ከአዲሰ አበባ ወደ ክፍለ አገር የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ እያስከፈሉ ነው

0
544

መነሻቸውን አዲስ አበባ አድርገው ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ማጓጓዣ አሽከርካሪዎች የፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን የትራንስፖርት ስምሪትና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ እያስከፈሉ መሆኑ ታወቀ።

አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ እና ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል መንገደኞችን በመጫን ስምሪት በሚደረግባቸው መናኽሪያዎች በመገኘት የተባለውን ከታሪፍ በላይ የማስከፈል ሂደት ታዝባለች፤ ከተሳፋሪዎችም ማረጋገጥ ችላለች።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ከአዲስ አባበ ወደ ደብረ ብርሀን እንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ወደ አዲስ አባባ የመጡ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ የመክፈያ ደረሰኙ ላይ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን ታሪፍ በመጻፍ ነገር ግን ተጨማሪ ገንዘብ በማስከፈል፣ ‹ለትራፊክ ፖሊሰ እንዳትናገሩ፣ ከተናገራችሁ አንጭናችሁም› እንደተባሉ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ከአዲስ አበባ ደብር ብርሀን በታሪፉ መሰረት የሚከፈለው 90 ብር ብቻ ቢሆንም፣ አሽከርካሪዎች 160 ብር እንዳስከፈሏቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አውጅ መታወጁ የሚታወቅ ሲሆን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አንዱ ዘርፍ ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ተብሎ የወጣው የትራንስፖርት አዋጅ ነው። በዚህም የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ሕዝብ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች የኮሮና ቫይረስን ስርጭት እንዳይባባስ መጫን ከሚችሉት ግማሽ ሰዎችን ጭነው እንዲንቀሳቀስና ተሳፋሪዎች ቀድሞ ከነበረው ታሪፍ የ50 በመቶ ጨምርው አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉን የትራንስፖርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዳልካቸው ጸጋዬ ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አሽከርካሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሕግ በመተላለፍ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ማስከፈልና ከተፈቀደው ውጭ የመጫን ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል። አዋጁን በመተላለፋቸውም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

አንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጻ፣ አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ አገር የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ከተፈቀደው በላይ እንድንከፍል እየተገደድን ነው የሚሉ ተሳፋሪዎች ሕጉን አውቀው ለሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪዎች ጥቆማ ባለመስጠታቸውና መብታቸውን ተከራክረው ከማስከበር ይልቅ የታዘዙትን መክፈል ስለሚቀናቸው፣ ተሳፋሪዎች ራሳቸው የፈጠሩት ችግር ነው ይላሉ።

ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ያጋሩ ተሳፋሪዎች እንደሚሉት፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በሕግ ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ይሄን ያክል ካልከፈላችሁ አንሄድም በማለት አማራጭ እንዲያጡ ስለሚደረጉ፣ ትክክል ባልሆነ መንገድ ተስማምተው አገልግሎቱን ለማግኘት መገደዳቸውን ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ ማንም ምድብተኛ አሽከርካሪ የተመደበለትን ቦታ አውቆ በሕጉ መሰረት አገልግሎት የመስጠት ግደታ እንዳለበት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ነገር ግን አንዳንድ አሽከርካሪዎች በዚህ አይነት አካሄድ ተሳፋሪዎችን በሕግ ከተፈቀደው ልክ በላይ እንዲከፍሉ እንደሚያደርጉ ሚኒስቴሩ መረጃው እንዳለው ገልጸዋል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንዳሉት፣ ተሳፋሪዎች አስቸኳይ ጊዜውን ተላልፈው ከታሪፉ በላይ እንዲከፍሉ የሚያስገድዷቸውን አሽከርካሪዎች ለሕግ አስከባሪዎች ባለመጠቆምና ለማሳወቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ችግሩ እንዲበራከት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በተለያዩ ስፍራዎች እየታየ ያለውን እንዲህ ዓይነት ችግር ለመፍታት ኅብረተሰቡ መብቱን ለማስከበር በንቃት ያለመሳተፍና የሕግ ጥሰት ሲያጋጥም ለሕግ አስከባሪዎች አለመጠቆም ይታይበታል። ችግሩን ለማስወገድ ከመንግሥት ጎን ሆኖ መብቱን ማስከበርና ከአላስፈላጊ ወጪ ራሱን መጠበቅ አለበት ሲሉ የሕዝበ ግነኙነት ኃላፊው አሳስበዋል።

የሕዝብ መጓጓዣን በሚመለከት በከተማ እና ከከተማ ውጪ በሚደረግ ጉዞ በትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ዘንድ የሚደረገው ቁጥጥር የተለያየ እንደሆነ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የሚያነሳው ቅሬታ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ በከተማ ውስጥ ያለው ቁጥጥር ጠንከር ያለ ሲሆን ከከተማ ውጭ በሚደረጉ ጉዞዎች ግን እምብዛም ቁጥጥር እንደማይታይ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here