ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል

0
651

በምርቶች እና ሸቀጦች ላይ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ።
ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር መደበኛ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ ለወቅታዊ ዋጋ ንረት ምክንያት የሚሆነው በንግድ ዘርፉ ላይ የመንግሥት ተቋማት ቁጥጥር መላላት ነው ተብሏል። ስለሆነም ኅብረተሰቡና የንግድ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ዘላቂነትና ተከታታይነት ያለው የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እና የባለሙያዎችን የሥራ እንቅስቃሴ መከታተል እንዲሁም መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
ከዚያም ባለፈ በሕገ ወጥ ንግድ ኮንትሮባንድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በመሥራት የተወሰዱ እርምጃዎችን በመገምገም የተገኘውን ውጤት እየለኩ መሄድ እንደ አንድ ቁልፍ ተግባር መውሰድ እንደሚገባም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ከዛም በተጨማሪ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ውጪ ንግድ ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት በምርቶች እና ሸቀጦች ላይ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ጎን ለጎን አቅርቦት ማሻሻል እና ትስስር መፍጠርም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ይገባልም ሲሉ አክለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here