በአፍሪካ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴን ማገድ አኅጉሪቱን በወር 65 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳጣት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
ይህም ኪሳራ ከአኅጉሪቱ 2 ነጥብ 5 በመቶ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ጋር የሚስተካከል መሆኑን ነው በአፍሪካ የመንግሥታቱ ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ሪፖርት ያመለከተው። በአሁኑ ወቅት በትንሹ 42 የሚሆኑ የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸው ተገልጿል።
አገራቱ የጣሉት ገደብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ ከባድ የሆነ የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንደሚፈጥር ነው ሪፖርቱ የገለፀው። የአፍሪካ አገራት ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች ዋጋ ማሽቆልቆልና ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት መፈጠር የኢኮኖሚ ቀውሱ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል ነው የተባለው።
ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012



