ሰሞኑን የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሥሩ በሚያስተዳድራቸው የንግድ ቤቶች ላይ ከ2000 በመቶ በላይ የሚደርስ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ በከተማዋ የሚገኙ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን አሰሙ።
አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአመዴ ገበያ በጫማ ንግድ ላይ የተሠማሩ ነጋዴ ለአዲስ ማለዳ እደገለጹት ከዚህ ቀደም እስከ 400 ብር ድረስ ይከፍሉ የነበረው የሱቅ ኪራይ አሁን ላይ 18ሺሕ ብር ሆኖባችዋል።
የተደረገው የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ከገቢያችን አንፃር ከፍተኛ ባይሆንም ኮርፖሬሽኑ ቤቶቹን በተገቢው ሁኔታ ሳያድስ እና ሕጎችን ሳያስተካክል ጭማሪውን መወሰኑ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ሌላው ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴ በበኩላቸው አሁን ለይ የተደረገው የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ድንገት በመደረጉ አስደንጋጭ ነው ይላሉ።
የዋጋ ጭማሪ ሲደረግም ከሱቆቹ ባለቤቶች ጋር በቅድሚያ መነጋገር ይገባ ነበር ያሉት ነጋዴው አሁንም ቢሆን መንግሥት ሊያወያየን ይገባል ብለዋል። ካልሆነ ግን አብዛኞቹ ነጋዴዎች ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ ምንጮቻችን ተናግረዋል።
የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎም ነጋዴዎች ለገሀር አካባቢ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተስተውሏል።
በከተማዋ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው ትላልቅ ሆቴሎችና የንግድ ማዕከላት ይገኛሉ። አብዛኞቹ ሱቆችም የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ወርሮ በነበረበት ወቅት የተሠሩ ናቸው።
አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ እንዳረጋገጠችው አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኙ ሦስት ያህል ኮርፖሬሽኑ የሚያከራያቸው ትላልቅ የመዝናኛ ቤቶች ኪራይ ይከፍላሉ።
የፈድራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ክብሮም ገብረመድኅን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የንግድ ቤቶቹ ላለፉት 40 ዓመታት ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደረገባችወም።
በዚህም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ኮርፖሬሽኑ ማግኘት ከሚገባው ባነሰ መልኩ ከሱቆቹ ገቢ ሲሰበስብ እንደቆየም ክብሮም ገልጸዋል። ኮርፖሬሽኑ በጥናቴ አረጋግጨዋለሁ እንደሚለው አብዛኛዎቹ ሱቆች በወር የሚያስገቡት ገቢ ከፍተኛ ነው።
አሁን ላይም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ሱቆች በእርጅና ብዛት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑም ተገልጿል። ከዛም ባለፈ የወሰዱትን ቁልፍ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው በሚሊዮን በሚቆጠር ብር የሚሸጡ ብዙ ናቸው የሚሉት ክብሮም፣ ይህን ተከትሎ ሱቆቹ መታደስ እና ሕጋዊነታቸውን ማረጋገጥ ስላለባቸው በእያንዳነዱ ሱቆች ላይ ዋጋ መጨምር ማስፈለጉን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ 972 የሚሆኑ የንግድ ቤቶች በካሬ ሜትር ከአንድ ብር በታች የሚከራዩ ሲሆን 2057 ቤቶች ደግሞ ከ10 ብር በታች በካሬ ሜትር ይከራያሉ። በንግድ ቤቶቹ ላይ የተደረገው ጭማሪ የዋጋ ግሽበት አያስከትልም ወይ በሚል አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ ክብሮም በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እዳይከሰቱ ከነጋዴዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር መታቀዱን አስታውቀዋል።
የፌድራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን በሥሩም 6635 የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን ያስተዳድራል።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011