ኮቪድ 19ን ለመከላከል ኢጋድ 25 ሺህ ዶላር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

0
655

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በኢትዮጵያ ኮቪድ 19ን ለመከላከል 25 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ተገለፀ።

ድጋፉ ለሕክምና የሚውሉ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች፣ ጓንቶችና የንጽሕና መጠበቂያዎች (ሳኒታይዘሮች)ን ያካተተ ሲሆን በኢትዮጵያ የኢጋድ የኮቪድ 19 ተወካይ ዶክተር ግሩም ኃይሌ ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ አስረክበዋል።

ዶክተር ግሩም በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንደተናገሩት ድጋፉ በተለይም በድንበር አካባቢዎች ለሚከናወኑ የጤና ሥራዎች የሚውል ሲሆን፣ ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን ያማከለ እንደሆነና በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ድጋፉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ሥራ ያጠናክረዋል ያሉ ሲሆን በድንበር አካባቢዎች በተለይም ከስደተኞችና ተፈናቃዮች ጋር ተያያዥነት ላላቸው ተግባራት እንደሚውልም ገልፀዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል ትብብር እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ሚኒስትሯ፤ ከዚህም አንጻር ተቋሙ ላደረገው አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎች የኢጋድ አባል አገሮች እንደሚደረግ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ መገለፁን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here