ግልጽ ፍኖተ ካርታ ‘ለሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ወሳኝ ነው

0
703

ኢትዮጵያ እንደ አገር ባሳለፈቻቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ የሥልጣን መንበሩን ይዘውሩት የነበሩት መንግሥታት ሥልጣንናቸውን ለማፅናት ደረጃው ይለያይ እንጂ ተቀናቃኞቻቸውን ላይም ሆነ ተራው ሕዝብ ላይ የተለያዩ የጭቆና እና የግፍ በትሮቻቸውን አሳርፈዋል። በተለይም የሥልጣን ተቀናቃኝ ሊሆኑ የሚችሉት ላይ የበትራቸው ጉልበት የበረታ ሲሆን፣ ከዚህም ከፍ ካለ እጅግ በጣም አሰቃቂ የግፍ ተግባራት ፈፅመዋል። በተለይም ደግሞ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ፣ በደርግ እና ኢሕአዴግ መንግሥታት ከተፈፀሙት አሰቃቂ የጭቆናና የግፍ ተግባራት መካከል የዜጎች ደብዛ መጥፋት፣ ግድያ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ማሰቃየቶች ይገኙባቸዋል።
ኢሕአዴግ “ጥልቅ ተሐድሶ” ካካሔደና አዲስ አመራር ወደ ሥልጣነ መንበሩ ካመጣ በኋላ በግልጽ ላደረገው ጥፋት በሊቀመንበሩ እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል ይቅርታ ጠይቋል።
ይህንን ተከትሎ የመጣውን የይቅርታ እና ምኅረት መንፈስ በመያዝ እንዲሁም በማያዳግም መልኩ አስከፊውን የግፍ ስርዓት ታሪካችንን ዘግቶ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት መስጠቱ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ለስደት የተዳረጉ ዜጎች እና ቡድኖች ዋስትና ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት በመመለስ በሠላም እና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ፣ አፋኝ ናቸው በሚል ሲወቀሱ የነበሩ ደርዘን ያህል አዋጆችን መከለስ፣ በጥቅሉ ጠባብ የነበረው የፖለቲካ እና ሲቪል ማኅበራት ምኅዳር እንዲሰፋ ማድረግ ለዚህ አዎንታዊ እርምጃ እንደማሳያነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው። እንዲሁም ብዙ ክርክር ያስከተለውና የተጀመረውን የዕርቅ መንፈስ እንዳያጨናግፈው እንደ ሥጋት እየተነሳ ያለው መንግሥት ከሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ጋር በተያያዘ የቀድሞ የደኅንነት እና ፖሊስ አባላት ላይ የወሰደው የእስር እርምጃ ነው።
ሌላው ደግሞ የዕርቅ ሒደቱ ተቋማዊ መሆን ላይ መልስ መልስ ይሰጣል ተብሎ የታለመለት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን” ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በኅዳር 26 ቀን 2011 መውጣትና በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ መጠበቁ፥ አሠራሩ ተቋማዊነት ላይ ጥሩ መሠረት እንደሚጥል ይጠበቃል።
‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ሲባል ሊያግባባ የሚችል አንድ ወጥ አስማሚ ብያኔ ባይኖርም ቀድሞ ለተፈፀሙ ስልታዊና ሰፋ ያሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥበትን ስርዓት ያመለክታል። ዓላማውም የተበዳዮችን በደል ዕውቅና መስጠት፣ ቀጣይነት ያለው ሠላም፣ ዕርቅና እውነተኛ ዴሞክራሲን ለማስፈን በጋራ መግባባት ላይ የቆመ መሠረት መጣል ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ አሰጣጥን ጉዳይ “በጥንቃቄ መተግበር ካልተቻለ ‘ለሽግግሩ’ ራሱ እንቅፋት ሊሆን ይችላል” ስለሆነም መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ የተጀመረውን ሒደት በጥንቃቄ ማስፈፀም ይኖርበታል።
አዲስ ማለዳ በኢትዮጵያ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ በስኬታማ መንገድ ማስኬድ እና ወደ ዴሞክራሲ በሠላም መሻገር እንዲቻል መንግሥት የሚከተሉትን ማድረግ አለበት በሚል ትመክራለች፡

  • የመንግሥት ሥልጣናቸውን ከለላ በማድረግ ከባድ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የፈፀሙ ወንጀለኞችን በነጻ እና ፍትሐዊ የዳኝነት ስርዓት ለፍርድ ማቅረብ፣
  • በሠሩት ጥፋት የተፀፀቱት የቀድሞ አጥፊዎች ሐቁን በሕዝብ ፊት ተናግረው ይቅርታ እንዲያገኙ ማድረግ፣
  • ጉዳት የደረሰባቸው ተጠቂዎች የደረሰባቸውን ግፍ እና በደል ተናግረው እፎይታ የሚያገኙበት እና ተክሠው የሚያገግሙበት ዕድል መፍጠር፣

ጋዜጣችን ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎችንም ስልቶች በመጠቀም ሁሉንም አማራጮች ያጣመረ፣ የተለያዩ አገራትን ተመክሮ ከግምት ያስገባ እና የኢትዮጵያ የውስጥ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚስማማ፣ በተለይም ደግሞ ተጠቂዎችን እና ቀሪ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በሚገባ ያሳተፈ እንዲሆን ጥሪ ታደርጋለች።
አዲስ ማለዳ ለዚህ ሒደት መሳካት መንግሥት ግልጽነት የተሞላበት መንገድ እንዲከተል ታሳስባለች። አሁን በረቂቅነት የተዋወቀው “የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን” ማቋቋሚያ አዋጅ በአግባቡ ሕዝባዊ ውይይት ሊደረግበት ይገባል። በተጨማሪም መንግሥት ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሑን’ የሚያስኬድበትን ፍኖተ ካርታ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here