዳችሁኝም እንጂ! ቫረሴ የተነሳባት የቻይናዋ ዉሃን ግዛት ትቆጣጠረዋለች ማለቴ ነው። ያ ደግሞ ሆኗል› በማለት መልሷል።

በተመሳሳይ ‹ሃይማኖታችን ስለማይፈቅድልን፣ በፈጣሪ አምሳል የተሠራ ነውና ፊታችንን አንሸፍንም፣ ጭንብል አናደርግም› የሚል ትምህርት ያስተምሩ የነበሩ የ‹ሃይማኖት› ሰዎች እንደነበሩም የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኀን ሲያነሱ ታይተዋል።

ይህ ሁሉ ጥፋት የሆነው መሪዎች እንዲህ ባሉ ምክሮች የሚዘናጉ እንዳይሆን ከመስጋት በላይ ሕዝብ ስለሚሳሳትና ለበሽታዎች ተጋላጭነቱ ስለሚጨምር ነው። ይህም እንዳለ ሆኖ ያልተባለ ነገር ፈጥረው የሚያወሩ እንዳሉም በኢትዮጵያ ቫይረሱ እንደተገኘ በተሰማ ማግስት ሲነገር ተሰምቷል። የገዳም አባቶችን በመጥቀስ ‹ይህን ይህን እስከ ዚህ ሰዓት ድረስ ተጠቀሙ ብለዋል› በሚል ሐሰተኛ መረጃም ብዙዎች የተባለውን ፈጽመው፣ ቫይረሱ አይዘንም በሚል መዘናጋት ውስጥ አንድና ኹለት ቀናት መኖራቸው የሚረሳ አይደለም።

ይህንንም የጤና ባለሞያዎች ደጋግመው ኮንነውታል። እንዲህ ያሉ ሃይማኖትን ተገን ያደረጉ ብቻ ሳይሆን በመንገደኛ የሚፈጠሩ መላምቶች ለሐሰተኛ መረጃዎች መስፋፋት ድረሻ ነበራቸው። ቫይረሱ አፍሪካውያንን አይዝም፣ ወጣቶችን አያጠቃም፣ ሕጻናትን አያገኝም የሚሉም የማይረሱ ሐሰተኛ መረጃዎች ናቸው።

መንግሥትና ሃይማኖት?
ሴኩላሪዝም መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ይላል። ይህ ግልጹ መረዳት ሲሆን መንግሥት ሃይማኖት እንደሌለው አካል ይቆጠራል። ምንም እንኳ ጽንሰ ሐሳቡ እጅግ ሰፊና ጥልቅ፣ እንደ አውዱ የተለያየ ሊሆን ቢችልም፣ ሁሉንም የሚያግባባው መሠረታዊ ነጥብ ግን ሃይማኖትና መንግሥት አንዳቸው በሌላቸው ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ ነው።

በሠለጠኑ አገራት ይህ እንደ ችግር ሆኖ አይታይም። በአንጻሩ በአፍሪካ ምድር ግን በበርካታ አገራት ሃይማኖትና መንግሥትን ነጣጥሎ ማሰብ ፈታኝ ነው። አጥኚዎች እንደሚናገሩት በሠለጠኑ አገራት፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ጉዳዩ አሳሳቢ ያልሆነው ከአፍሪካ በተለየ በአገራቱ የሚገኙ ሃይማኖቶች ብዝኀነት ያላቸው ባለመሆናቸውና የተከታዮቻቸውም ብዛት በአፍሪካ ምድር ያለውን ያህል ስላልሆነ ነው።

ታድያ አሁንም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በአፍሪካ ምድር የአገራት መንግሥታት ሃይማኖት ተቋማትን እንዲሁም እምነትን በሚመለከት መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ተሰምቷል። ለምሳሌ በታንዛንያ የሆነው ይነሳል። የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) በታንዛንያ የሦስት ቀን አገር አቀፍ ጸሎት እንደታወጀ ያወሳል። ከአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 94 በደረሱበት ጊዜ ነበር አዋጁ የታወጀው።

ይህም አዋጅ በመንግሥት ደረጃ ነበር ይፋ የተደረገው። በተመሳሳይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራትም የሃይማኖት ተቋማት ምዕመናኑ ጸሎት እንዲያደርጉና በዛም እንዲተጉ ከማሳሰባቸው በላይ የአገራቱ መሪዎችና መንግሥትም፣ ‹ጸልዩ! እንጸልይ!› ሲሉ ተደምጠዋል።

በዚህ ጊዜ በታንዛንያ መንግሥት በአገሪቱ አካላዊ መራራቅና ማኅበራዊ ፈቀቅታ እንዲኖር ያሳሰበ ቢሆንም፣ የእምነት ተቋማት ግን ሳይዘጉ በነጻነት አገልግሎት እየሰጡ ቆይተዋል። ይህንን እና በሌሎች አገራትም ያለውን የእምነት ተቋማት አለመዘጋት በመቃወም በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙኀን መረጃዎችን ያቀብሉ ነበር። ‹የአፍሪካ መሪዎች በር ከመዝጋት ይልቅ ጸሎት ነው ወይ ለቫይረሱ የሚሰጡት ምላሽ› የሚሉ ዘገባዎችም ተነብበዋል።

አንዳንድ መሪዎች እንደውም ‹በእምነት የምንበረታበት ጊዜ እንጂ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ላይ የምንተማመንት ጊዜ አይደለም› ብለዋል ተብሎ ተወቅሰዋል። ይህም ያልተገደበ እንቅስቃሴ በእምነት ይሳበብ እንጂ አንዳንዶች መሪዎች የምጣኔ ሀብት ድሽቀት ጉዳይ አሳስቧቸው ነው ቸል ያሉ የመሰሉት ያሉም አልጠፉም።
በኢትዮጵያም መጋቢት 28/2012 ነበር አገር ዐቀፍ የጸሎትና ምህላ አዋጅ የታወጀው። ይህም በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተወሰነ ይሁን እንጂ ክዋኔው የመገናኛ ብዙኀን የአየር ሰዓት በመንግሥት በኩል የተሰጠው መሆኑ ይታወሳል። ይህን በማንሳት ታድያ ጉዳዩ ‹ሴኩላሪዝም›ን የሚጥስ ነው ያሉ አሉ። እነዚሁ ሰዎች መንግሥት እያለሳለሰ ከሚያደርገው ሃይማኖት ውስጥ የመግባትና ተጽእኖ የመፍጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋታቸውን አካፍለዋል።

‹‹ዛሬ ብዙዎች በሚፈልጉት መንገድ መንግሥት መንቀሳቀሱን አትዩ። ነገ በሃይማኖት ዙሪያ የማትፈልጉትን ሲያደርግ አፍ ያሳጣችኋል›› ብለው የመከሩም አሉ።
ሥማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ለአዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡ አስተያየት ሰጪ ይህን ነጥብ አንስተዋል። ይልቁንም የጸሎትና የትምህርት መርሃ ግብሩ እንዳይቀጥል እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል። ምንም እንኳ እርሳቸው በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የነበሩ ቢሆንም፣ ‹የመንግሥት አካሄድ ደስ የሚል አይደለም። በእርግጥ ያደረጉት ነገር አሁን ሊያስመሰግን ይችላል። ቢሆንም ዛሬ ሁላችንንም ደስ የሚያሰኘንን ነገር አድርገው ነገ በራሳቸው መንገድ እንድንሄድ ሲፈልጉ እንቢ እንዳንል የሚያደርግ ሊሆን ይችላል።›› ብለዋል።

አያይዘውም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመደበኛ ሥራቸው ጋር በተያያዘ በሃይማኖት የሚመስሏቸውን ወደ ሥልጣን ማምጣታቸውን እርሳቸውም እንደ ሁሉም ሰው እንደሚታዘቡ በመጥቀስ፣ ‹ይህን ጉዳይ ጮክ ብለን አላወራነውም። ጉዳዩ ሴኩላሪዝምን የሚጋፋ ይሁን ወይም ሌላ፣ እኔ ግን መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ተጽእኖ ወደ መፍጠር እንዳይገባ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው።› በማለት ገልጸዋል።

ይህን ስጋት የሚጋሩ ጥቂቶች አይደሉም። እንደማሳያም በዚሁ ኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቻይና የሆነውን ጉዳይ ያስታውሳሉ። የቻይና መንግሥት እንደ መንግሥት ከሃይማኖት የተገለለ ቢመስልም ኤቲዝምን የሚደግፍ ነው። ይህንንም በመንግሥት ፖሊሲና አሠራሮች ውስጥ በጉልህና በግልጽ ያንጸባርቃል።

ታድያ አሁን ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ፣ በወረርሽኙ ዙሪያ የሚሰጡ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች እንዲቀሩ በማለት ጸረ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። በይዢንግ የሚገኝ አንድ ቤተክርስትያንን አፍርሷል፣ ጉያንግ በሚባል ግዛት ካለ ቤተክርስትያን ራስ ላይ የነበረ መስቀልም እንዲነሳ አድርጓል።

ሻንዶንግ በተባለች ሌላዋ የቻይና ግዛት፣ በቀጥታ የኢንተርኔት አገልግሎት ስብከትም ሆነ ትምህርት እንዳይሰጥ ተከልክሏል። ይህም በቻይና የሚገኙ ክርስትያኖች በአንድ በኩል ስደታቸውን ለመቀነስ በተጓዳኝ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሚደረገውን በአካል መራራቅ ለመተግበር ያደረጉት ጥረት ነበር። ሆኖም አገሪቱን በሚመራው መንግሥት የተፈቀደላቸው አይመስልም።

በአንጻሩ በአሜሪካ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጎን ቆሞ የታየበት አጋጣሚ አለ። የዚህም ማሳያ በሚሲሲፒ የሆነው ነው። በሚሲሲፒ በመኪና ማቆሚያ ስፍራ ምዕመናን ተሰብስበው ነገር ግን ሁሉም ከየመኪናቸው ሳይወጡ፣ በድምጹ ማጉያ የሃይማኖት ትምህርት ተከታትለዋል፤ አምልኮም ፈጽመዋል። ይህንንም ተከትሎ የከተማዋ አስተዳደር የአምስት መቶ ዶላር ቅጣት በእያንዳንዳቸው በስፍራው በተገኙ ምዕመናን ላይ ጣለ።

ነገር ግን መንግሥት ሃይማኖትን የመለማመድና የመተግበር መብታቸውን በማንሳትና ላደረጉትም ጥንቃቄ እውቅና በመስጠት ከቤተክርስትያኒቱ ጎን ቆሟል።
ይህ ከባህር ማዶ የሚሰማ ክስተት ሆኖ፣ በኢትዮጵያም የኢፌዴሪ መንግሥት ለሃይማኖት ተቋማት የሚየስተምሩበትና ወረርሽኙን ለመግታት የሚያግዙበትን መንገድ አመቻችቷል። ‹ለአንድ ወር በአገር ዐቀፍ ደረጃ እንጸልይ› ሲሉም አዋጁ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እንዲሆን፣ ለተግባራዊነቱም የቴሌቭዥን ጣቢያዎቹን እንካችሁ ብሎ የአየር ሰዓት እንዲያገኙ አድርጓል።

ወረርሽኙን ከመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብ የሚቻል ባይሆንም ለሃይማኖት ተቋማት ግን ክልከላው ጠብቆ ተግባራዊ አልሆነም፣ ምንም እንኳ ሥማቸው እንዳይጠቅስ የፈለጉት አስተያየት ሰጪ በዚህ ሐሳብ ባይስማሙም። እርሳቸው እንደሚሉት እንደውም በሃይማኖት ተቋማት አዋጁ የበለጠ ተግባራዊ ሆኗል ነው።

‹‹በቴሌቭዥን እንድታዩ እያደረግን ነው። መስጂድም ሆነ ቤተክርስትያን በአካል መሄድ አይጠበቅባችሁም እያሉን ነው። ከንግድ ማእከላት በላይም በወታደር እየተጠበቁ ያሉት አምልኮ ስፍራዎች ናቸው። የሃይማኖት ተቋማት ሕጋዊ እውቅና ስላላቸው ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ይመቻሉ። በትክክል ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ቦታ ላይ ግን ቸልታ በግልጽ ይታያል።›› ሲሉ አንስተዋል።

ስብከትና ትምህርት በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን
በአሜሪካ የሚገኘው የፌዴራል የተግባቦት ኮሚሽን፣ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እምነትን አጥብቀው እንዲይዙና እንዲበረቱ አሳስቧል። ይህንንም ያለው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነው። ለዚህም በተለይ በክርስትና የትንሣኤ በዓል ሰሞን ሦስት ሳምንት ይቆያል የተባለው የቀጥታ ስርጭት እንዲያስተላልፉም ፈቃድ ሰጥቷል፣ አበረታቷልም።

ይህም በሳምንት ቢያንስ የሦስት ሰዓት ጊዜ የተሰጠው ሲሆን፣ ጊዜያዊ ነው።
ይህም መገናኛ ብዙኀን አሰራጮች አካላዊ መራራቅን እንደሚያበረታቱ ያግዛል የተባለ ሲሆን፣ ለማኅበረሰቡ ወሳኝ የሆኑ ክዋኔዎችን ለእይታ መብቃታቸውም ሰው በአካል መሄዱን ይተካለታል ብለው በማሰብ ነው። ይህንንም ለማድረግ በርካታ የቴሌቭዥን መርሃ ግብሮችን ለማጠፍና ለማቆየት ተገደዋል።

የኖረችበት ስርዓት ለገነባትና እንደ ጠንካራ መሠረት ለሚያገለግላት አሜሪካ ጉዳዮ ላይከብድ ይችላል። በአንጻሩ በአፍሪካ እንደውም በኢትዮጵያ እንዲህ ያለ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያሳስባቸው ብዙዎች ናቸው። በየዋህነት ሃይማኖታቸውን እንደሚያክብርላቸው የሚያስቡ ብዙ ዜጎች ቢኖሩም፣ የነገን ስጋት ለማየት አለመቻላቸውንም ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የአዲስ ማለዳ አስተያየት ሰጪ ጠቅሰዋል።

የመብቶችና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማእከል (ካርድ) ዋና ሥራ አስኪያጅ በፍቃዱ ኃይሉ በበኩላቸው ይህን ስጋት ይጋራሉ። ምንም እንኳ ለአማኞች የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ጸሎት መታወጁ ጥሩ ነው ቢሉም፣ በግላቸው ግን እንደሚያሳስባቸው ጠቅሰዋል።

‹‹…ያሳስበኛል፣ መንግሥት ሴኩላሪዝምን በቁምነገር አይወስደውም። የመንግሥት ሚድያዎች እንዲህ ካለ ነገር ቢታቀቡ ጥሩ ነው።›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዜጎች ሃይማኖተኛ መሆንና የመንግሥት ሃይማኖተኛ መሆን የተለያየ ነው ያሉት በፍቃዱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግሮቻቸው ሕዝቡ ሃይማኖተኛ ስለሆነ መንግሥትም እንደዛው ነው የሚል አንድምታ አላቸው። ይህም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

መንግሥት ከሃይማኖት ገለልተኛ መሆን እንዳለበት አጥብቀው ገልጸዋል። እንደውም በሳይንስ ነው መመራት ያለበት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። ሃይማኖቶች በባህሪያቸው አግላይ በመሆናቸውና ተከታያቸው ያልሆነን እንደ ከሃዲ የሚቆጥሩ፣ ከአንዳቸው ሌላውም ሕግጋቶቻው የተለያዩ ስለሆኑ፣ እነዚህ ተቃራኒ ሕግጋት በመንግሥት አዋጅና ፖሊሲ ሊንጸበረቁ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ አዝማሚያዎች ቀስ በቀስ እየተጠራቀሙ ነው በሃይማኖት ውስጥ መንግሥት ገብቶ እንዲገኝ የሚያደርጉት በማለትም ስጋታቸውን አጥብቀው አንስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here