በሐዋሳ አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 70 ብር እየተሸጠ ነው

0
650

በሐዋሳ ቤንዚንን ከማደያዎች በመቅዳት በሕገ ወጥ ገበያ እስከ 70 ብር የሚሸጡ ባለ ሦስት እና ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ የቤንዚን ንግድ ነዳጅ ማደያዎች ላይ ተሰልፈው እንደሚውሉ የከተማው አስተዳደር ተናግሯል፡፡ በከተማው የተንሰራፋውና ለሳምንታት ያልተፈታው ሕገ ወጥ የቤንዚን ንግድ ለአስተዳደሩ ፈተና በመሆን ቀጥሏል፡፡
የከተማዋ የንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ ቦንቲ ቦቼ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በሐዋሳ ከወትሮው የተለየ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ባይከሰትም ከከተማዋ ዙሪያ የሚመጡ ሞተር ሳይክሎችና ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎች ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ 15 የነዳጅ ማደያዎች ቢኖሩም አምስቱ ብቻ በሙሉ አቅም እየሰሩ እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል። አምስቱ ያለበቂ ነዳጅ አቅርቦት እያቆራረጡ የሚሠሩ ሲሆኑ ቀሪ አምስቱ ደግሞ በተለያየ ምክንያት ሥራቸውን አቁመዋል፡፡ በቂ አቅርቦት የሌላቸው ማደያዎች ሲጠየቁ እናመጣለን ከሚል ምላሽ በዘለለ ያመጡት ነዳጅ አለመኖሩንም አክለው ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከተማዋ በቂ አቅርቦት እያገኘች አለመሆኑን የጠቀሱት ቦንቲ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር የከተማዋ የነዳጅ ኮታ ከፍ እንዲልላቸው እየተደራደሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ከአቅርቦት እጥረቱ ባለፈ ትልቁ ፈተና ሕገ ወጥ የቤንዚን ንግድ መበራከቱ እንደሆነ የገለጹት ቦንቲ ከዚህ ቀደም ማንም ሰው ከማደያዎች በጀሪካን እየገዛ በከፍተኛ ዋጋ ይቸረችር የነበረበትን ሕገ ወጥ አሠራር ማቋረጥ መቻሉ ሌላ ፈተና ይዞ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ አዲሱ ፈተናም ሁሉም ግለሰብ የሞተር ሳይክልና የባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ መሆኑን ተከትሎ የመጣ ነው ብለዋል፡፡ በደቡብ ክልል በተለይም ሞተር ሳይክሎችን መግዛት እንደ ሀብት መለኪያና ልማድ እንደሚቆጠር ይነገራል፡፡ በሐዋሳ ዙሪያ የሚገኙ ባለ ተሸከርካሪዎች ቤንዚን ለማግኘት ወደ ሐዋሳ መምጣቸውን ተከትሎ ተሸከርካሪዎች ወደ ሕገ ወጥ ንግድ ገብተዋል ነው የተባለው። ከማደያ ወረፋ ደርሷቸው በሊትር 19 ብር አካባቢ ሰለባትዮዋቸውን የሚሞሉ አሽከርካሪዎች ከኋላ ለተሰለፉት ተሸከርካሪዎች እስከ 70 ብር እየሸጡና እንደገና እየተሰለፉ መሆኑን ያሳወቀው መምሪያው ችግሩን እንዳባባሱት አሳውቋል፡፡ ይህን ለመከላከልም ተሸከርካሪዎች ነዳጅ ሲቀዱ ታርጋቸው እየተመዘገበ እንዲያልፉ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አክለዋል። ችግሩን ለመፍታትም የከተማዋ መንገድ ትራንስፖርትና ትራፊክ ተቋማት በጋራ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
የከተማዋ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊው ዘሪሁን ሰለሞን በበኩላቸው ካሉት 15 ማደያዎች ስራ ላይ የሚገኙት ከአምስት እንደማይበልጡ በመጥቀስ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ስለመኖሩ አንስተዋል፡፡ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ላለፉት 20 ቀናት ማታ ማታ ነዳጅን ከማደያዎች በኮንትሮባድ የማሸሽ ተግባር እየተፈጸመ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በተደረገ ክትትል ተሳታፊዎች በሕግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነውም ብለዋል፡፡
የቦንቲን ሐሳብ የሚጋሩት ዘሪሁን ወረፋ ደርሶት የሚቀዳ አሽከርካሪ ዞሮ በሕገወጥ መንገድ እስከ 70 ብር መሸጡ ከትራንስፖርቱ አገልግሎት ይልቅ ሕገወጥ ንግዱ ላይ እንዲጠመድ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ይህን ለማስቆምም በተለይም ለባለሁለትና ሦስት እግር አሽከርካሪዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ እንደ ዘሪሁን ገለጻ መምሪያው ሕጋዊ እውቅና የሰጣቸው ከሁለት ሺህ 500 በላይ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችና 10 ሺህ አካባቢ ሞተር ሳይክሎች በሐዋሳ አሉ፡፡ ይሁንና በሌሎች አካባባዎችም ያጋጠመው የነዳጅ እጥረትና የተሸርካሪዎች መብዛት ከሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከሻሸመኔና አርሲ ሳይቀር ቤንዚን ፍለጋ ወደ ሐዋሳ መምጣታቸው ሕገ ወጥ ንግዱን እንዳባባሰው ዘሪሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
በሕገ ወጥ ንግዱ ተሰልፈው በሚውሉት ተሽከርካሪዎች ሳቢያ ከተማዋ የትራንስፖርት ችግር አልገጠማትም ወይ? ያልናቸው ኃላፊው ዘሪሁን ባሉት 460 ሚኒባሶችና 17 የከተማ አውቶቡሶች አገልግሎቱን እየሰጡ በመሆኑ የከፋ ችግር እንዳልገጠማቸው አስረድተዋል፡፡ ችግሩ ሲከፋ መናኸሪያ ቆመው በሚውሉ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች እየተጠቀሙ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የነዳጅ እጥረቱ ከአንድ ወር በላይ መቆየቱን በመጥቀስ በማደያዎች ተሰልፈው የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን ማየት መልመዳቸውን ተናግረዋል፤ ችግሩ ቶሎ ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ይገልጻሉ፡፡ ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው እጥረቱ የከፋው በቤንዚን ተጠቃሚዎች ላይ መሆኑን ነግረውናል፡፡ የተለያዩ የሞተርና ባለ ሦስት እግር አሽከርካሪዎችን አስተያየት ብንጠይቅም ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ግን ‹‹ቤንዚንን በሕገ ወጥ ንግድ እየተጠቀሙ በአቋራጭ ለመክበር እያጭበረበሩ ያሉ አሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃዬን እገፋበታለሁ›› ብሏል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here