በአዲስ አበባ የደራው የሐሰተኛ ሰነዶች ገበያ

Views: 1929

በአንድ የማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ ባልደረባ ለሆነችው ለ22 ዓመቷ ሜላት አስመላሽ (ሥሟ የተቀየረ) ዳጎስ ያለ ክፍያ የሚያስገኝ የማስታወቂያ ሥራ ማግኘቷን እንዲሁ በቀላሉ የምታልፈው አጋጣሚ አልነበረም። ለወራት በኮንትራት በምትሠራበት የማስታወቂ ድርጅት ሥራውን ሊሰጣት መስማማቱ መልካም ዜና ቢሆንም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር(‘ቲን’) ከሌላት 30 በመቶ እንደሚቆረጥባት ስታውቅ ግን አቋራጭ መፍትሔ ካልፈለገች ገቢው እንዳሰበችው እንደማይሆን አምናለች።

ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት በማምራት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥሯን ለማውጣት የሔደችው ሜላት የቀበሌ መታወቂያ በመጠየቋ ተወልዳ ካደገችበት አካባቢ መልቀቂያ በማምጣት የአዲስ አበባ መታወቂያ መሞከሯን ተያይዛዋለች።

በቤት ቁጥሩ መታወቂውን የሚያወጣለት ሰው በማጣቷ መፍትሔ ፍለጋ ያነጋገረቻቸው ጓደኞቿ ደጋግመው ተመሳሳይ የሆነውን በማሠራት ትገላገል ዘንድ ያሳምኗታል። ለዚህም አገልግሎት ከ700 እስከ 1500 ብር ብቻ መጠየቁ ልታገኝ ካለው ገቢ ጋር በማነፃፀር ጊዜ ሳትሰጥ ማፈላለግ ትጀምራለች።

በቅድሚያ የከፈለችው 700 ብር አይበቃም ጨምሪ ተብላ በተደጋጋሚ የተጠየቀችው ሜላት በብዙ ልምምጥ ሕገ ወጥ መታወቂያውን በመጨረሻ ያገኘች ሲሆን እሱን ተከትሎ ባወጣችው ቲን መሰረት ካገኘችው ገቢ ላይ ኹለት በመቶ ብቻ ግብር በመክፈል ሐሳቧ መሳካቱን ትናገራለች። ነገር ግን ይህ የማይታደሰው መታወቂያ አንድ ቀን መዘዝ ያመጣብኛል በሚል ፍርሃት ውስጥ ለወራት መብሰልሰሏን ግን አትደብቅም።

በቀበሌ መታወቂያ የማያበቃው የሕገ ወጥ ሰነዶች ሰንሰለት ወደ ተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰርጎ መግባቱ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል። በተለይም በኮንስትራክሽን፣ በትምህርት፣ በሕክምና፣ በተለያዩ አስተዳደራዊ ደብዳቤዎች፣ የቤት እና የተሸከርካሪ ማረጋገጫዎች እንዲሁም የመንጃ ፈቃድን ጨምሮ የተለያዩ የብቃት ማረጋገጫዎች በዋናነት የሚሠሩ ሰነዶች ናቸው። ለዚህም እንደየማስረጃዎቹ ዓይነት የሚጠይቀው ዋጋ፣ ለማዘጋጀት የሚጠይቀው ጊዜ እንዲሁም የመንግሥት አካላት ተሳትፎ ይለያያል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ለሦስት ዓመት ትምህርቱን ተከታትሎ ያቋረጠው ዮሐንስ ዳኜ (ሥሙ የተቀየረ) ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት የተደላደለ ሕይወቱን መምራት ከጀመረ ሰነባብቷል።

ወደዚህ ሥራ የገባበትን አጋጣሚ ሲያስታውሰው “አንዲት ከውጭ አገር የመጣች ሴት የመጣችበት የአንድ ወር የእረፍት ጊዜ ቢጠናቀቅም ሌላ አንድ ወር ጨምራ አገር ቤት መቆየት በመፈለጓ የተሰጣትን ለአንድ ወር የምታራዝምበትን መንገድ አሳየችኝ” ይላል።

“በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ትንሽ ለመቆየት ሲፈለጉ የሚጠቀሙትን የሕመም እረፍት ፈቃድ አመሳስዬ እንድሠራላት, ከዚህ ቀደም ያሰራችውን ማስረጃ ይዛ መምጣት ተነጋገርን። ሥራውም በኮምፒውተር ላይ የሚያልቅ ቀላል በመሆኑ ላፍታም ሳላመነታ ዕድሌን ተጠቀምኩ።”

ለማንኛውም ሕገ ወጥ ሰነድ ኅትመት መሰረታዊ የሆነው የማኅተም ሥራ እንደሆነ የሚናገረው ዮሃንስ, የመጀመሪያ ደንበኛው እራሷ ማኅተም የሚሠሩ እና ፒያሳ አካባቢ በተለምዶ ዶሮ ማነቂያ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ወዳሉ ሰዎች ወስዳ እንዳሳየቸው ይናገራል። አካባቢው ብዙ የሕገ ወጥ ሰነዶች ሥራ የሚስተዋልበት እንደሆነም ይናገራል። እሱም በቀላሉ የተግባባቸው እነዚህ ወጣቶች የአንድ ጊዜ ሥራውን ከመሥራት ባለፈ ደንበኝነታቸውን በማጠናከር ሕገ ወጥ ሰነድ ማዘጋጀቱን እንደተማረ ይገልፃል።

በዚህ የሕገ ወጥ ሰነድ ተጠቅማ ወደ አገር ቤት ስትመጣ እረፍቷን የምታራዝመው ወጣት, በዘንድሮ ዓመት በለስ ቀንቷት እሱም እንደቀላል በሠራው ሰነድ 3 ሺሕ ብር ክፍያ ተቀብሎ እስከ አሁን እንጀራዬ ወደሚለው ሥራ ተቀላቀለ። እንደዋዛ በገባበት በዚህ ሥራ ለሦስት ዓመት ኑሮውን ከመምራቱም ባሻገር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በማቋረጥ በከተማዋ አለ የተባለ የሕንፃ ተቋራጭ ሆኖም እየሠራ ይገኛል።

የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማስረጃዎች
የሕንፃ ተቋራጭነት ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈለጉ መስፈርቶችን ለማሟላት የማይችሉ ግለሰቦች ፈቃዱን ለማግኘት የሚያስፈልጉ የተለያዩ ማሽነሪዎች፣ ተሸከርካሪዎች፣ ባለሙያዎች እና የተለያዩ የቅጥር ውሎች ሳይኖራቸው ሕገ ወጥ ሰነዶችን በመግዛት ፈቃድ እንደሚያወጡ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ የኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት ይናገራሉ።
ለዚህም በተለይ ከጥቅም ውጪ ሆነው በየመንገዱ በቆሙ መኪኖች የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር (ሊብሬ) በመውሰድ እና ወደ ሥማቸው በማስተላለፍ ፈቃድ ለማውጣት የሚጠየቀውን ተሽከርካሪ መስፈርት ለማሟላት የሚጠቀሙበት ሲሆን ለዚህ አገልግሎትም እንደመኪናው ዓይነት እስከ 100 ሺሕ ብር ይጠየቃሉ።

ፈቃዱን የሚሠጠው የኮንስትራክሽን ባለሥልጣንም ተቋራጩ በእርግጥም እነዚህን ግዴታዎች በእርግጥም አሟልቷል ወይ የሚለውን በአካል ሔዶ አያረጋግጥም። አልፎ አልፎ በአካል ሔዶ የማረጋገጥ ሥራ እንኳን ሲሠራ ብቃታቸው እና ጥራታቸውን ከመፈተሽ ይልቅ በሰነዶቹ ላይ ብቻ በመመስረት ፈቃድ ይሰጣል።

በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት ዳዊት ብሩክ እንደሚሉት ተቋሙ በሚያደርጋቸው ድንገተኛ ክትትሎች አስፈላጊ መስፈርቶችን ያላሟሉ ድርጅቶችን በመለየት በድኅረ ገጻቸው ላይ እንደሚሳውቁ ቢገልፁም ፈቃድ በማውጣት ወቅት ግን እቃዎቹ መሟታቸውን በአካል እንደማያረጋግጡ ያምናሉ።

“አንዳንዴ ያቀረቡትን ሰነዶች አጠራጣሪ ከሆኑ በአካል በመሔድ ክትትል የምናደርግ ሲሆን ለዚህም ከማገድ ጀምሮ የሰነዶቹ መጭበርበር ከተረጋገጠም ፈቃድን እስከመሰረዝ እንደርሳለን” ይላሉ።

የባለሥልጣኑን ማኅተሞች እና ልዩ ልዩ የማረጋገጫ መንገዶች ለናሙና ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች በመበተን ቁጥጥርና ቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ቢሠሩም የሕገ ወጥ ሰነዶችን ግን ለማዳከም እንዳልተቻለ ይናገራሉ። በተቋሙ ፈቃድ ያወጡበትን መኪና ፈቃድ ካወጡ በኋላ መሸጥ፣ በሐሰተኛ ሰነድ የባንክ ደብዳቤ ማቅረብ፣ ሐሰተኛ የትራንስፖርት ባለሥልጣን የእድሳት ደብዳቤ ማቅረብ ባለሥልጣኑ በተደጋጋሚ የሚያገኛቸው ወንጀሎች ናቸው። ሰነድ በማጭበርበር ክስ የሚመሰረትባቸውና በአስተዳደር በኩል ተወስኖ ቅጣት የሚጣልባቸው እንደሉም ዳዊት ይናገራሉ።

ተጫራቾች ለጨረታ ሲቀርቡ ሙሉ ሐሰተኛ ሰነዶች ይዘው ይቀርባሉ ያሉት ዳዊት ለማረጋገጥ ወደ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣኑ የተላኩ ሰነዶች በመለየት ከአንድ እስከ ኹለት ዓመት የእድሳት ክልከላ ይጣልባቸዋል ብለዋል። ባለሥልጣኑ በፌደራል ደረጃ 19 ሺሕ 410 ፈቃዶችን የሚያስተዳድር ሲሆን ከዚህ ውስጥ በአግባቡ እያሳደሱ እና ፈቃዳቸውን በዘለቄታዊነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን ከ7 ሺሕ እንደማይበለጡ ዳዊት ይናገራሉ።

በጨረታ ወቅት የሚያቀርቡ ሰነዶች በግንባታው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጨረታ አካሔዶች ላይም በሰፊው ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ሰነዶቹን የሚያዘጋጁት ወጣቶች ይናገራሉ።

የሥራ ልምድ ማስረጃዎች
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በያዝነው ዓመት ባወጣው ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን የቀጥታ ሥራ ፈላጊ እና 7 ሚሊዮን በተለያየ መንገድ ሥራ ፈላጊ እንዳለ አረጋግጧል። ይህ በሆነበት ሁኔታ አብዛኛው የሥራ ማስታወቂያ የሥራ ልምድ መጠየቁ ሥራ ማግኘትን አስቸጋሪ ያደርገዋል። በተጨማሪም በተለይ ገና ወደ ሥራ የሚገቡ ወጣቶች በሥራ ፍለጋ እና እጦት መዛል ውስጥ ስለሚሆኑ ሕገ ወጥ ሰነዶችን በማሠራት ጠባቡን የሥራ ማግኘት ዕድላቸውን ለማስፋት መሞከራቸው የዕለት ተዕለት ሀቅ ነው።

በተለይም በፋብሪካ ሥሞች የሚፃፉ የሥራ ልምዶች እንደሚበዙ እና የፕላስቲክ አምራች ፋብሪካዎች ሥም በብዛት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አዲስ ማለዳ ያደረገችው ዳሰሳ ያሳያል።

አብዛኛዎቹ ቀጣሪዎችም የተወዳዳሪዎቻቸውን የቀድሞ አሰሪ ወደ ተባሉት ድርጅቶች በመቅረብ ያለማጣራታቸው ወይም አልፎ አልፎ በሚደረጉ ማጣራቶች የሰነዶቹን ሐሰተኛነት ቢያረጋግጡም ለሕግ አሳለፎ ከመስጠት ይልቅ ከውድድር በማግለል ብቻ የሚያልፉት በመሆኑ ሐሰተኛ ሰነድ ተጠቃሚዎች ያለምንም ስጋት እንዲጠቀሙ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በያዝነው አመት ባወጣው ጥናት በየዓመቱ ሶስት ሚሊዮን የሥራ ፈላጊ እና 7 ሚሊየን በተለያየ መንገድ ስራ ፈላጊ እንዳለ አረጋግጧል፡፡

የትምህርት ማስረጃ
የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ተንሰራፍተው የሚገኙት እነዚህ የሕገ ወጥ የትምህርት ማስረጃ መፈልፈያ ሱቆች በተለይም በፒያሳ፣ ቦሌ፣ ገርጂ፣ አራት ኪሎ እና በመሳሰሉት አካባቢዎች መገኘታቸውን አዲስ ማለዳ በአካል ተገኝታ ለማረጋገጥ ችላለች።

በመደበኛው የከፍተኛ ትምህርት ስርዓት ውስጥ ገብተው ውጤት ላይ መድረስ ያልቻሉ ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ክፍያ በመክፈል አንድም ሙሉ በሙሉ ሐሰተኛ ማስረጃ በማሠራት ወይም በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ በሚገኙ ሠራተኞች ትብብር ፋይል በማስከፈት ሰነዱን ያገኛሉ።

በብዛትም ወደ ተለያዩ የውጪ አገራት የሚሔዱ ሰዎች የትምህርት ማስረጃውን በማሠራት የሚሔዱበት አገር የሚጠይቀውን መስፈርት ለማሟላት ይጠቀሙበታል። ይህ አገልግሎት የሚሰጠው የዲጂታል ኅትመት በሚሠሩ፣ የማኅተም መቅጫ ቤቶች እንዲሁም የጽሕፈት አገልግሎትና ተያያዥ ሥራዎች መስጠትን ሽፋን ባደረጉ አነስተኛ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ ነው።

ለእነዚህ የትምህርት ነክ ማስረጃዎች በቀጥታ ተባባሪ ከሆኑት የመንግሥት አካላት ውስጥ ዋነኛው የትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነ ይነገራል። በተለይም በሕይወት የሌለ ሰውን የሰነድ ታሪክ በመውሰድ የሕገ ወጥ ሰነድ ፈላጊውን ሥም በማስገባት መሥራት ነው። የትምህርት ማስረጃውን የሚፈልገው ሰው እሱ በሚገልፀው የትምህርት ደረጃ የተማረ የሚያውቀውን የሟች ግለሰብ ሙሉ መረጃ ይዞ መሔድ ብቻ ይጠበቃል።

በኋላም ሰነዱን የሚሠሩት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመሔድ በሕይወት የሌለውን ሰው ከመረጃ ቋት ውስጥ በመሰረዝ አዲስ በሚሠራው ሰው የመረጃ ልውውጥ የሚካሔድ ሲሆን ለዚህም ከ20 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ብር ይጠየቃል።

በቀላሉ እና በተደጋጋሚ ከሚሠሩ የትምህርት ማስረጃዎች አንዱ የውጤት ግብረ መልስ (Grade Report) ነው። ይህም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲ ማኅተሞች ያላቸው ሕገ ወጦቹ በመረጡት መንገድ የሚሠሩ ሲሆን አገልግሎቱን የሚገዙት ግለሰቦች ተቋማቱን መምረጥ እንደማይችሉ ዮሃንስ ያስረዳል።

በዚህ አገልግሎት በተለይም ከ35 እስከ 45 ዓመት ያሉ ተጠቃሚዎች ቁጥር በርካታ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያደረገችው ቅኝት ያሳያል። አገልግሎቱ እንደ ማስረጃ ፈላጊው አቅም ሁኔታ እየታየ ክፍያ የሚጠየቅበት ሲሆን ከፍተኛው የገንዘብ ጣሪያም 100 ሺሕ ብር አካባቢ ይዳሳል፣ እንደ ዮሃንስ ምስክርነት።

የሕክምና ማስረጃዎች
ወደ ተለያዩ የውጪ አገራት ለሚደረጉ ጉዞዎች ዕድሜን ለማሻሻል ሲባል በሰፊው የሚዘጋጀው ሕገ ወጥ የልደት ካርድ በዋናነት በሕክምናው ዘርፍ የሚሠራ ሰነድ ነው፤ የማሠሪያ ዋጋው እስከ 5 ሺሕ ብር ይደርሳል። ዮሃንስ ከአንድ ዓመት በፊት ያጋጠመውን በክትባትና በልደት ሰርተፊኬት መካከል የአንድ ቀን ልዩነት ያጋጠማት ወጣት ወደ ውጪ አገር የመሔድ ዕድሏን ልታጣ በነበረበት ወቅት ካርዱን አስተካክሎ እንደሠራላት ለአዲስ ማለዳ የሐሰተኛ ማስረጃ የሥራ ገጠመኙን አካፍሏል። ዩሃንስ የሕክምና ተቋሞቹ የልደት ካርድ ላይ የሚያጋጥሙ ስህተቶችን ለማስተካከል ወይም የጠፋ የልደት ካርድን እንደገና ለማውጣት ያለው አሠራር ለዚህ እንደሚዳርጋቸው ጨምሮ ተናግሯል።

አብዛኛው የሕክምና ማስረጃ ቀላል በሚባል መልኩ የሚሠራ መሆኑንም ይናገራል። በተለይ በአነስተኛ ገንዘብ የሚዘጋጀው የሐኪም የእረፍት ትእዛዝ የግል እና የመንግሥት ሆስፒታሎችን ማኅተም በማስቀረፅ ይገለገሉበታል። አብዛኛዎቹ አገልግሎት ፈላጊዎቹ ከሳምንት በላይ እረፍት የሚፈልጉ ሲሆኑ የሚፈልጉትን የቀን ርዝመትና የሕመም ገለፃ ራሳቸው እንዲጽፉ የሚደረግ ሲሆን ለዚህም ከአንድ መቶ እስከ አምስት መቶ ብር ክፍያ ይጠየቃሉ።

የቀበሌ መታወቂያ
ዮሃንስ እንደሚለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክፍለ ከተሞች እና ቀበሌዎች መረጃቸውን በኮምፒውተር ማመሳከር ሥራ በመጀመራቸው የመታወቂያ ሥራን በቀጥታ ከመሥራት ይልቅ የመሸኛ ደብዳቤውን በማዘጋጀት እንደሚሠሩ ይናገራል። ሆኖም ይህንን ተቋቁመው የቤት ቁጥር በመፍጠር ሕገ ወጥ መታወቂያ የሚሠራ ሲሆን አንዳንዴም ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር ሕጋዊ መታወቂያ በማውጣት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ሰዎች የአዲስ አበባን መታወቂያ ለማግኘት ሲሉ ይህንን መንገድ በሰፊው የሚጠቀሙ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኤርትራዊያን ከ3 ሺሕ እስከ 5 ሺሕ ብር የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ የአዲስ ማለዳ ቅኝት ያመላክታል።

ማኅተም አንድ
ማኅተም ለመቅረፅ ‘ኮሬል’ ሶፍትዌር በመጠቀም በማኅተሙ ላይ የሚገኙ ሎጎ እና የፊደል አጣጣል በጥንቃቄ የማኅተሙን ቅርጽ (ክብ፣ አራት ማዕዘንና ሦስት ጎን) በጠበቀ መልኩ ይሠራል። የቅርፁ ጉዳይ ሲያልቅ የፊደል እና የዓርማ መመሳሰል ላይ በጥንቃቄ ለመሥራት ይቻላል። ማኅተሙን በቤት ውስጥ ለመሥራት ኹለት ከ5 ሴንቲ ሜትር ያላነሱ ወፍራም መስታውቶች፣ ብርሃን አስተላላፊ ፕላስቲክ፣ ኹለት ፍሎረሰንት መብራቶች፣ የማኅተም ፊደሎቹን እና ቅርፁን የሚሠራው ወፍራም ፕላስቲክ መሰል ኬሚካል ዋና ዋና ግብዓቶች ናቸው። በአንድ ጊዜ ላይሳካ የሚችለው ቀረፃ እስከ አምስት ጊዜ በሚደረግ ሙከራ ይጠናቀቃል። ማኅተም ለማሠራት ሌላኛው አማራጭ ሕጋዊ የማኅተም ቀራጮች ማተሚያ ቤቶች ሲሆኑ የንግድ ፈቃድ ካላየን አንሠራም ብለው ቢያቅማሙም በትውውቅ እንዲሁም እስከ 500 ብር በማስከፈል አገልግሎቱን ይሰጣሉ። ይህ በፒያሳ አካባቢ እንደልብ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ በደረገችው ቅኝት ለመታዘብ ችላለች።

እንደ ማጠቃለያ
የወንጀል ሕጉ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ መታወቂያ፣ የሕክምና ምሥክር ወረቀት የመሳሰሉትን ሰነዶች በሚያዘጋጁ ግለሰቦች ላይ ከ3 ወር እና ከ10 ዓመት በማይበልጥ እሥራት የሚያስቀጣ ሲሆን መንግሥታዊና ወታደራዊ ሰነዶች የሙስና ወንጀል ሲሆኑ እስከ ዕድሜ ልክ የሚያስፈርድ ይሆናል ሲሉ የፀረ ሙስና ዐቃቤ ሕግ ሆነው ያገለገሉት ጠበቃው ይድነቃቸው ኃይሌ ይናገራሉ።

ይህ ወንጀል ዋስትና መብት የሚያስነፍግ ነው የሚሉት ይድነቃቸው ማኅተም፣ የብር ኖቶች፣ ቼክ፣ ሲፒኦ፣ ቲተር እና ተያያዥ ኅትመቶች በሕገ ወጥ መንገድ ሲያትም የተገኘ ወይም ሲጠቀም የተያዘ ከአምስት ዓመት ያልበለጠ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ይናገራሉ። ይህ ድንጋጌ በሕጋዊ መንገድ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩ ማተሚያ ቤቶችም እንደሚሠራ የሚናገሩት ባለሞያው እነዚህን ኅትመት መሥሪያ ቁሳቁሶች በሕጋዊነት ፈቃድ ያወጣባቸው ግለሰብም ሕጋዊ በሆነ መልኩ እስካላስወገዳቸው በእርሱ መሣሪያዎች እስከተሠራ ድረስ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ይናገራሉ።

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠራ ግለሰብ ሐሰተኛ ሰነዶች ሲሠራ ወይም ሰርቶ ቢገኝ ከ5 እስከ 25 ዓመት ቅጣት ይጣልበታል። ይሁንና የደኅንነት ጉዳይ፣ በሕዝብና በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ሰነዶች ሲሆን እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ሊከብድ እንደሚችል የሚነገሩት ይድነቃቸው, ወንጀሉ ሆን ተብሎ ሳይሆን በቸልተኝነት እና መደረግ የነበረበት ጥንቃቄ ባለመደረጉ የመጣ ወንጀል ከሆነ ግን እስከ ሦስት ዓመት ድረስ እንደሚያስቀጣ አብራርተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚቀርቡ ሐሰተኛ ሰነዶች መኖራቸውን የሚናገሩት ይድነቃቸው የፍትሕ ስርዓቱ ላይ ከሚያጠሉት ጥቁር ጥላ ባሻገር ጠበቃ እና ደንበኛ መካከልም ከባድ የሆነ ያለመተማም ስሜት እንደሚፈጥር ይናገራሉ።
የሌላውን ጥቅም በመንካት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረገው ይህ ተግባር በእውነት ላይ በተመሠረቱ ግለሰቦች ላይ ፍርድ ያጓድላል ይላሉ።

በተጨማሪም በግንባታው ዘርፍ ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድርን በመፍጠር በግንባታው ላይ የጥራት ችግር፣ ከግብር (ታክስ) በተያያዘ ሰነዶችን በማሠራት ያልከፈሉትን ግብር ከፍለናል ከዛም አልፎ ተመላሽ የሚጠይቁ፣ የትምህርት ማስረጃ የሚያሠሩት በአግባቡ ተምረው የተመረቁ ተማሪዎችን ዕድል ይዘጋሉ፣ መንጃ ፈቃድም እንዲሁም በሰው በአገርና በንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። በአጠቃላይ የሐሰተኛ ሰነዶች ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ የማይሰጠው ከሆነ በአገር ምጣኔ ሀብትና ደኅንነት ላይ ከባድ ተግዳሮት እንደሚደቅን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com