የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና ምሁራኑ – በዘመነ ኮሮና

0
1056

ተቋማት ሕጋዊ ሰዎች ናቸው። እንደ ግለሰብ ስኬትን እንዲሁም ውጣ ውረድን፤ አንዳንዴም ውድቀትን ያስተናግዳሉ። ከዚህ መካከል ስኬታቸው ለብዙዎች በተምሳሌትነት ሊጠቀስ የሚችል ተቋማትን እናውቃለን። ዛሬም አዲስ ማለዳ ብዙዎች ቢያውቋቸው ብዙ ይማሩባቸዋል ያለችውን ተቋም ቃኝታለች፤ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ። ሳይንስ አካዳሚው በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የወሰደውን ድረሻም በወፍ በረር ተመልክታለች።

ምሥረታ
ጉለሌ አካባቢ የሚገኘው የአካዳሚው ጊቢ አበባ ይዞ ከሚጠብቅ ሰው በላይ እንግዳን በራሱ ዜማ ይቀበላል። ጥንቃቄ የተመላ አያያዙ የአንድ ባለሀብት ጊቢ እንጂ ለብዙዎች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው ብሎ ለማመን ነጋሪን ይፈልጋል። ጊቢው በቀደመው ጊዜ ለኢትዮጵያ በእውቀትና ምርምር ሥራ ላይ እኔ ነኝ ያለ አስተዋጽኦ ያበተረከቱት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ቤት ነበር። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፤ ተገብቶት ይህን ቤት መቀበሉ አንድም በቅርስነት ጠብቆ እንዲቆየው አንድም መልሶ ሞገስን እንዲላበስበት አስችሎታል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከ11 ዓመታት ገደማ በፊት የተወሰኑ ምኁራን ‹‹ኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ያስፈልጋታል›› በሚል ሐሳብ የተጸነሰ ነው። ከጥንስሱ ጀምሮ የነበሩትና አሁንም ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ፤ ለአዲስ ማለዳ እንደነገሯት፤ ማእከሉ በይፋ ከመመሥረቱ በፊት በበርካታ ምኁራን ብዙ ውይይት ተደርጎበታል። ‹‹ምን በምን አኳኋን ሊሠራ ይችላል? ምን ውጤትስ ሊገኝ ይችላል?›› የሚለውን ጥያቄ ከመመለስ ጀምሮ አንድን ማእከል እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የሚታለፈውን ሁሉ አልፏል።

በምሥረታው ሂደት የአካዳሚው መተዳደሪያ ደንብ ወጣ፣ ለአባላት የሚኖረው መስፈርት ተለየ ምስረታውም በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 ይፋ ሆነ፤ የመጀመሪያዎቹ አባላት ተመዘገቡ። ዓላማውም እንዲህ የሚል ነበር፤ ‹‹በኢትዮጵያ የሳይንስን ባህል ማሳደግ፣ የምርምር ባህል እንዲያድግ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንዲሁም የሳይንስና አጠቃላይ የእውቀት ስርጭትን ለማገዝና አገር የምትጓዝበትን የእድገት ጎዳና በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግ።››

ሳይንስ
በአጋጣሚ ወይም በተደጋጋሚ ከመስማት የተነሳ ይሆናል፤ ሳይንስ ሲባል የብዙዎች ትኩረት የተፈጥሮ ሳይንስ ነው፤ ማኅበራዊ ሳይንስ ብዙውን ጊዜ ይዘነጋል። ፕሮፌሰር ማስረሻ እንዳሉት ታድያ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሲቋቋም ሁሉንም የእውቀት መስኮች እንዲያቅፍ ሆኖ ነው። በዚህም ማኅበረሰባዊ ሳይንስ፣ የሰባዕታት /Humanities/ ሳይንስ እንዲሁም ሥነጥበባት በአንድ አውድ ታድመዋል።

ይህ ማለት የተፈጥሮ ሳይንስን ለማሳደግ ከሚደረጉ ጥረቶች ባሻገር አካዳሚው ማኅበራዊ ዘርፍን የሚዳሳሳ፤ ሥነጥበብን የሚያግዝ እንቅስቃሴ ያደርጋል። ለዚህ አንዱ ማሳያ የሥነጥበብ ማxeከል በውስጡ መከፈቱ ነው። ስዕል፣ ቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ሥነጽሑፍ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዲደረግባቸው ማxeከሉ ዕድሉን አመቻችቷል።

ተምሳሌትነት
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ማኅበራዊ እንዲሁም ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎችንና ተናጋሪዎችን ከተመልካችና አድማጭ ጋር መደበኛ በሆኑ ወርሃዊና በየአስራ አምስት ቀኑ በሚደረጉ መድረኮች ያገናኛል። ታድያ በእነዚህ መድረኮች እንደ ርዕሰ ጉዳዩ የታዳሚና የመገናኛ ብዙኀን ትኩርት ከፍና ዝቅ ቢልም፤ ክዋኔው አልታጎለም። ‹‹ብዙ ሰው አልመጣም ማለት ጉዳዩ ትንሽ ነው ማለት አይደለም። የእኛ ዋና ትኩረት የምናነሳቸው ጉዳዮች ምን ያህል ለአገር ይጠቅማሉ የሚለው ነው። ብዙ ሰው መጥቶ ቢያይ ደስ ይለናል፤ ጥቂቶች ቢመጡም እናስተናግዳለን።›› አሉ፤ ፕሮፌሰር ማስረሻ።

‹‹በትንሹ ታምነሃልና…›› እንዲል፤ ማxeከሉ ከጊቢ አያያዙ ጀምሮ ጥንቃቄን የተላበሰ መሆኑ ያስታውቃል። በአንጋፋና ታላላቅ ምኁራን ከተቋቋመው ማእከል ባለፈ ወጣቶች ሊሳተፉበት የሚችሉበትም የወጣቶች የሳይንስ አካዳሚ እንዲቋቋም መሆኑም ብዙ እርምጃ የመራመድ ያህል የሚቆጠር ስኬት ነው።

ሳይንስ አካዳሚ እንዲህ ጥንቅቅ ያለ ተቋም እንዲሆን ያስቻለው ምን እንደሆነ ለፕሮፌሰር ማስረሻ አዲስ ማለዳ ያቀረበችው አንዱ ጥያቄ ነው። እርሳቸው እንዳሉት ማእከሉ ሲቋቋም ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳቱና አባላቱም በየሙያቸው ላቅ ያለ ድርሻ ያበረከቱ መሆናቸው፤ አልፎም ከምኁራኑ መካከል ማእከሉን በመምራት የተመረጡ ግለሰቦች ብዙ የሥራ ልመድና ለአገር አስተዋጽኦ ለማድረግ ትጋት ያላቸው መሆኑ አንዱ የደረሱበት ደረጃ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ፕሮፌሰር ማስረሻ እንዳሉት ማእከሉ እንደተመሠረተ በቦርድ የበላይነት የሚንቀሳቀስ የራሱ ጽሕፈት ቤት እንዲኖረው መደረጉና የራሱን መርሃ ግብር አውጥቶ መንቀሳቀሱ በዓላማው ስር አንዳንድ ውጤቶች ለማምጣት አግዟል።

‹‹አካዳሚው የታላላቅ ምኁራን ስብስብ ነው። በአገር ውስጥ 260 ምኁራን፣ ከውጪ ደግሞ 150 የሚሆኑ አባላት አሉን። እነዚህ አባላት በተለያየ መስክ የተካኑ ናቸው። ስለዚህ ለምክረ ሐሳብ ለማድረግና ጥናቶችን ለማከናወን የምንጠቀመው አባላቶችን ነው። ጥቶችን በማስጠናት ግን በእነርሱ ብቻ አንወሰንም።›› ብለዋል። ጥናት ለማስጠናት አካዳሚው ተቸግሮ አለማወቁ እዚህ ላይ ነው። ከዚህ በተረፈ በሌሎች እንቅስቃሴዎችም ሙያና እውቀታቸውን ሊያካፍሉ የሚፈልጉ ባለሙያዎች ሁሉ ይሳተፋሉ።

መንግሥት ይህን ማእከል ለማገዝ የተወሰነ በጀት በየዓመቱ ይመድባል፤ ይህም የሰው ኃይሉን ወጪ እንደሚሸፍን ነው ፕሮፌሰር ማስረሻ የገለጹት። ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ለሚደረጉ ጥናቶች ገቢ የሚሆኑ የሥራ ማስኬጃዎች የአካዳሚውን የተለያዩ ወጪዎች ይሸፍላሉ።

እቅዶች
ዋናው የአካዳሚው ተግባር በሳይንስና ቴክኖሎጂን የሚደግፉ ሥራዎችን መሥራትና ኅብረተሰቡም የተሻለ የሳይንስ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ነው። ለዚህም የሚደረጉ ሳይንሳዊ ገለጻዎችና የተለያዩ የውይይት መድረኮች አጋዥ መሆናቸውን ማስረሻ ገልጸዋል። ከዛ ባለፈ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት በመረጃ ላይ የተመሠረተ የምክር ሐሰብ ለመስጠት ጥናቶች ይደረጋሉ። ይህንን አካሄድና ጥናት አጠናክሮ መቀጠል የአካዳሚው ቀጣይ ጉዞ አካል ነው።

በአካዳሚ ስር የተቋቋመው የብላቴን ጌታ ኅሩይ የሥነ ጥበባት ማእከል እንቅስቃሴም አለ። ይህም በየጊዜው አውደ ርዕዮችን ያካሂዳል፤ ውይይት ያደርጋል፣ የሥነጥበብ ሥራዎቸም ይታዩበታል። ከዛም ውጪ ከወራት በፊት (አዲስ ማለዳ ይህን ጥንቅር ባዘጋጀችበት ሰዓት) ልጆችና ወጣቶች የሳይንስ ፍቅር እንዲኖራቸውና ሳይንስን በመዳሰስ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያድረግ ማእከል ተከፍቷል። ይህንንም ማስፋፋትና ማስተዋወቅ ከማእከሉ እቅዱ መካከል ተካትቷል።

በዘመነ ኮሮና
ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ አግዷል፣ ፈትኗል። ሳይንስ አካዳሚም በተመሳሳይ የወረርሽኙ ነገር እንቅስቃሴዎቹን ሳይፈትንበት አልቀረም። በተለይም በየወሩ ይካሄድ የነበረው ሳይንሳዊ ገለጻ የውይይት መድረክ ተገትቷል። በመጋቢት ወር ሊካሄድ ከታሰበው መርሃ ግብር ጀምሮም ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ አሁን ኹለት ወራት ተቆጥረዋል። ያም ሆኖ ማእከሉ ሥራውን አልተወም። ይልቁንም ምሁራን ወረርሽኙን በሚመለከት ሊያበረክቱ በሚችሉት ሚና ዙሪያ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ተሰምቷል።

የሳይንስ አካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም በጉዳዩ ላይ ከሸገር ሬድዮ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ‹ከምሁራን ምን ይጠበቃል› በሚል ጉዳይ ላይ በሰጡት ሐሳብም፣ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጠነ ሰፊ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ጠቅሰው ይህም ጉዳት በሁሉም ዘርፍ ላይ የታየ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ አገር ኢትዮጵያ በጤናው ላይ ያላት አቅም ውሱን ነው። ይህ ወረርሽኝ ደግሞ ጭራሽ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳያደርገው ተሰግቷል። የኖረውን ሥራ አጥነት እንዳያብስና በኢኮኖሚው የቀነሰው የማምረት አቅምም ሊያስከትል ከሚችለው የምግብ እጥረት ጋር ተደምሮ ኢትዮጵያን ከባድ ቀውስ ውስጥ እንዳይከታት ተፈርቷል። ማኅበራዊ እሴቶች አሁንም እየተፈተኑ ነው።

እነዚህን ቸግሮች ነቅሰው የጠቀሱት ፕሮፌሰር ጽጌ፣ ምሁራን በዘርፉ በጥናትና መረጃ እንዲሁም ምርምር ላይ የተደገፈ ሳይንሳዊ ምክሮች የመስጠት፣ ማኅበረሰብን የማንቃት፣ ስለቫይረሱ ምርምር የማድረግ፣ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ መንገድ መፈለግ ይችላሉ ብለዋል። በሙያቸውም ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳቱ እንዲቀንስ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

ቫይረሱ ከየት መጣ፣ እንዴት እንከላከል፣ ምን ይደረግ የሚለውን ከመተንተን ባለፈም የምሁራንን ድርሻ ጠቅሰዋል። ይልቁንም የወደፊቱን በማጥናት ‹ድኅረ ኮሮና ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች› የሚለውን ከወዲሁ መቃኘት ያስፈልጋል። በወረርሽኙ ምክንያት ብዙ ከሰው ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ስለሚዛቡ ከወዲሁ መዘጋጀት አለብን። ከፖሊሲ ጀምሮ ለድኅረ ኮሮና ኢትዮጵያ ከወዲሁ ምሁራን መዘጋጀት፣ ምን ይደረጋል የሚለው ላይ ሐሳብ ማቀበል፣ እንዴት ኅብረተሰቡን ማነሳሳትና ኪሳራውንም ማካካስ እንችላን የሚለውም በየዘርፉ መታየት አለበት። ይህ አንድም የምሁራን ድርሻ ነው ብለዋል።

አካዳሚው ታድያ ይህን ሲያሳስብ የራሱን የቤት ሥራ በመሥራት ነው። በዚህም መሠረት የኮሮና ቫይረስን በሚመለከት የምሁራን ቡድን መዋቀሩን ፕሮፌሰሩ ያነሱ ሲሆን፣ ቡድኑም ከሁሉም መስክ የተወጣጡ ባለሞያ ምሁራንን የያዘ ነው። አንደኛው ቡድንም የሰዎች ደኅንነት ላይ ምርምር ያካሂዳል። ይልቁንም ቫይረሱ በሥነ አእመሮ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳይ በጥልቀት አጥንቶም መፍትሔ ይፈልጋል። በተጓዳኝ ሌላው ቡድን ደግሞ ግንዛቤ በመስጠት፣ ምክረ ሐሳቦችን በማቀበልና በማሳወቅ፣ ሙያዊ ድጋፍና መረጃ የመስጠት ሥራ ይሠራል። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚውም እነዚህን ተግባራት አስተባብሮ እየሠራ ነው፣ ፕሮፌሰር ጽጌ እንደገለጹት።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here