የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ 44 ግለሰቦች በገንዘብ ተቀጡ

0
632

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ተሰባስበው ጫት ሲቅሙ እና ሲጋራ ሲያጨሱ የነበሩ 44 ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ከ3 ሺሕ እሰከ 3400 ብር ሲቀጡ ቀሪው አንድ ግለሰብ የሦስት ወር እስራት የተፈረደበት መሆኑ ተገለፀ።
መንግሥት በዓለማችን ብሎም ኢትዮጵያ ላይ ሰጋት እየፈጠረ ያለውን የኮቨድ-19 ኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል፣ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል። በአዋጁም አራት እና ከአራት በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ ተሰባስቦ መገኘት የተከለከለ መሆኑ ተቀምጧል። ይሁን እንጅ በቸልተኝነት እና በመዘናጋት የወጣውን አሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ክፍተቶች ይታያሉ።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መርማሪ ሳጅን አያሌው ጌታቸው መንግሥት ያወጣውን የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ በክፍለ ከተማው ስር በሚገኙ ሰባት ፖሊስ ጣቢያዎች የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም አዋጁን ጥሰው በሚገኙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ክልከላውን በመጣስ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙትን በተመለከተ እንደተናገሩት፣ ተሰብሰበው ጫት ሲቅሙ እና ሲጋራ ሲያጨሱ የነበሩ 44 ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ከሦሰት ሺሕ እሰከ ሦሰት ሺሕ አራት መቶ ብር የተቀጡ ሲሆን፣ ቀሪው አንድ ግለሰብ የሦሰት ወር እስራት የተፈረደበት መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በጥፋት ላይ የተገኙትን መረጃዎችን በማሰባሰብ 14 መዝገቦችን በማደራጀት በተለያየ ጥፋት ላይ የተገኙ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አሰታውቀዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ወረርሸኝን ለመከላከል፣ለመቆጣጣርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ታስቦ የወጣ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፣ የአዋጁን ዓላማ በመረዳት ኅብረተሰቡ ክልከላ ከተደረገባቸው ደርጊቶች ራሱንና ሌሎችን በመጠበቅ ለፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች የዕለት ተዕለት ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here