የቴሌቪዥን ጣቢያዎች 156 ሚሊዮን ብር ገቢ አጡ

0
1183

በኢትዮጵያ ውስጥ ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱ 13 የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ባጋጠመ የገበያ መቀዛቀዝ 156 ሚሊዮን ብር የሚሆን ገቢ ማጣታቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስተር ማኅበር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የማኅበሩ አባላት ሚዲያዎች በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት ከመጋቢት 4/2012 እስከ ሚያዝያ 19/2012 ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ ከአየር ሰዓት ሽያጭ ያገኙ የነበረውን 156 ሚሊዮን ብር ገቢ ማጣታቸውን አስታውቋል።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሻው ወልደሚካኤል ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጊዜ ወዲህ በተለይም በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ያጋጠመው የገቢ መቀነስ በፍጥነት በመጨመሩ፣ ተቋማቱ ሊቋቋሙት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ የማኅበሩ አባል የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከዚህ በፊት ለሚሰጡት አገልግሎት ክፍያ የሚሰበስቡት በቅድሚያ አገልግሎቱን ሰጥተው እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ሰዓት ግን የአየር ስዓት ሽያጭ እና የንግድ ተቋማት ማስታወቂያ ከመቆሙ ባሻገር ተቋማቱ ለሰጡት አገልግሎት እንኳን የሚገባቸውን ክፍያ መሰብሰብ አልቻሉም ብለዋል።

የብሮድካስት ሚዲያ ዘርፉ አብዛኛውን ገቢውን የሚሰበስበው የአየር ስዓት በመሸጥ እና የንግድ ተቋማት ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ እንደሆነ የገለጹት እንደሻው፣ በአሁኑ ጊዜ የንግድ ሥራዎች በመቀዛቀዛቸው የብሮድካስት ሚዲያዎች ገቢ በእጅጉ መቀነሱን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ሚዲያዎች ችግሩን የሚቋቋሙበት እና ያጡትን ገቢ የሚያካክሱበት መንገድ መፍጠር አንዳልተቻለም እንደሻው ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ተናግረዋል።

ነገር ግን የሚዲያዎቹ ችግሩን ተቋቁመው መቀጠል ለመንግሥትም ሆነ ለኅብረተሰቡ፣ በተለይም ስለኮሮና ቫይረስ መረጃ ለማድረስ አስፈላጊ በመሆናቸው፣ በሥራ ላይ የሚቆዩበትን አቅም ለማመቻቸት ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማስፈጸም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በቅርበት በማማከር ችግሩን ሚዲያዎቹ በራሳቸው መወጣት ስለማይችሉ ለመንግሥት የሚቀርቡ የድጋፍ ጥያቄዎችን እየደገፈ መሆኑንም እንደሻው አንስተዋል።

ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ለብሮድካስት ባለሥልጣን የድጋፍ መጠየቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም አክለው አስታውቀዋል።
ማኅበሩ ቸግሩን ለመቋቋም በሚደርገው ጥረት መሰል ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን የማፈላለግ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝና ለሚዲያዎች አስቸኳይ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አውስተዋል። በሌላ በኩል ከሚዲያ ካውንስል ጋር በመተባበር ሚዲያ ፈንድ ለማቋቋም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የተሳተፈበት ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል።

ማኅበሩ ወደፊት በጉዳዩ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ለመመካከር መዘጋጀቱን አዲስ ማለዳ ከማኅበሩ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ማኅበሩ ወቅቱን መሰረት አድርገው ከመንግሥት የመጡ አማራጮችን ሚዲያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የግብር ቅነሳና ከወለድ ነጻ ብድር እንደሚያቻችላቸው እንደሚጠይቁም ማኅበሩ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ እየታየ ያለው ችግርም እየከፋ በመምጣቱ አንዳንድ ጣቢያዎች እስከመዘጋት እንደደረሱ፣ አንዳንዶች ደግሞ የሠራተኛና የደሞዝ ቅነሳ እያደረጉ መሆኑን እንደሻው አክለው አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር ውስጥ 13 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ጣቢዎች ለሳተላይት አገልግሎት ክፍያ ብቻ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላሉ። ጣቢያዎቹ ከ2 ሺሕ 700 በላይ ቋሚ ሠራተኞችን ያስተዳድራሉ። ለሚያስተዳድሯቸው ሠራተኞችም በየወሩ 41.4 ሚሊዮን ብር ደሞዝ እንደሚከፍሉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር በኢትዮጵያ ውስጥ በግል የሚሠሩ እና ፈቃድ ያላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባለንብረቶች ስብስብ ሲሆን፣ የተመሠረተውም 2010 መስከረም ወር ነበር። አባላቱም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት (ኢቢኤስ)፣ ፋና ቲቪ፣ ዋልታ ቲቪ፣ ቃና ቲቪ፣ አርትስ ቲቪ፣ ጄ ቲቪ፣ አፍሪ ሄልዝ ቲቪ፣ ኦቢኤስ ቲቪ፣ ኤል ቲቪ፣ አሃዱ ቲቪ፣ ዲደብሊው ቲቪ፣ አሻም ቲቪ እና ሀገሬ ቲቪ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here