በቀረጥ እዳ ተይዘው የሚገኙ ንብረቶች የሚመለሱበት አግባብ እንዳለ ተገለጸ

0
810

ከ2008 እስከ 2011 ባሉት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቀረጥ እዳ ምክንያት ተይዘው የሚገኙ ንብረቶች ለባለቤቶች የሚመለሱበት አግባብ እንዳለ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ሚያዚያ 28/2012 በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ንብረቱ ተመላሽ የሚሆነው ንብረቱ ለሦስተኛ ወገን ያልተላለፈ ከሆነ ሲሆን፣ ድርጅቱ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መኖሩ ሲረጋገጥ እና ንብረቱ ተንቀሳቃሽ ከሆነ ዋስትና አቅርቦ መጠቀም እንደሚችልም ተገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በሚል የሚኒስተሮች ምክር ቤት የወሰነውን ውሳኔ መሰረት ተደርጎ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይጀመራል ሲሉ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በዚህ መሠረት የግብር እዳ ምህረት ማድረግ፣ የመክፈያ ጊዜ ማራዘምና የሚከፍሉትን ማበረታታት የተመለከቱ ውሳኔዎች ከሚያዝያ 28 ቀን 2012 ጀምሮ በየቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉም ገልፀዋል። የግብር እዳ ምህረት የመክፍያ ጊዜ ማራዘምና የሚከፍሉትን ማበረታታት በኹለት ምድብ ተከፍሎ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምድብ እስከ 2007 የነበረ ውዝፍ ዕዳ መቀጫ፣ ፍሬ ግብርና ወለድን ጨምሮ ሙሉ ሙሉ እንዲነሳላቸው ተደርጓል።

በኹለተኛው ምድብ ከ2008-2011 ያለው ጉዳያቸው የታየው በሦስት ዓይነት መንገድ ሲሆን፣ የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ የደረሳቸው ግብር ከፋዮች መቀጫ፣ ፍሬ ግብርና ወለድ ያለባቸው ከሆነ የፍሬ ግብሩን 25 በመቶ በአንድ ወር ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 28/2012 ጊዜ ውስጥ ከፍለው 75 በመቶውን በአንድ ዓመት እንዲከፍሉ ተወስኗል። እንደ ላቀ ገለጻም፣ ይህን ተስማምተው በአንድ ወር ውስጥ ደብዳቤ ለሚያስገቡ ግብር ከፋዮች መቀጫና ወለድ እንዲነሳላቸው ተወስኗል።
በሌላ በኩል በአንድ ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ፍሬ ግብሩን ለሚከፍሉ 10 በመቶ ከፍሬ ግብሩ ተቀንሶላቸው መቀጫና ወለድም እንዲቀርላቸው ተደርጓል።

በኹለተኛው ምድብ ውስጥ ገቢያቸውን አስታውቀው የከፈሉ ነገር ግን በተቋሙ ኦዲት ተደርጎ የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ያልደረሳቸው ግብር ከፋዮች በ30 ቀናት ውስጥ በኦዲት የተገኘውን የፍሬ ግብር 25 በመቶ ቅድሚያ በመክፈል ቀሪውን 75 በመቶ በአንድ ዓመት ውስጥ ለመክፈል የክፍያ ጊዜ ውል ተፈራርሞ በውሉ በተገለፀው ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ካጠናቀቀ ቅጣትና ወለድ ይነሳል። በአንድ ወር ውስጥ የፍሬ ግብሩ 100 በመቶ ለመከፈል የሚስማማ ወለድና ቅጣት ከማንሳት በተጨማሪ ከፍሬ ግብሩ 10 በመቶ ይቀነስላቸዋልም ተብሏል።

ሌላው ገቢን አሳውቀው ክፍያ ያልጀመሩትን የሚመለከት ሲሆን፣ ከሚያዚያ 28/2012 ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ አሳውቀው ከከፈሉ በተመሳሳይ የምህረቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲል የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከዛም በተጨማሪ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ውሳኔው ተፈፃሚ የሚሆነው ግብር ከፈዮች የጀመሩትን የታክስ ይግባኝ ወይም በየደረጃው ያሉ ክርክሮችን ካቋረጡ እና በውሳኔው መስማማታቸውን ግብር ለሚከፍሉበት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሲያመልክቱና ሲያሳውቁ ነው ብለዋል።

ላቀ አያይዘውም ውሳኔው የተወሰነበት ዓላማ በኮቪዲ-19 የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለመደጎም ታስቦ ግብር ከፋዮች ወደ ንግድ እንቅስቃሴ ገብተው የምርትና አገልግሎት አቅርቦት እንዳይቋረጥ ለማድረግ፣ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን በሥራ ላይ እንዲያቆዩ እና ግብር ከፋዮች ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው እንቅስቃሴ የጀመሩት ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሆነ አውስተዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም የግብር እዳ ለነበረባቸው ምህረት ማድረግ እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ ግብራቸውን በተገቢው መንገድ ሲከፍሉ ለነበሩ ደምበኞች የማዘናጋት ችግር እንዳይኖር ተብሎ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር ብለዋል። ለዛም በማሰብ በየዓመቱ ተገቢው ግዴታ የሚወጣውን ግብር ከፋይ ለመደገፍ የሚደረገውን ሂደት እውቅና መስጠት እንቀጥላለን ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here