የለይቶ ማቆያዎች ጥበቃ ይጠናከር!

0
587

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተሰራጭቶ እና ወረርሽኝነቱ ተረጋግጦ አገራት የተቻላቸውን የመከላከል እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። በተለይም ደግሞ የወረርሽኙ መነሻ የሆነችው ቻይና አጣዳፊ ምላሽ እና እርምጃ በመውሰድ የወረርሽኙን ግስጋሴ በአጭር ጊዜ እና የተፈራውን ያህል ጉዳት ሳያደርስ በመግታት ወደ ቀደመው እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች።

የቻይና በስፋት ይጠቀስ እንጂ ከቻይና ጋር ረጅም የድንበር አካባቢዎችን የምትጋራው ቬትናም በሥነ ምድራዊ አቀማመጥ ከወረርሽኙ መነሻ ጋር የቀረበች ብትሆንም በዓለም ላይ ካሉ አገራት በሽታውን ተቆጣጠሩት ከሚባሉ አገራት የመጀመሪያዋ ሆናለች። ቬትናም ኮቪድ 19 በቻይና ይፋ ከሆነበት ጊዜ በመጀመሪያዎቹ ቀናት አካባቢ በአገሯ በበሽታው የተጠቃ ሰው ማግኘቷን አስታውቃ ነበር። ነገር ግን ከመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ ቁርጠኛ አማራጭ በመውሰድ እስከ አሁን ድረስ ምንም ሞት ካልተመዘገበባቸው አገራት ምናልባትም ብቸኛዋ አገር ሆናለች። ከዚህም በተጨማሪ ከ20 ቀናት ወዲህ አዲስ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ያልተመዘገበባት አገርም እንደሆነች በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እየተዘገበ ይገኛል።

በተጠቀሱት አገራት የወረርሽኙን መዛመት እና የመዛመት ፍጥነት ለመግታት በየትኛውም መንግሥት መዋቅር ያሉ ተዋረዶች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው የማያጠያይቅ ሀቅ ነው። ከዚህም ውስጥ ታዲያ ማኅበራዊ ፈቀቅታ፣ አፍና አፍንጫን በጨርቅ ወይም በጭንብል መሸፈን፣ በንክኪ የሚደረጉ ሰላምታዎችን መከልከል እንዲሁም ለበሽታው መዛመትና ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የተባሉ የአመጋገብ እና የአኗኗር ዘይቤዎችን በይፋ እንዲከለከሉ ሆነዋል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ሰዎች በቫይረሱ በተያዙ እና መያዛቸው በተተረጋገጠ ወቅት ከወዳጅ ወይም ከቤተሰብ ተለይተው በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ እንዲሁም ከዓለም ዐቀፍ አገራት ወደ አገራቸው የሚመጡ ዜጎች ወይም መንገደኞች በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ማስገደድ አንዱ እና ዋነኛው ተግባር ነበር። በዚህ ኹሉ ጥንቃቄም ውስጥ በሽታውን ከግስጋሴው መቀነስ ቢቻልም፣ እንደ ቻይና ያሉ አገራትን ግን የዜጎቻቸውን ሕይወት ሳያስከፍላቸው አላለፈም፣ እያስከፈላቸውም ይገኛል።

በአገራችን በኢትዮጵያም ዘግይቶም ቢሆን ዓለም ዐቀፍ በረራዎች ተቋርጠዋል፣ አንዳንዶቹ እንዲያውም ከመዳረሻ አገራት በወጣ የጉዞ ክልከላዎች እንጂ በኢትዮጵያ ተነሳሽነት አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ሌላኛው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ መግቢያ እና ከአገር መውጫ ኹሉም ድንበሮች እንዲዘጉ እና ከካርጎ ማጓጓዝ ባለፈ ምንም ዓይነት ሰዎች ጉዞ ሙሉ በሙሉ እንዲከለከል ሆኗል። በአየርም ሆነ በየብስ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎችም ለ14 ቀናት በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያዎች እንዲሰነብቱ እና በቫይረሱ አለመያዛቸው ከተረጋገጠ እንዲወጡ እና ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው።

ይህ ታዲያ የወረርሽኝ መዛመት በጊዜ እንዲገታ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው እሙን ነው። ይሁን እንጂ በተለይም በአውሮፕላን ማረፊያ ከውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ጠባቂዎችን በገንዘብ በመደለል ወደ ለይቶ ማቆያ ሳይገቡ በቀጥታ ወደ ቤታቸው የሚሄዱበት ሁኔታ ይስተዋላል። መንገደኞች በአውሮፕላን ማረፊያ በደረሱበት ጊዜ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲሄዱ የሚደረጉበት አሠራር ቅልጥፍና ያለው ባለመሆኑ፣ መንገደኞች በተጨናነቀ ስፍራ ለረጅም ሰዓታት በመቆየት እንደሚጉላሉ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ የሚደርሷት የቪዲዮ መልዕክቶች ያስረዳሉ።

ከዚሁ ሁሉ እጅግ የከፋው ደግሞ አቅም የሌላቸው እና በተዘጋጁት ሆቴሎች ለ14 ቀናት ከፍለው መቆየት የማይችሉ እንዲሁም በመንግሥት በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ላይ እንዲገቡ የሚደረጉ ሰዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እጅግ የላላ መሆኑን ከሰሞኑ የሚወጡት መረጃዎች ያመላክታሉ። አዲስ ማለዳ ጉዳዮን መንግሥት ችላ ማለት ሳይሆን ከመቼውም በበለጠ ትኩረቱን ሊሰጠው እንደሚገባ ታስገነዝባለች። በተደጋጋሚ ከለይቶ ማቆያ ስፍራዎች አምልጠው ወደ ትውልድ ስፍራቸው በመሄድ ላይ ሳሉ መጥፋታቸው በመረጋገጡ እና በሚደረጉ ክትትሎች የሚያዙ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ወረርሽኙ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲገባ ዓይነተኛ መንገድ በመሆኑ የትኛውም ባለ ድርሻ አካል በለይቶ ማቆያዎች ላይ ጠንከር ያለ ጥበቃ ማድረግ እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ተይዘው ድሬዳዋ በሚገኝ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉ ግለሰቦች ተለይው ከተቀመጡበት ስፍራ ጠፍተው አማራ ክልል ሸበል በረንታ ወረዳ መግባታቸውን እና የወረዳው አስተዳደር ስድስት የሚሆኑትን ግለሰቦች እያፈላለገ መሆኑን በፌስ ቡክ ገጹ ከሳምንታት በፊት መግለጹን ማንሳት ይቻላል። አዲስ ማለዳ ይህን ክስተት በተመለከተ በለይቶ ማቆያዎች ላይ የሚደረገው ጥበቃ በቂ ነው ብላ አታምንም። ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ሌላ ባለ ድርሻ አካል ከእስከዛሬው በበለጠ ጥበቃውን በማጠናከር በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጤነኝነታቸው ተረጋግጦ ካልሆነ በስተቀር አምልጠው እንዳይወጡ ማድረግ ይኖርበታል የሚል ምክር ታስተላልፋለች።

በተለይም ደግሞ ከቀናት ወዲህ በለይቶ ማቆያዎች ውስጥ በሚደረገው የወረርሽኙ ምርመራ የሚገኘው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተዳምሮ፣ ከዛ አምልጠው የሚወጡ ግለሰቦች ወደ ኅብረተሰቡ በመግባት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ጥንቃቄው በይበልጥ እንዲተገበር አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ከኬንያ በመምጣት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኝ የነበረ ሰው አምልጦ በመውጣት ሀላባ ቆሊቶ በክትትል እንደተገኘ ከሰሞኑ መገናኛ ብዙኃን ሲያስተጋቡት የነበረ ጉዳይ ነው። ግለሰቡ በቫይረሱ የተያዘ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ከለይቶ ማቆያ ወጥቶ ሀላባ እስኪደርስ ድረስ ሊበክል የሚችለውን የሰው ብዛት ለመቁጠር የሚያዳግት ነው። ይህ ደግሞ የሚደረገው ቁጥጥር ማነስና አምልጠው በሚወጡ ሰዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አለመኖሩ ማሳያ ነው።

በመሆኑም አዲስ ማለዳ በለይቶ ማቆያዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ከማጥበቁም በላይ አምልጠው በሚወጡ ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ሰትል ታሳስባለች። ምክንያቱም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ወደ ኅብረተሰቡ በሚገባበት ወቅት ቫይረሱ የእርሱ ብቻ መሆኑ ስለሚያቆም ብዙዎችን ሊበክል ስለሚችልና የከፋ ጉዳት ስለሚደርስ ነው። በመሆኑንም ከዚህ ቀደም የተፈጠሩት የማምለጥ ተግባራት እርምት እርምጃ ባለመወሰዱ በቀጣይም ሊኖር ስለሚችል ከወዲሁ ይታሰብብት ስትል አዲስ ማለዳ አቋሟን ታስታውቃለች።

በተለይም ደግሞ በብዛት ከመዲናዋ በወጡ እና በክልል ለይ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ዘንድ ይህ አይት ክስተት መታየቱ እና አምልጠው ወጥተውም ስለ ቫይረሱ እምብዛም እውቀት ወደ ሌለው ማኅበረሰብ ስለሚገቡ ትልቅ የሚሰተው ጉዳት ይከፋል። ስለዚህ በክልል ከተሞች እና ለይቶ ማቆያ ስፍራዎች የክልል የጸጥታ መዋቅሩ በሚገባ እና በተጠንቀቅ ለይቶ ማቆያዎችን እንዲጠብቅ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ከመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ጀምሮ ከአምቡላንስ አምልጦ ከመሮጥ የጀመረው ወደ ለይቶ ማቆያ ያለመግባት ሂደት፣ በኋላም ወደ ማምለጥ ከፍ ብሏል። ይህ ደግሞ የለይቶ ማቆያውን ጥቅም እርባና ቢስ የሚያደርግና ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረገውን ርብርብ በዜሮ የሚያባዛ በመሆኑ ከወዲሁ መላ ሊበጅለት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስታውቃለች።

መንግሥትም ይህን ተረድቶ ይሆናል የሚለውን እና ወረርሽኙን በተመለከተ በቁጥጥር ስር ለማዋል በተለመደው መንገድ ለመሄድ ብቅ ብቅ እያሉ የሚገኙትን እና ከለይቶ ማቆያ አምልጦ የመውጣት እንቅስቃሴዎችን ከወዲሁ መላ ሊያበጅላቸው ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here