ዝክረ ግንቦት 1997

0
1337

ዮሐንስ ዓለሙ (ሥማቸው የተቀየረ) በአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎችን በማለፍ እስከ መካከለኛ መኮንንነት ድረስ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። ዩሐንስ ከለጋነት የዕድሜ ደረጃቸው ጀምሮ እስከ ጉልምስናቸው ያለቀቃቸው ወታደርነት ሥነ ልቦና ተክለ ሰውነታቸውን ብቻ ሳይሆን ሰዓት አክባሪነታቸውንም የገነባ የመልካም ሥነ ምግባራቸው ምንጭ እንደሆናቸው ያሳብቃል።

ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት በወርሃ ግንቦት የሦስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ የተከሰተውን ግርግር መንግሥት ፈታበትን መንገድ እና የዩሐንስም የሕይወት ዑደት ምህዋሩን የለቀቀበት ጊዜ ነበር። ዮሐንስም በዐይነ ሕሊናቸው ወደ ኋላ መለስ ብለው እያስታወሱ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዩሐንስ ምርጫ 97ን ተከትሎ የተከሰተውን ሕዝባዊ ቁጣ ለማብረድ ከመንግሥት ወገን የተወሰደውን እርምጃ እንዲያስፈጽሙ ከባልደረቦቻቸው ጋር ኃላፊነት ተጥሎባቸው ወደ ዕዝ ጣቢያቸው በማምራት አገር የማረጋጋት (በወቅቱ መንግሥት የሚጠቀምበት ቃል እንደነበር ባለታሪካችን ጠቅሰዋል) ሥራን ሲሠሩ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ አገር ለማረጋጋት የተሠራው ሥራ ወገንን በመግደልና አካል በማጉደል የተከናወነ እንደነበር ወደ ኋላ ታሪካቸውን አስበው ዛሬ የተከናወነ ያህል ቀንና ሰዓት ሳይስቱ ይናገራሉ።

‹‹በየቀኑ የሚረግፈው ወጣት አንጀት የሚቆርጥ ነበር። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አገር ልታጣው የምትችለውን አምራች ወጣት ስታስበው ደግሞ ቁጭትህ ይንራል። እኔ በምመራው ዕዝ ውስጥ ወታደሮች ወደ ሕዝብ እንዳይተኩሱ አስፈላጊውን ትዕዛዝ በማስተላለፍ እንዲያው የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረግ ብችል እንኳን ብዬ እርምጃን ወስጄ ነበር። ነገር ግን ይህ የእኔ ውሳኔ አለቆቼ ጋር ደርሶ ኖሮ እኔን በግምገማ አውርደው ሊያስሩኝ ምናልባትም ሊገሉኝ እንደሚችሉ ከማእከላዊ ዕዝ የሚወጡ መረጃዎች ወደ እኔ ይደርሱኝ ጀመር።

እኔም ከቀናት በፊት እንደዚሁ ከሚመሩት እና ከዕዝ ጣቢያቸው ወደ ማእከላዊ ዕዝ ተጠርተው ከተገመገሙ በኋላ ወደ እስር ቤት የገቡ ጓደኞቼን ታሪክ ስሰማ ስለቆየሁ፣ መረጃዎች በደረሱኝ ሌሊት የመስክ አሽከርካሪውን እንዲቀር አድርጌ ወደ ደቡብ ሱዳን ኮበለልኩ። በጣም አስገራሚው ነገር እኔ በግሌ የሰማሁት የመሰለኝ መረጃ ሌሎችም ሰምተውት ኖረው በሌሊት ወደ ተሸከርካሪዋ እየገባሁ ሳለ ተከትለውኝ በመምጣት የሆነውን ሁሉ እንደሚያውቁ እና አብረውኝ መኮብለል እንደሚፈልጉ አስረድተውኝ፣ ላንከዳዳ ተማምለን መሣሪያችንን እንኳን (እኔ በግሌ ከታጠኩት ሽጉጥ በስተቀር) ምንም ነገር ሳንይዝ ነበር የኮበለልነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ያለፈውን አውስተዋል።

ወደ ደቡብ ሱዳን የኮበለሉት ባለታሪካችን በወቅቱ ነጻነቷን ያላገኘችው ደቡብ ሱዳን የዋናው ሱዳን አካል ነበረችና ከድንበር ተይዘው ወደ ካርቱም እንደተወሰዱ እና የኢትዮጵያ የመከላከያ አባላት እንደሆኑ በመታወቁ ወዲያው የጥገኝነት እና በተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ጉዳይ ተመዝግበው ከኹለት ዓመታት የሱዳን ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ማቅናታቸውን ይናገራሉ። አብረዋቸው ከኮበለሉት የሠራዊቱ አባላት ጋር ወደ አሜሪካ የገቡት ዩሐንስ፤ አንደኛው የበርሃ ጓዳቸው ወደ ስካንዲኒቪያ ስዊድን ማቅናቱን እና አሁንም ኑሮውን በስዊድን ኡሚያ ከተማ እየመራ ነው ይላሉ።

በወቅቱ ተወስዶ በነበረው እርምጃ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምእራብ እስከ ምሥራቅ አንድ አይነት እና የኃይል ዕርምጃው፣ በርካታ ወጣቶች ለሞት፣ የተረፉት ደግሞ ለስደት እንደተዳረጉ ባለታሪካችን ይናገራሉ።

‹‹ሱዳን ስደተኛ ጣቢያ ያገኘናቸው ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን አፈና እና ጭቆና በመፍራት እና ጓደኞቻቸው ሲገደሉ እና ተይዘው ተወስደው ደብዛቸው ሲጠፋ ‹ነግ በእኔ!› በሚል አገር ጥለው ሱዳን የገቡ እንደነበሩ እዛው ተረዳን። በጣም ነበር ልቤ የተነካው። ፖለቲካው አገር ጠባቂ የሆነውን መከላከያ ሠራዊትን በሰው ዘንድ አስቀያሚ ምስል እንዲኖረው በማድረግ በተለይ ወጣቱ በጥርጣሬ እና በጥላቻ እንዲመለከተው በማድረጉ እንደ እግር እሳት ይበላኛል። ቀን ኹላችንንም እኩል አደረገን እና ስናሳድዳቸው ከነበሩ ወጣቶች ጋር በአንድ ስደተኛ ጣቢያ ውስጥ አገኛኝቶን እኩል ስደተኞች የሚል ሥያሜ ሰጠን። ምን የመሰለች አገር እያለችን በእኔ እበልጥ በእኔ እሻል የፖለቲካ አዙሪት እርስ በርስ ተላልቀን ተረፍነው። ለስደት ተዳረግን›› ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

ባለታሪካችን አሁን ከ12 ዓመታት የአሜሪካን አገር ቆይታ በኋላ በቅርቡ ኹለተኛ ዓመቱን ያከበረው ለውጥ በትረ መንግሥቱን በያዘ ከአንድ ዓመት በኋላ አገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ጥለውት እንደሄዱት አልሆነላቸውም፤ ነገሮች ተለዋውጠዋል። ባለታሪካችን ዩሐንስ ከኹሉም የሚቆጫቸው ግን ኢትዮጵያ ሚሊኒየም በዓሏን በምታከብርበት ወቅት በአገራቸው ላይ አለመኖራቸው እና በባዕድ አገር በአገር ናፍቆት እንዴት እንዳሳለፉት ሲያስታውሱ ነው። አሁንም ስሜታቸው ይረበሻል።
‹‹አኔ እድለኛ ነኝ። ወደ አገር ቤት ከገባሁ በኋላ መከላከያ ውስጥ አብረውኝ ሲያገለግሉ የነበሩ ሰዎችን ፍለጋ ተንቀሳቅሼ ነበር። የተወሰኑት በስደትም ላይ ሆኜ እንደሰማሁት ታስረው እንደነበርና የት እንደደረሱ እስከ አሁን ቤተሰቦቻቸው እንደማያውቁ ነው። ሌሎች ደግሞ ማእረግ አግኝተው አሁንም በአገር መከላከያ ውስጥ የሚያገለግሉ ትጉህ ወታደሮች ሆነዋል። በተለይ በእኔ ዕዝ ስር የነበሩ ቆፍጣና ወታደሮችን በማየቴ እና በማዕረግም ከእኔ በመብለጣቸው ተደስቻለሁ። ነገር ግን በሕይወት ተርፈው ማየቴ ነው ዋናው እና ትልቁ ነገር።

የአለቆቼን ወደ ዕስር ቤት መጓዝ ታዝቤያለሁ። በአንድ አካባቢ መከማቸታቸውንም እንዲሁ። ነገር ግን ቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት በሰማሁበት ወቅት የተደበላለቀ ስሜት ነው የተሰማኝ። በእርሱ የአስተዳደር ዘመን መከላከያ ልጇን ልትፈልግ በወጣች እናት ላይ ተኩሷል፣ በእርሱ አገዛዝ ዘመን እኔ እና ስንት አገርን ልንጠቅም የምንችል ሰዎች በባዕዳን አገር ስደት ገብተን የማይገባንን የኑሮ መንገድ ተቀላቅለናል። በቃ! የሞቱን ዜና በሰማሁ ሰዓት ደስታ፣ ሀዘን፣ ቁጭት፤ ድብልቅልቅ ነበር ያለብኝ›› ሲሉ እርሳቸው ከኢትዮጵያ ርቀው በሄዱበት ወቅት በአገር ውስጥ የተከናወኑ ዐቢይ ክስተቶች እየመዘዙ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ኢትዮጵያ ማለት ለዩሐንስ ያኔ በ1997 ወርሐ ነሐሴ በምርጫቸው በድቅድቅ ጨለማ ትተዋት እንደወጡ ያልተመለሱባት፣ መከራዋን እና ዓለሟን በቅርብ ሆነው ያልተካፈሏት፣ የዕለት ህልማቸው ግን ቀርበው የማይኖሩባት የሩቅ አገር ሐሳባቸው ነበረች። ወደ አገር ቤት በተመለሱም ጊዜ በእርግጥ ደማቸውን ሰጥተው፣ አየሯን ምገው ያደጉባት፣ በዱር በገደሉ ተዋድቀው ሰንደቋን ያቆሙላት አገር አልመስልህ አለቻችው። ነገር በሙሉ በአጭር ጊዜ እንደዚህ ተለዋውጦ ይጠብቀኛል ብለው ያላሰቡት ዩሐንስ፣ ግራ መጋባታቸው አልቀረም።

‹‹በጣም አስደንጋጭ ነገሮች እየታዘብኩ ነው። በተለይ ደግሞ ይኸው አንድ ዓመት ሞላኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባዱን ውዝግቦች እና አሁን ያለው አመራር ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው ማሳያ የሆኑ ጉዳዮች ከዚህም ከዛም ብቅ ብቅ ብለዋል። በእኔ አስተያየት ሳይቃጠል በቅጠል ሊባሉ እንደሚገቡ እና ቁርጠኛ እርምጃ እንጂ ማስታመም እንደማያስፈልግ ነው የምረዳው›› ሲሉ ነባራዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ይገልጻሉ።

አዲስ ማለዳ 1997 የተካሄደውን ምርጫ በሚመለከት ትውስታቸውን እና በእርሳቸው አስተያየት ምን ይመስል እንደነበር ጥያቄ አቅርባ ነበር። እንዲህ አሉ፤ ‹‹ሠራዊቱ ውስጥ ኹሉም በትኩረት የሚከታተለው ጉዳይ ነበር። እውነትም ትክክለኛ ዴሞክራሲ እየተስተጋባ ነው የሚል ግምት የያዙ መኮንኖችም ነበሩ። ነገር ግን ወዲያው ተደጋጋሚ እና ከቀን ወደ ቀን አቅማችንን እንድናደራጅ እና ምርጫው ጋር በተያያዘ ከባድ ኃላፊነት ሊጣልብን እንደሚችል በመምሪያዎች በኩል ትዕዛዝ ሲተላለፍ ጥያቄዎች መነሳት ጀመረው ነበር።

‹ምንድነው? ምርጫውን ነጻ እና ፍትሃዊ ነው የምናደርገው ስትሉ አልነበረም ወይ? ታዲያ እንደዛ ከሆነ ከምርጫው በኋላ ምን የሚያስፈራ ጉዳይ ይገጥማል ተብሎ ነው የምንዘጋጀው? እየተባለ ክርክር በሠራዊቱ ውስጥ ነበር። ከኹሉም ግን ሠራዊቱ እንዲመርጥ ሲወሰን ድንገተኛ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በጣም ደስ የማይል ስሜት ተፈጥሮ ነበር›› ሲሉ ያስታውሳሉ።

በእርግጥ በዘመነ ኢሕአዴግ የፖለቲካውን አካሄድ የለወጠ ኹነት እንደነበር ባለታሪካችን ያወሳሉ። ከዛ ዓመት ጀምሮ ነገሮች እንደታሰቡት ያልሄዱበትና ገዢው ፓርቲም ኹሉንም ነገር በጥርጣሬ እየተመለከተ መራመድ የጀመረበት እንደነበርም ያወሳሉ። ‹‹በነገራችን ላይ ከምርጫ 97 በኋላ የተነሳው ትኩሳት ነው አሁን ያለውን ለውጥ እውን እንዲሆን ያደረገው። በየቦታው ሕዝባዊ ቁጣ እና እምቢ ባይነት ነበር። ነገር ግን በመሣሪያም በምንም ሲታፈን ቆይቶ ነበር።›› ሲሉ ያስረዳሉ።
የያኔው ኢሕአዴግ ‹‹ምርጫው ነጻ እና ፍትሀዊ›› ይሆናል ብሎ ከምርጫው አስቀድሞ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት ተሰጥቷቸው ክርክር ሲያደርጉ፣ ቅስቀሳቸውን ሲያስተጋቡ እና ከፍ ሲልም ገዢውን ፓርቲ አፈር ሲያስግጡት ተስተዋለ። በሕዝቡም ዘንድ መንግሥት ሲሰደብ አይቶ የማያውቀው እና እየተካሄደ የነበረውን እንቅስቃሴ ለሚመለከት በእርግጥም እውነተኛው እና የተናፈቀው ዴሞክራሲ ስጋ መልበሱን አልተጠራጠሩም።

ይህንንም ተከትሎ ሕዝቡ ይሆነኛል፣ ይስማማኛል፣ ቢመራኝ እኔን እንደ ግለሰብ ብሎም ኢትዮጵያን እንደ አገር ዕድገቷን አፋጥኖ የተሻለች አገር መፍጠር ይችላል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ሐሳብና መርህ በግልጽ ማራመድ፣ ማስተጋባት ጀመረ።

ከወራት በፊት የተጀመረው የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በተለይም ደግሞ ሚያዚያ 29 እና 30 የገዢው ፓርቲ ድጋፍ ሰልፍ እና ከተፎካካሪው ፓርቲ ውስጥ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ለተባለው የተፎካካሪ ፓርቲ ድጋፍ የታየው የድጋፍ ሰልፍ፣ የምርጫ ሂደቱን አዝናኝ እና ቀልብ ሳቢ፤ የምርጫ ውጤቱን ደግሞ እጅግ አጓጊ አድርጎት አለፈ።

እንዲያውም በሚያዚያ 29/1997 በገዢው ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ላይ መስቀል አደባባይን ላጥለቀለቀው ሕዝብ የወቅቱ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹ይህ ሕዝባዊ ማዕበል ምርጫውን ያለምንም ማጭበርበር ያሸንፋል›› የሚል ንግግር አሰምተው ነበር። በዚህም ጊዜ ‹‹ማጭበርበርን›› ምን አመጣው የሚል ሽሙጥ እና ትችት በብዙዎች ዘንድ ሲስተጋባ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።

በወራት የምረጡኝ ቅስቀሳ እና ጎራ ለይቶ የሐሳብ ፍጭት ሲካሄድበት የነበሩት ቀናት ተገባደው የቁርጥ ቀኗ ግንቦት 7/1997 መጣች። ሰውም ከማለዳው ጀምሮ ድምጹን ለመስጠት ተሰለፈ። ነገሮች በአስገራሚ ፍጥነት ተካሂደው ገዢው ፓርቲ በአሸናፊነት መመረጡን ይፋ ተደረገ። ከዚህ በኋላ ግን ነገሮች እንደነበሩት አልቀጠሉም፤ መልካቸውን ቀየሩ።

‹‹ድምጼ ተሰርቆብኛል›› ያሉት ወደ አደባባይ ወጡ፤ መንግሥትም በወቅቱ ‹‹ተመጣጣኝ እርምጃ›› ያለውን በሕዝቡ ላይ ወሰደ። ይሁን እንጂ ከወርሃ ግንቦት 1997 የጀመረው አለመረጋጋት ቀጣዩ ዓመት 1998 ድረስ አልበረደም ነበር። በርካቶች ወደ እስር የተጋዙበት፣ ሰብዓዊ መብታቸው የተጣሰበት እንደነበር በተደጋጋሚ በዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲስተጋባ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here