የኮንትሮባንድ እቃዎች ወደ መሀል አገር እንዳይሰራጩ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

0
764

የኮሮና ቫይረስ ወደ አገር ቤት መግባቱን ተከትሎ እየተደረገ ባለው ጥብቅ ክትትል የኮንትሮባንድ እቃዎች በድንበር ላይ በሚገኙ ኬላዎች እየተያዙ ሲሆን፣ የሚያዘው መጠን ምንም እንኳን እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ወደ መሀል አገር እንዳያልፉ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ከሚያዚያ 21 እስከ 26/2012 ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ነገር ግን ወደ መአል አገር የሚደረገው ስርጭት በከፍተኛ መጠን መቀነሱን የገቢዎች ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

እንደ ሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡሚ አባጀማል ገለጻ፣ 72 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በ11 ስፍራዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። እንዲሁም ጅግጅጋ፣ ድሬደዋ፣ ሀረር፣ ሞያሌ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ሑመራ፣ ሞጆ፣ አዲስ አበባ፣ አዋሽ፣ ጅማ እና ሌሎች የጉምሩክ ኬላ ጣቢያዎች ተለይተዋል።
ኡሚ እንዳሉት እነዚህ እቃዎች ቁጥጥሩን ቢያልፉ እና ወደ ኅብረተሰቡ ቢገቡ ጉዳቱ ከባድ ይሆን ነበር። በዚህም ጥብቅ ቁጥጥር በመደረጉ ከተያዙት የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች ውስጥ ተሽከርካሽሪ፣ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶች፣ ጭንብሎች (ማስኮች)፣ ምግብና የምግብ ነክ ቁሳቁሶች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ ቅሽር ቡና፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የተለያዩ ዓይነት ጥይቶች፣ ሺሻና በገቢ እቃ አወጣጥ ታክስ ሳይከፈል ሊጭበረበር የነበሩ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል።

ከዛም በተጨማሪ በአንድ ድርጅት 23 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ከቀረጥና ታክስ ነፃ አስገብቶ ከተፈቀደላቸው የኢንቨስትመንት መስክ ውጪ አገልግሎት ሲሰጥ በመገኘቱ፣ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉንም ኡሚ ጨምረው ገልጸዋል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነቷ ገለጻ የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የገቢዎች ሚኒስቴር የተለያዩ ጥብቅ ቁጥጥሮችን (ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ) በማድረጉ ምክንያት እነዚህ በአገር ላይ ቢገቡ ከፍተኛ የሆነ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ቁሳቁሶች መያዛቸው እና ከዚህ ቀደም ከነበረው የኮንትሮባንድ ሕገ ወጥ ንግድ አለመቀነሱን ጠቅሰዋል። ነገር ግን ቁጥጥሩ በመጨመሩ ምክንያት በሕገ ወጥ መንገድ ገብቶ ወደ ኅብረተሰቡ ይከፋፈል የነበረውን ግን መቀነስ እንደተቻለ ኡሚ አባጀማል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኡሚ አክለው እንዳሉት የኮንትሮባንድ ሥራ በአገርና ሕዝብ እድገት ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ የፌዴራል፣ የመከላከያ እና የክልሎች የፀጥታ አካላት ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመሆን የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለመንግሥትና ለሕዝብ ገቢ እንዲሆን በጋራ እየተሠራ ነው።

በስድስት ቀናት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ከተያዙ እና 70 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶች በተጨማሪ ከ15 ቀን በፊት ማለትም ከሚያዚያ 13 እስከ 18 /2012 ዋጋቸው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን አዲስ ማለዳ ከሚኒስቴሩ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ከተያዙት የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች ውስጥ ጥራቱ ያልተረጋገጠ ምግብና የምግብ ነክ እቃዎች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ ቅሽር ቡና፣ በሐሰተኛ ሠነድና በጎብኝዎች ሥም የገቡ ተሽከርካሪዎች፣ ልባሽና አዳዲስ አልባሳት፣ ሽቶ፣ ሲጋራ፣ የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች እንዲሁም በገቢ እቃ አወጣጥ ታክስ ሳይከፈል ሊጭበረበር የነበሩ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የኮንትሮባንድ እቃዎች የተያዙባቸው ቦታዎች ደግሞ ድሬደዋ፣ ሞያሌ፣ ሀዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ሞጆ፣ አዲስ አበባ፣ አዋሽ፣ ጅማ እና ሌሎች የጉምሩክ ኬላ ጣቢያዎች እንደነበሩ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here