ከወረርሽኙ ተጓዳኝ ‹ሕዝብ› እና ‹መንግሥት› ሠራሽ ፈተናዎች

0
678

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዎና ፖለቲካዊ ሕይወቶች ላይ ቀውስን አስከትሏል። ወደፊት የሚመጣውም ከባድ እንደሚሆን ከወዲሁ እየተጠበቀ ነው። ይህም ብቻውን ትልቅ ፈተና ነው የሚሉት መቅደስ ቹቹ፣ እንዲህ ባለ ከባድ ወቅት ሕዝብ እና መንግሥት ሠራሽ ተጨማሪ ፈተናዎች ሊቀረፉ ይገባል፣ መንግሥትም ሆነ ዜጎች እርምጃቸውን በዚህ ልክ ሊያጤኑ ያስፈልጋል ሲሉ የተወሰኑ ነጥቦችን አንስተዋል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ግንቦት 8/2012 በወጣው ሰማንያኛ እትሟ ካስነበበቻቸው ዜናዎች መካከል አንደኛው ‹በቦሌ ክፍለ ከተማ 500 የሚሆኑ የመሥሪያ ቦታዎች በመንግሥት መፍረሳቸው ታወቀ› የሚል ነበር። በዚህም እንደተቀመጠው በክፍለ ከተማው አደይ አበባ ስታድየም ዙሪያ ከ2010 ጀምሮ ለሥራ ቦታ የተሰጣቸው የነበሩ ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድንገት ከቦታው እንዲነሱ መደረጉንና ለሥራ የቀለሱት ትንንሽ የላስቲክ ጎጆም እንደፈረሰባቸው የሚያስታውቅ ነው።

የሚያሳዝነው እነዚህ ሰዎች ከ500 በላይ ሲሆኑ፣ የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንና ኑሯቸውን ለመግፋት ሻይ እና ቡና፣ የታሸጉ መጠጦችና መሰል ምርቶችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ናቸው። አዲስ ማለዳ በዜናው ላይ እንዳኖረችው ከሆነ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የተገኘ ምላሽ የለም። ቢያንስ ሁኔታውን ለመረዳት ከመንግሥት ወይም ‹አፈረሱ› ከተባሉ አካላት መልስ ያስፈልግ ነበር። ይህ አለመሆኑ ግን ጉዳዩን ‹መንግሥት ሠራሽ› ችግር ያደርገዋል ማለት ነው። በተለይ እንዲህ ባለ ከባድ ጊዜ።

ይልቁንም ደግሞ በስፍራው በሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ሴቶች መሆናቸው ተጠቅሷል። እርግጥም ደግሞ እንዲhe ባሉ አገልግሎት ሰጪ ሥራዎች ላይ በብዛት የሚገኙት ሴቶች ናቸው። ከሴቶችም የልጆች እናት የሆኑ ይበረክታሉ። ለብቻቸው ልጆች የሚያሳድጉ ሲሆኑ ደግሞ፣ የኮቪde 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በእጅ አዙር ካሳረፈባቸውና ከሚያሳርፍባቸው ዱላ በተጨማሪ ሌላ ፈተና እንደሚሆን ግልጽ ነው።

በዜናው ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ ‹‹የልጅ እናት የሆኑ የችግሩ ሰለባዎች ልጆቻቸው ከዚህ በፊት ትምህርት ቤት ላይ በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ይመገቡ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ልጆችን መመገብና ማስተዳደር አቅቷቸው በአጭር ጊዜ ለጎዳና እና ለልመና ሕይወት እንደሚጋለጡ አስታውቀዋል።›› ይላል።

እንዲህ ያሉ አስከፊ ጊዜያት የተለመዱ አይደሉም። ወረርሽኝም ቢሆን እዛም እዚህም ወቅት ጠብቆ ከሚነሳው፣ በጤና ዘርፍ ኢትዮጵያ ካለባት አቅም ማነስ እንዲሁም አጠቃላይ ድህነቷ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ካልሆነ በቀር፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃና በዓለም ስጋት የሆነ ወረርሽኝ በየጊዜው የሚከሰት አይደለም። እናም ታድያ አንድነትና ጽናትን፣ መተሳሰብና መደጋገፍን አጠንክሮ፣ ክፉ ጊዜው እንዲያጥር ማፋጠን ይጠበቃል።

በአንጻሩ ግን ከወረርሽኙ ስጋት ላይ የሚታከሉ ፈተናዎች ጎልተው ይታያሉ። እነዚህንም ሰዎች ወይም ዜጎች በራሳቸው ላይ የሚፈጥሩት ሲሆን የቀረውን ደግሞ መንግሥት የሚፈጥርላቸው ነው። እንዴት አድርገው ነው እነዚህ አካላት ችግርና ፈተናን እየፈጠሩ የሚገኙት የተባለ እንደሆነ፣ የተወሰነ ከትዝብቴ ልጥቀስ።

‹ሕዝብ› ሠራሽ ፈተና
ዓለማችን በተለያየ ጊዜ ያስተናገደቻቸው የተፈጥሮ አደጋዎች ምንጫቸው ቢጠና የሰው ልጅ ጥፋት ውጤት ናቸው። ምንም እንኳን ይህን ሐሳብ መንፈሳዊ ሰዎችና ሃይማኖተኞች ብቻ ሊናገሩት የሚችሉ ቢመስልም፣ እንደው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ያደረሰው ጥፋት በራሱ በተፈጥሮ አንጻራዊ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም።

የተፈጥሮ አደጋ የሚባሉ ጎርፍና አውሎ ነፋስ መሰል አደጋዎች፣ ወረርሽኞች፣ ድርቅና ረሃብ ሳይቀሩ፣ የሰው ልጅ ምድር ላይ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት የሚከሰቱና የተከሰቱ ናቸው። የሰው ልጅ ተፈጥሮን ረብሿልና። አንድ ግለሰብ ‹እኔ ምን አድርጌ?› ሊል ይችላል። ግን ሁሉም በአቅሙ የሚያደርገው ትንሽ የሚመስል፣ መንገድ ላይ በግዴለሽነት ቆሻሻን ከመጣል ጀምሮ ያለ ጥፋት ድምር ነው አገር የሚያክል ችግር የሚፈጥረው።

አሁን ባለንበት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅትም ትንሽ የሚመስሉ፣ አንድ ሰው ብቻውን ስላደረጋቸው ጉዳት የሚያደርስ ሳይመስለው የሚገፋበትና ሁሉም ሰው ያንን ስሜት በሚያንጸባርቅበት ጊዜ፣ ሰው ሠራሽ ተደራቢ ችግሮች ይፈጠራሉ። ይኸውም አንደኛው አጋጣሚን ለመጠቀም የሚደረግ ጥረት ነው። በአጋጣሚው መሬት መውረር፣ በአጋጣሚው ገንዘብ ማትረፍ፣ በአጋጣሚው ዝናን መሸመት…ወዘተ።

በፖለቲካውም እንደዛው ነው። ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተከሰተበት ጊዜ አገራዊ ምርጫ የሚደረግበትና በፖለቲካው ጉዳይ ለውጥ የሚጠበቅበት ሰሞን ነው። በሚገርም ሁኔታ በቀን በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ላይ በቫይረሱ ምክንያት እየረገፉ እየተመለከቱ ማዕበሉን እንደሚሻገሩ ‹ያመኑ› ሰዎች ተጨማሪ መቶ ዓመት የሚኖሩ ይመስላሉ።

አሁን ላይ የፖለቲከኞች ንትርክ አገር ለማትረፍ፣ የዴሞክራሲን መሠረት ለመጣል፣ ፍትሃዊ ምርጫን መፈለግ፣ እውነተኛ ለውጥን መሻት ወዘተ ሲባልም እንሰማለን። እኔ በበኩሌ ይህን አላምንም። የትኛውም ቢሆን ሊቀጥል የሚችለው ሰዎች ወይም ዜጎች በጤናማ ሁኔታ በሕይወት ሲኖሩ ብቻ ነው። ለሰዎች ሕይወትና ጤና ማሰብ ያልቻሉ ፖለቲከኞች፣ ተቃዋሚዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስንመለከት ግን፣ ጉዳዩ ስለ ሕዝብ ሳይሆን ስለ እነርሱ እንደሆነ እናውቃለን።

የሴቶች መብትን በሚመለከት ግን እነዚህ ሰዎች ቢጠየቁ መልሳቸው እንደ አሁኑ አይሆንም። የሴቶች መብት ብሎ ከመጮኽ በፊት የአገር ሰላም ይቀድማል ይላሉ። ከፖለቲካ ንትርክና ከምርጫ በፊት የሰው ልጅ ጤና እና ደኅንነት ይቅደም ሲባል ግን፣ በየት በኩል!

ይህን የምናጋግል እንደዛው ተጨማሪ ፈተና ነን። ይህ የአንዱን የፖለቲካ አካሄድ የመደገፍ ሌላውን የመንቀፍ ጉዳይ አይደለም፣ ደኅና መሆን ላይ ትኩረት መስጠት ነው። በየሆስፒታሉ የሚገኙና ይህ ጽሑፍ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ 400 ለደረሱ የቫይረሱ ተጠቂ ኢትዮጵያውያንና እነርሱን በመንከባከብ ለተጠመዱ፣ ቀጥሎ ምን ያህል ሰው በራቸውን አንኳክቶ እንደሚመጣ በስጋት እየጠበቁ ላሉ የሕክምና ባለሞያዎችም ማሰብ ነው።

አሁን ትግሉ መሆን ያለበት ከወረርሽኙ ጋር እንጂ እርስ በእርስ አይደለም። አሁን ትግል ካስፈለገም ቅንጣት ከሆነው ሕዋስ ጋር እንጂ ከመንግሥት ጋር አይደለም።
እንደ ሕዝብ መደማመጥ መቻልና ማስተዋልም ያስፈልጋል። የተተነፈሰውን፣ የተባለውን፣ የተነገረውን ሁሉ ከፖለቲካ ጋር ማያያዝ ይደክማል። ለምን እንደማይደክመን አይታወቅም እንጂ፣ ሰው በተናገረ ቁጥር ጸብ አጫሪ ቃላት እንደመፈለግ ነው። ወረርሽኙን ለመከላከልና ለተቸገሩት ለመድረስ እህልና ገንዘብ እንደምንሰጥና እንደሰጠን ሁሉ፣ በጎ ሐሳብ መስጠትም ትልቅ ዋጋ አለው። ከምንም በላይ እንደ ሕዝብ ልናደርግ የምችለው ራሳችንንም መጠበቅ ነው።

መንግሥት ሠራሽ ፈተና
መንግሥት ፍጹም እንዲሆን አይጠበቅም። ሰዎች ተደራጅተው ሌሎችን ሰዎች ለመምራት ስለተመረጡና ስለበቁ፣ ባለሥልጣንም ተስለባሉና ኃላፊነት ስለተጣለባቸው እንጂ ሰው መሆናቸው አይቀየርምና። ነገር ግን የተሻለ ውሳኔ የሚሰጡ፣ አርቀው የሚያስቡና ነገን የሚመለከቱ የተሻሉ ሰዎች እንዲሆኑ ስርዓት የሚባል ነገር ተፈጥሯል። በዛ ስርዓት እስከሄዱ ድረስ ተስማምተን እንዘልቃለን።

እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሰዓት መንግሥት እየጨመራቸው ያሉ ፈተናዎች ቀላል አይደሉም። የሰዉን ሕይወት የበለጠ ያከብዱታል። እርግጥ ነው ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስመሰግን የሚባል ሥራ ታይቷል። ያም ግን ክፍተቶች አሉበት። ለምሳሌ አንደኛው የሕግና መመሪያ ክፍተት ነው።

የእምነት ተቋማት በሮቻቸውን በመክፈታቸው እንጂ ባለፈው ሰሞን በምዕመናን ላይ የሚደርሰው ድብደባ ቀላል አልነበረም። ይህም የሆነው ‹የሕዝብ አገልጋይ› የተባሉ የመንግሥት ሹም ሰላም አስጠባቂ ኃይል የምንላቸው ፖሊሶች በምዕመኑ ላይ የሚያደርሱት ድብደባ ነው። አንድ ፖሊስ ደስ ባሰኘው ሰዓት ዱላ የማንሳትና ሰውን የመምታት ሥልጣን እንዳለው ከተሰማው፣ ይህ የመንግሥት ጥፋትና ችግር ነው።

የራሳቸውን ክብር እንጂ ሕግን የማያስከብሩ ፖሊሶች ይታያሉ። በተፈጠረላቸው የሕግና መመሪያ ክፍተትም ሰው ሳይሆን እንስሳ እንደሚጠብቁ ሁሉ ዱላን ከእጃቸው አይነጥሉም። ከዛም የሚብሰው አጥፊውን ሳይሆን ‹ምን አጠፋሁ?› ብሎ በሰላም የሚጠይቀው ላይ ነው ዱላቸው የሚያርፈው።

ከዛም አልፎ መግቢያው ላያ ያነሳሁት ሰዎችን የማስነሳት ሥራ ይታያል። ሕገወጥ እንኳ ቢሆኑ ይህ አግባብ አይመስለኝም። ማሳወቅ አንድ ነገር ነው፣ ወይም አሁን ላይ መሬት እያጠሩ ያሉ ሕገ ወጦችን መቆጣጠርም ተገቢነቱ አያጠራጥርም። ግን ቢያንስ ከኹለት ወርና ከዛ በላይ ቀደም ብለው በቀለሱት ጎጆ የሚኖሩና የሚሠሩትን ግን ለጊዜው ባሉበት እንዲቆዩ ማድረግ ያስፈልጋል።

ግልጽ ነው። መንግሥት በብዙ ወጪ፣ በብዙ የበጎ አድራጊዎች ድጋፍ ጎዳና ያሉ፣ ቤት የሌላቸው፣ የቀን ምግብ የማያገኙትን እያነሳ ነው። ታድያ በዚህ በኩል ለምን በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ሰዎችን ይጥላል? የሥራ አጥ ቁጥር ከዚህ ከፍ የሚል ከሆነ፣ በቀጣይ የክረምት ወራት ከደመናማና ሰማይ ዝናባማ ወቅት በተጓዳኝ ለሕይወት የሚያሰጉ ዘራፊና ሌቦችን ማፍራት እንደሚኖርም ማስተዋል የግድ ነው።

በተጓዳኝ ለሴቶች ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል። በሚፈርሱ ቤቶች፣ ይነሱ በሚባሉ የንግድ የላስቲክ ጎጆዎች ውስጥ የሴቶች ሕይወት አለ። እነዚህ ሴቶች፣ እነዚህ ሰዎች በቅንጡ ሁኔታ እየኖሩ፣ ትርፍ ለማግበስበስ የሚዳክሩ አይደሉም። ይልቁንም የእለት የራሳቸውን ጉርስና የልጆቻቸውን ምግብ ለመቻል የሚታገሉ ናቸው።
መንግሥት ለምን አልጠበቀንም፣ እንደ ዜጋ ለምን ትኩረት አልሰጠንም፣ ድምጻችን ይሰማ፣ ተቃዋሚ/ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይወክሉን ወዘተ ብለው ድምጻቸውን እንኳ አሰምተው አያውቁም። ባገኙት ጉድለት የራሳቸውን ጉድለት ለመሙላት ደፋ ቀና ነው የሚሉት።

ሲጠቃለል፤ ይህ እንግዲህ ለመነሻ ያህል ያነሳሁት ሐሳብ እንጂ ሁሉንም ነገር ያጤነና ዙሪያ ገቡን ያካለለ አይደለም። ዋናው ነጥብ ግን ከወረርሽኙ በተጓዳኝ በራሳችን ላይ ሌላ በሽታ አንሁን የሚል ነው። መንግሥትም ሌላ ሸክም አይፍጠር። ምክንያቱም በዚህ መካከል ማንም አይጠቀምም፣ የሚጠቀም የሚመስለው ካለም ሞኝ ነው። ይልቁንም ከቫይረሱ በተጨማሪ የምንጎሳቆልበትንና የምንታመምበትን ተጨማሪ አማራጭ እንፈጥራለን፣ ያም የከፋ ይሆናል። መንግሥትም እርምጃዎቹን የማያጤን ከሆነ ይህን ያፋጥነዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here