ኮሮና በአፍሪካ

0
707

አፍሪካ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ጥፋት ያደርስባቸዋል ተብለው የተሰጋላቸው በርካታ ደሃ አገራት ስብስብ ናት። ቫይረሱ ወደ አፍሪካ ከገባ ኹለት ወር ገደማ ጀምሮ ተንታኞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ሕይወት አደጋ ላይ እንዳለና በቫይረሱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን እንደሚሞቱ ይጠበቃል ብለው እየጠበቁ ነበር። ሆኖም የስርጭቱ ፍጥነት እንዳሰቡት አለመሆኑን ተከትሎ፣ አፍሪካ በቂ ምርመራ ስላላካሄደች ነው የሚል ትንታኔን መስጠት ቀጠሉ።

አሁን ግን ሊያዩት የፈለጉትን ውጤት እንዳገኙ ሁሉ በአፍሪካ በሚገኙ አገራት በድምሩ ከመቶ ሺሕ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ፣ ጉዳዩን መገናኛ ብዙኀን እየተቀባበሉት ይገኛሉ። አንድም ሰው ሳይገኝባት የቆየችው ሌሴቶም ግንቦት 13/2012 በቫይረሱ የተያዘን የመጀመሪያ ሰው እንዳለ አሳውቃለች። ቫይረሱ የተገኘባት የመጨረሻዋ አፍሪካዊት አገርም ሆና ተመዝግባለች።

ያም ሆኖ፣ የተለያየ ውዝግብ ቢነሳም፣ በድህነት ላይ ሌላ ችግር የተደቀነባት አፍሪካ፣ አሁንም ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ መንገዶችን እየተከተለች ትገኛለች።

የቢቢሲ ዘገባና አምስቱ አገራት
ቢቢሲ በድረገጹ ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት አፍሪካ አገራት ቫይረሱን በሚመለከት አንድ ዘገባ አስነብቧል። ‹ኮሮና በአፍሪካ ሳይመዘገብ ነው ወይስ መቆጣጠር ተችሎ› በሚል ርዕስ ከቀናት በፊት (ግንቦት 12) በወጣው በዚህ ዘለግ ያለ ጽሑፍ፣ አሁንም የዓለም ጤና ድርጅት ሩብ ቢሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን በቫይረሱ እንደሚያዙና ከ150 ሺሕ እስከ 190 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ለሞት ይዳረጋሉ ማለቱን ጠቅሷል።

በአፍሪካ እየሠሩ ያሉ በጎ አድራጎትና ድጋፍ ሰጪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ስጋታቸው ትኩረቱ ሁሉ ኮሮና ላይ ሆኖ ሌሎች የጤና ጉዳዮች መዘንጋታቸው ላይ ነው። እነርሱ ደግሞ እንደሚሉት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሕጻናት የፖሊዮ፣ የኩፍኝ፣ የቢጫ ወባ እና ሌሎች ክትባቶችን አልወሰዱም ወይም እየወሰዱ አይደሉም። በዚህም ላይ የጤና መከታተያ በቂ ቁሳቁስ የለም። ልጆች ክትባት እንዲያገኙ ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድንም ወላጆች ስለሚፈሩ፣ አስፈላጊው ራስን መጠበቂያ ቁሳቁስ ስለሌላቸው፣ በየቤታው መቀመጡን መርጠዋል።

ኮንጎ
ቢቢሲ በዘገባው ሽፋን ከሰጣቸው አገራት መካከል አንደኛዋ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ናት። በኮንጎ ቫይረሱ በአፍሪካ መግባቱ ይፋ ከተደረገበት ኹለትና ሦስት ወራት ቀደም ብሎ ገብቶ እንደሆነ የአገሪቱ የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ። ኮንጎ ሳታውቀው በፊትም ቫይረሱን ይዛ ቆይታለች የሚል መላምትም አለ። የጤና ባለሞያዎች እንዳሉት ታድያ፣ ባለሞያዎቹ ሳይቀሩ ሳያውቁት ቀድመው ለቫይረሱ ተጋልጠው ነበር። ‹‹እንደውም በጊዜ ሂደት አንዳች በሽታውን መቋቋም የሚስችል አቅም ሳንፈጥር አልቀርንም›› ብለዋልም፣ ሐኪሞቹ።

አዲስ ማለዳ ይህን ዘገባ አጠናቅራ ባጠናቀቀችበት ወቅት (እስከ ግንቦት 14) በኮንጎ 1835 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። በኮንጎ ኪንሻሳ የመጀመሪያው በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱን ተከትሎ በመጡት ተከታታይ ቀናት ቫይረሱ በአገሪቱ 26 ግዛቶች ውስጥ ተሰራጭቷል። የ61 ሰዎችን ሕይወትም ነጥቋል።

ኬንያ
ኬንያ ሌላው ቢቢሲ ትኩረት የሰጣት አፍሪካዊት አገር ናት። በኬንያ ያሉትና የተመዘገቡት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአንጻሩ ብዙ የሚባል ባይሆንም፣ በቫይረሱ ምክንያት ይሁን አይሁን ያልታወቀ የብዙ ሰዎች ሕይወት ግን አልፏል። ዘገባው እንዳሰፈረው ከሆነ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከመጋቢት መጀመሪያና ከዛም ቀደም ብሎ፣ በመተንፈሻ አካል ጋር ተያያዥ የሆነ በሽታ ከወትሮው በ40 በመቶ መጨመሩ ታይቷል።

እነዚህ የመተንፈሻ አካል በሽታ የተባሉት ቲቢ፣ ጉንፋን እና አስም ናቸው። እያደር ታድያ ሕመማቸው በጣም እየከፋና ወደ ሆስፒታል የሚሄዱና ሕይወታቸው የሚያልፍ ብዙ ኬንያውያን ነበሩ። ግን ሞታቸው በቫይረሱ ምክንያት እንደሆነ አልተመዘገበም፣ ምርመራም አልተከናወነም።

የኬንያ ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ወደ አስገዳጅ ማቆያ መላክን ጠልተውና ፈርተው ወደ ሆስፒታል መሄድን ስለማይፈልጉ ይሸሻሉ። ይህም የሆነው የኬንያ መንግሥት በኬንያ የሚገኙ ኳረንቲኖች ውስጥ የሚገቡት ሰዎች እንዲሁም ቫይረሱ ይኖርባቸዋል ተብለው የተጠረጠሩትም በግድ የራሳቸውን ወጪ ሸፍነው እንዲቆዩ ስላደረገ ነው። አልፎም ‹‹አንዳንድ ማቆያዎች ከማረሚያ ቤት ያልተሻሉ፣ ንጽህና የጎደላቸውና ሰዎች የበዛባቸው በመሆናቸው ለአካላዊ መራራቅ እንኳ በቂ ቦታ ያላቸው አይደሉም›› ቢቢሲ አናገርኳቸው ያለው የዐይን እማኞች ያሉት ነው።

ናይጄሪያ
ናይጄሪያ ይልቁንም ሰሜናዊ ናይጄሪያ ቢቢሲ የተመለከታት ሌላዋ አገር ናት። ከሦስት ወር በፊት በናይጄሪያ የቫይረሱ ስርጭት ከጀመረ ጀምሮ፣ የብዙ ሰዎች መታመምና መሞት በብዛት ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት ሙሐመድ ቡሐሪ መዘጋጋቱን በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እንዲራዘም አድርገዋል። ካኖ በተባለች የናይጄሪያ ከተማ በሚገኝ የመቃብር ስፍራ የመቃብር ቆፋሪ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ ‹‹ቤተሰቦቻችን ከሚነግሩንና በታሪክ ከምናውቀው የኮሌራ ወረርሽኝ በኋላ እንዲህ ያለ አስከፊ ነገር አይተን አናውቅም። ያም ከ60 ዓመት በፊት ነበር።›› ብለዋል።

በሰሜን ናይጄሪያ የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ የሚያገለግሉ የሕክምና ባለሞያዎችም በሰጡት አስተያየት፣ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎችን በብዛት ሲያስተናግዱ እንደነበር አንስተዋል።

ባለፉት ሦስት ወራትም ከተለመደው መጠን 40 እና 45 በመቶ በላይ የጨመረ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ በሽታን እንዳስተናገዱ ነው የሚናገሩት። ከእነዛም መካከልም ቀላል የማይባሉት የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንደሆነ በኋላ በምርመራ ተረጋግጧል።

በናይጄሪያ ታድያ አስፈላጊ ቁሳቁስ ባለመኖሩ የተዘጉ የሕክምና ማእከላት ሳይቀር አሉ። በአንጻሩ ግን ምርመራ ሊፋጠን እንደሚገባ ነው ባለሞያዎቹ ደጋግመው እየተናገሩ ያሉት። ያ ካልሆነ ስርጭቱን ለመቆጣጠር የበለጠ ከባድ ያደርገዋል። እንዲያም ሆኖ ደግሞ በናይጄሪያም እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ፣ ንክኪን በመፍራት ወደ ሆስፒታል የማይሄዱ ሰዎች ብዙ ናቸው።

ናይጄሪያ ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት ሰዓት ከ7 ሺሕ በላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች በምርመራ አግኝታለች። ታድያ በዋና ከተማዋ ሌጎስ ምንም እንኳ የእንቅስቃሴ ገደቦች ተደርገው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በከፊል እንቅስቃሴዎች ፈቃድ አግኝተዋል። ይህንንም ብዙዎች ይልቁንም በወረርሽኙ ዙሪያ በናይጄሪያ የሚሠሩ ሰዎች ሲቃወሙት ተሰምቷል።

ኢትዮጵያ
ቢቢሲ በዚህ ዘገባው ኢትዮጵያንም ቃኝቷል። ዘገባው በኢትዮጵያ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ ሕመምና በሽታ የተለመደ ነው በሚል የሚጀምር ሲሆን፣ እነዚህ በሽታዎችም በየዓመቱ በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ ሞቶች በሦስተኛ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞት የሚያስከትሉ ናቸው።

ታድያ በኢትዮጵያ የሚሠሩ ሕክምና ባለሞያዎችን አነጋግሬ ነበር ያለው ቢቢሲ፣ በዛም አሁን ላይ ያልተገኙ ነገር ግን የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው ሕሙማን ይመጣሉ ብለው ቢጠብቁም እንደሌለና፣ ብዙ ሕሙማን እንዳልተገኙ ገልጸዋል። ሌላው ቀርቶ የተለመደው የጉንፋን በሽታ እንኳ እንደወትሮው በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ አይደለም።

ከቀናት በፊት ግን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨረ፣ ከነጠላ አሃዝ ወደ ኹለት አሃዝ እያደገ ነው። ቢሆንም ድምር ቁጥሩ ግን አሁንም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛና ደኅና የሚባል ነው።

እንዲያም ሆኖ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በሮቿን የመዝጋትን አማራጭ እስከ አሁን አልተጠቀመችም። ይልቁንም የተወሰኑ የሚባሉ ለምሳሌ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መገደብ፣ ከአራት በላይ ሰዎች እንዳይሰበሰቡና ከሆነም ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ መከታተል፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች እንዲደረጉ ቁጥጥር ማድረግ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ማሻሻዎችን መተግበርና ወዘተ ላይ ጠንካራ ሥራዎች ተሠርተዋል።

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አሁን ባለው ልክ እንዲሆን ምክንያት ነው እየተባለ የሚነሳው አንዱና ዋነኛው ጉዳይ የጎብኚዎች በብዛት አለመኖር ወይም መቀነስ ነው። የገና በዓል እንዲሁም ጥምቀት ቀደም ብለው የተከናወኑና ያለፉ በዓላት በመሆናቸው ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደየአገራቸው የተመለሱበት ጊዜ ነው፣ ወረርሽኙ የተከሰተበት ወቅት።

እንዲሁም ወረርሽኙ በስፋት ያልተሰራጨበትና ብዙ ሰው ያልተገኘበት ሌላ የማይታወቅ ምክንያትም ሳይኖር አይቀርም የሚለው ቢቢሲ፣ እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ የሚያስታብልና ሁሉን ተቆጣጥረነዋል የሚያሰኝ አይደለም በማለት ያክላል። ይልቁንም የምርመራ አቅምን በጨመረ ቁጥር የሚሆነውን ማየት፣ እስከዛም ጥንቃቄው ላይ ማተኮር ተመራጭ ሆኗል።

ኡጋንዳ
በምሥራቅ አፍሪካ ጥብቅ የመዝጋት አሠራርን የተከተለችው አገር ኡጋንዳ ናት። ይህም አካሄድ የጠቀማት ይመስላል። በኡጋንዳ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 160 ሲሆን ይህም በንጽጽር ዝቅተኛ የሚባል ነው። ይህ ዘገባ እስከወጣበት ሰዓት ድረስም ምንም ዓይነት ሞት አላስተናገደችም።

አብዛኛው በኡጋንዳ የተካሄደው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ምርመራ በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የተደረገ እንደሆነ ዘገባው አካቷል። እነዚህም ከጎረቤት አገራት ወደ ኡጋንዳ የሚገቡት ናቸው። በጊዜውም ከተመረመሩና ቫይረሱ ከተገኘባቸው 139 ሰዎች መካከል 79 የሚሆኑት የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው።
የእንቅስቃሴ ገደብ ከመደረጉ ጋር ሆስፒታሎች ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተያያዘ ሕሙማንን አለማስተናገዳቸውና የታመሙ ሰዎችም በብዛት አለመኖራቸው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ይሰጣም። በአንጻሩ እንደዛ ላይሆን ይችላል፣ የእንቅስቃሴ ገደም መኖሩ ከቤታቸው እንዳይወጡ አስቀርቷቸው ይሆናል የሚል ግምትም ይሰጣል። በቫይረሱ የተያዙና አነስተኛ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችም በቤታቸው ሆነው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ይህም ማለት ቫይረሱ ቢኖርም በምርመራ አልታወቀም ነው። ምክንያቱም እንደተጠቀሰው የእንቅስቃሴ ገደብ ኡጋንዳውያንን ወደ ሆፒታሎች እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል።

በቅርቡ ታድያ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በየቤቱ ስለሞቱ ሰዎ መረጃዎችን ቤት ለቤት በመዞር ቃለመጠይቅ በማድረግ የሞታውን ምክንያት ለማወቅ አቅዷል። ይህም ሟቾች ያሳዩት የነበረው ምልክት ከቫይረሱ ጋር ተያያዥ ነው አይደለም የሚለውን ለማወቅ ይረዳል ተብሏል።

ጥብቅ የሆነውና በኡጋንዳውያን የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብን በሚመለከት ይነሳል ወይስ በዚህ ይቀጥላል የሚለውን በሚመለከትም፣ የእንቅስቃሴ ገደቡ ከመቀነሱ በፊት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን እድሜያቸው ከስድስት ዓመት በላይ ለሆኑ ቅድሚያ ሊያድል እንደሆነ የኡጋንዳ መንግሥት ቃል ገብቷል። ነገር ግን በቫይረሱ ምክንያት ሥራቸውን ያጡ ሰዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው። በተለይም ምን በልተን እናድራለን የሚለው ከፍተኛ ስጋት ሆኗል።

ታድያ ጭንብሉ በተባለው መልክ የሚሰራጭና ያም ስኬታማ የሚሆን ከሆነ ሙሴቪኒ ቢያንስ የንግድ ቤቶች እንዲከፈቱ ይደረጋል ሲሉ ቃል ገብተዋል። እንዲሁም መንገዶች ለትራንስፖርት እንቅስቃሴ ክፍት ይሆናሉ፣ በዛም ቢያንስ መደበኛ ሲጭኑ ከነበረው ተሳፋሪ ግማሽ እንዲጭኑ ይደረጋል ብለዋል።

ስጋቶችና መጽናናቶች
ኮሮና ቫይረስ ለአፍሪካ ከፍተኛ ስጋት መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ አንዳንዶች ‹ምን ያሟርቱብናል!› ሲሉ ይሰማል። በእርግጥም ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ ሁሉም የፈራው ለአፍሪካ ነበር። እንጂ በምን ተዓምር አሜሪካና አውሮፓን እንዲህ ያሸንፋቸዋል ተብሎ ይታሰባል! ታድያ ግን አፍሪካ እንደተፈራው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕመምተኛ አልተገኘባትም። ሆኖም እያደር እየጨመረ እንደሆነ ግልጽ ነው።

በአኅጉር ደረጃ ሲታይ አፍሪካ ቫይረሱ ከተስፋፋባቸው ስድስት አኅጉራት መካከል አፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ቀዳሚዋ አውሮፓ ስትሆን፣ ሰሜን አሜሪካ፣ እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ ከአፍሪካ በላይ፣ አውስትራሊያ/ኦሽኒያ ደግሞ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ይህም ይህ ጥንቅር እስከተዘጋጀበት እስከ ግንቦት 14 ድረስ ያለ መረጃ ነው።

እንደው ይህን ስናነሳ አብሮ ሊጠቀስ የሚችል ሐሰተኛ ዜናም አለ። ይህም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ የመጀመሪያው የክትባት ሙከራ በአፍሪካ ይከናወናል ብለዋል የሚል ዜና ነው። ሮይተርስ ግን ጉቴሬዝ እንደዛ ሲሉ አልሰማንም፣ ዜናው ሐሰተኛ ነው ብሏል።

በአንጻሩ ከሰሞኑ እኚሁ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ጉቴሬዝ ባስተላለፉት መልእክት ጥሩ ነገር ተናግረዋል። በተለይም ‹አታሟርቱብኝ! ክፉ ክፉውን አትጥሩብኝ!› የምትለው አፍሪካ፣ ብዙዎች ያንን የሚናገሩት አንድም ጥንቃቄ እንዲደረግ በማሳሰብ አንዳንዴ ደግሞ ‹ቁጠሩ እንዴት ዝቅተኛ ሊሆን ቻለ!› በሚል ጉዳዩን ከተዐምር በመቁጠር ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጉቴሬዝ በጎ ሐሳብ በማንሳት፣ አፍሪካንም በማወደስና በማመስገን፣ ሊደረግላት ስለሚገባው ድጋፍ በማንሳትና ጥንቃቄ እንድታደርግ በማሳሰብ ቀዳሚ ሳይሆኑ አይቀሩም።

የተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ጉቴሬዝ አፍሪካን አመስግነዋል። ይልቁንም የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን በሚመለከት በወሰዱት ፈጣን እርምጃ ያመሰገኗቸው ሲሆን፣ እንዲያም ሆኖ ብዙዎች ወደ ከፋ ድህነት ሊገቡ እንደሚችሉ ግን ስጋታቸውን አልሸሸጉም።

አልጀዚራ እንደዘገው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊው በአፍሪካ የታየው ጥቂት የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር አፍሪካ ከወረርሽኙ አስከፊ ገጽታ ተርፋ እንደሆነ ማመላከቻ ተስፋ ነው ወይም ሊሆን ይችላል ብለዋል። እርሳቸው ይህን መልእክት ባስተላለፉበት ጊዜ በአፍሪካ ከ2 ሺሕ 500 በላይ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ አሁን ላይ ቁጥሩ ከ3 ሺሕ ቢበልጥም በአንጻሩ ደኅና የሚባል ነው።

ጉቴሬዝ ታድያ ከጤናው እክል በላይ አፍሪካውያን የጀመሩት የእድገት ጉዞ ፈተና ላይ ይወድቃል የሚለውን ነጥብ አንስተዋል። አልጀዚራ እንደገዘበው ከሆነ በንግግራቸው ‹‹ወረርሽኙ የአፍሪካ እድገት የሚፈታተን ነው። የቆየውን እኩልነት ማጣት የሚያከርም፣ ረሀብን የሚያመጣ፣ የምግብ እጥረትና የበሽታ ተጋላጭነትም ሊያሰፋ ይችላል›› ብለዋል።

ይህ ምንአልባት ቫይረሱ ከዚህ በላይ ይሰራጫል ከሚለውም የከፋ ግምት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የዚህ እውነትነት ከምንም በላይ ለአፍሪካ ቅርብ ነው። እርሳቸውም ቁጥሩ አሁን ላይ አነስተኛ ቢሆንም ሊባባስና ድንገት ሊነሳ ስለሚችል ጥንቃቄ ላይ እንዲጠነክሩና በተያዘው ብርታት እንዲቀጥሉ በማለት አሳስቧል።

ታድያ ጥሪም አቅርበዋል። ይህም ጥሪ ዓለም ዐቀፍ ሲሆን፣ የአፍሪካን የጤና አጠባበቅ ስርዓት ለማጠናከር፣ ምግብን ተደራሽ ለማድረግና የኢኮኖሚ ቀውስን ለመቆጣጠር ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ያም ብቻ ሳይሆን ትምህርትን መደገፍ፣ ሥራን መጠበቅ፣ አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን ማቆየት፣ ያጡትንም ገቢ መመለስ ያስፈልጋልና ድጋፉ ለአፍሪካ መድረስ ይኖርበታል ብለዋል።

የብድር ነገርንም አንስተው፣ መክፈል ለማይችሉት የተሻለ የብድር አከፋፈል ስርዓት ሊበጅና ሊተገበር ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል። እንደሚታወቀው ባለፈው ወር ኃያላኑና በኢኮኖሚ የዳበሩ፣ ብድር የሚሰጡ አገራት የዓለማችንን ደሃ አገራት የተወሰነውን እዳ መሰረዛቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህም የሆነው በቫይረሱ ምክንያት እነዚህ ደሃ አገራት ሸክሙ ይበዛባቸዋል ብለው ነው። ለጉቴሬዝ ግን ያ በቂ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት በድረ ገጹ ይህን ጉዳይ አስምሮበት፣ እርግጥም ዓለም ዐቀፍ ትብብር በሚገባ ያስፈልጋል ሲል አስፍሮታል።

የፈረንሳይ አገር ዐቀፍ ራድዮን ከጉቴሬዝ ጋር ያደረገውን ቆይታ መሠረት አድርጎ ያወጣው ዘገባ ላይ፣ ጉቴሬዝ አፍሪካን ሲያደንቁ በተለይም በሰዓቱ በተወሰዱት ቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ መሆኑን ጠቅሷል። አፍረካ የተደነቀላትና ሌላው በአገራቱ መካከል የታየው ትብብር፣ የጤና ባለሞያዎችም በሙሉ ኃይል ወደ ሥራ ማስገባት መቻላቸው፣ ማቆያዎችን አስገዳጅ ማድረግ እናም ድንበርን መዝጋት ተጠቅሷል።

ከዛ በተፈረ አለመተማመን እንዳይኖርና ሐሰተኛ ዜናን ለመቆጣጠር የተደረገው እንቅስቃሴና ከኤች አይቪ እንዲሁም ኢቦላ ወረርሽኞች የተወሰደው ልምድ ቀላል ዋጋ የሚሰጠው አይደለምም ተብሏል። አፍሪካ ባቫይረሱ ምክንያት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሕይወታቸው ካለፉ 334 ሺሕ 680 ሰዎች መካከል 3115 ያህል ሰዎችን ነው ያጣችው። ይህ ቁጥር ቀላል ሆኖ ሳይሆን የኹለት ወራት እድሜን ተሻግሮ ሦስተኛውን ወር በጀረመው የቫይረሱ ስርጭት መለስተኛ ነው የሚባል መጠን ስለሆነ ነው።
አሁንም ታድያ በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ የሆነው ከተደረገው የምርመራ መጠን አነስተኛነት አንጻር ነው የሚሉ ግምቶች አሉ። የተባበሩት መንግሥትታትም ይህን የዓለም ጤና ድርጅት ሐሳብን በማንሳት፣ ቫይረሱ በአፍሪካ በሚገኙ 47 አገራት ከ83,000 እስከ 190,000 ሰዎችን ሕይወት ሊነጥቅ ይችላል ብሏል። ይህም ታድያ እንደ ትንቢት መፈጸሙ የማይቀር ራዕይ ሳይሆን የአፍሪካ አገራት መንግሥታት አካሄድና ውሳኔያቸውን መሠረት አድርጎ ሊቀየር የሚችልም ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሴቶችንም ጉዳይ አልዘነጋም። ድረ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሑፍም፣ ሴቶች ከፍተኛ የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸው የታወቀ ነገር ነው። እናም ማበረታቻና ማጠናከሪያ ፓኬጆች ቅድሚያ ለሴቶች እንዲሰጡና የሴቶችን ማኅበራዊ ደኅንነት እንዲጠበቅም አደራ ተብሏል። የቤት ውስጥ ጥቃት ከፍ እያለ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም፣ የሴቶች ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ የሰዎች መብት በዚህ አጋጣሚ እንዳይጣስም እንደዛው።

‹‹ብዙ ከባድ ውሳኔዎች በመንግሥታት ሊተላለፉ ይችላሉ።›› የሚለው የተባበሩት መንግሥትታ፣ ‹‹በዛ ውስጥ የዜጎችን አመኔታ እና ተሳትፎ ማግኘት ወሳኝ ነው። ቫይረሱን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለመግታት በአፍሪካም መግታት ወሳኝ ነው።›› ሲልም አሳስቧል።

አፍሪካ ከተባበሩት መንግሥትታ ያገኘችው ጥሩና ከበጎ ሐሳብ የመነጨ የሚመስል አስተያየት ኖረም አልኖረ፣ በእርግጥም በዚህ ቫይረስ በብዙ መፈተኗ አይቀሬ ነው። ጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉ የአፍሪካ አገራት እንዳሉ ሁሉ በማፈንና አግባብ ያልሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ይህን ቀን ለማለፍ የሚጥሩ አገራት መኖራቸውም ግልጽ ነው። እንደተባለው ግን ቫይረሱ ሁሉን ያዳረሰ ስለሆነ አንዱ ጋር ጠፍቶ ሌላው ጋር እንዲቆይ ሊደረግ ስለማይገባ፣ አፍሪካ ቫይረሱን ለብቻዋ ሳይሆን ከዓለም አገራት ጋር በጋራ እንደምትታገለው ግልጽ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here