በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና (ሚኒስትሪ) መቼ፣ እንዴት እና በምን ዓይነት ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት ምንም አይነት ውሳኔ ላይ አለመደረሱ ታወቀ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዳኜ ገብሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍልን ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች 12 ሺሕ ቢሆኑም ፈተና አሰጣጡ እንዴት እና መቼ ይሰጥ የሚለው ጉዳይ ላይ ግን ውሳኔ ላይ መድረስ አልተቻለም። እንደ ዳኜ ገለጻ ከሆነ፣ የ12ኛ ክፍልም ይሁን የስምንተኛ ክፍል ፈተና እንዴት እና በምን መንገድ ይሁን የሚለውን ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ንግግር የሚወሰን ይሆናል። እስከ አሁን ግን ምንም የተገለጸ ነገር የለም ሲሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የወረርሽኝ ስርጭቱን ለመግታት በማሰብ ተማሪዎች በቤታቸው በመሆን እንዲሳልፉ መወሰኑ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ተማሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ መወሰኑን ተከትሎ በተማሪዎቹ ላይ የድብርት፣ ትምህርት የለም ብሎ በስንፍና መዘናጋትና የቸልተኝነት ሁኔታ እንዳይኖር በማሰብ፣ ወቅቱም የአገር ዐቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የሚደረጉ ፈተናዎች የሚኖሩበት ጊዜ ስለሆነ፣ ለፈተና እንዲዘጋጁ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሞዴል ፈተናን በቴሌግራም እንዲሰጣቸው መደረጉን ዳኜ አንስተዋል።
ከዛም በተጨማሪ ‹ትምህርት በቤቴ› በሚለው መርሃ ግብር ተማሪዎች በቤታቸው መሆናቸውን ተከትሎ ምንም እንኳን መጽሐፍት ቢኖሯቸውም ከዛ በተጨማሪ የመምህራን እገዛ ስለሚያስፈልጋቸው በሬዲዮ፣ በአፍሪ ኸልዝ የቴሌቭዥን ጣቢያ ከ7ኛ እስከ 12ተኛ ድርስ ላሉ ተማሪዎች ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ከዛም በተጨማሪ የተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ በቴሌግራም እና በዩትዩብ ቻናሎች እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ገለፃ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ትምህርት ነክ ጉዳዮችን ማስተላለፍ ያስፈለገበት ምክንያት ትምህርት ስርዓቱ እንዳይቋረጥ በማሰብ ነው። ከዛም በተጨማሪ ሞዴል ፈተናውን በቴሌግራም መስጠት ያስፈለገው ተማሪዎቹ ለሚቀጥለው ክልላዊ ፈተና እንዲዘጋጁ ሲሆን፣ ለ12ኛ ክፍሎች ደግሞ ብሔራዊ ፈተና ስላለ ምን ያህል እራሳቸውን አብቅተዋል የሚለውን እራሳቸውን እንዲገመግሙ ለማቻል ነው።
ነገር ግን ይላሉ ኃላፊው፣ ትምህርት ቢሮው በትክክለኛው ሰዓት እና ጊዜ ሞዴል ፈተናውን በቴሌግራም ቻናል ወደ ተማሪዎች ያደረስን ቢሆንም ተማሪዎቹ ጋር ግን ለመመለስ ለረጅም ሰዓት እየቆየ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ይሄን ይበሉ እንጂ ተማሪዎቹ ላይ ግርታ ተፈጥሮ ወይንም በጥልቀት እየመረመሩት ሊሆን እንደሚችል በመገመት፣ ከባድ ብለን ላሰብነው ጥያቄ በአፍሪ ኸልዝ ማብራሪያ እና መልስ እየሰጠን እየደገፍናቸው ነው በማለት አክለዋል።
እንደ ዳኜ ገለጻ፣ ይሄ ይደረግ እንጂ ተማሪዎች ራሳቸውን ከማዳበር እና ከመመዘን ባሻገር በቴሌግራም ቻናል የተላለፈው ሞዴል ፈተና ውጤት የሚሰጥበት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
‹‹በተጨማሪም ትምህርቱ እና የፈተናው ስርአት ለኹሉም ተደራሽ ይሆናል ወይ›› የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እየመጣብን ነው ያሉት ዳኜ፣ አሁን የኮሮናን ስርጭት ለመከላከል እና ያለውንም ንክኪ ለመቀነስ ታስቦ ይሄ መደረጉን አስረድተዋል። ‹‹እንደ ቀድሞው ሊሆን አይችልም። ነገር ግን እኛ በራሳችን አብዛኛውን ተማሪ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራን ነው።›› ብለዋል።
በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አካባቢ የሚገኝ ማርች 8 የተባለ ትምህርት ቤት ልጃቸውን የሚያስተምሩ ወላጅ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ‹‹የዘንድሮ ፈተና ልጄ እንዴት እንደሚፈተን አላውቅም። እስከ አሁንም ቤት እንዲቀመጡ በታዘዙት መሰረት ቤት ሆኑ እንጂ እያጠኑ አይደለም። የተለያዩ ፈተናዎች እና ትምህርት ነክ ጉዳዮች ይሰጣሉ ይባል እንጂ ልጆቹ ጋር እየደረሰ አይደለም›› ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ የዘንድሮ ፈተና እንዴት መዝንው እንደሚያሳልፉም ግልፅ ባለመሆኑ ልጆቹም ጭንቀት ላይ እንደሆኑ እና ቢቻል ተላልፎ ለሚቀጥለው እንደ መደበኛው ተምረው ቢፈተኑ መልካም እንደሆነ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወረዳ 01 ቃለ-ሕይወት ትምህርት ቤት ነው ልጄ የሚማረው የሚሉት ወላጅ፣ ትምህርት ቤቱ የግል መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹ልጆቻችን ቤት ውስጥ ስለሚውሉ መንግሥት በሚዲያዎች የሚያስተላልፈውን ትምህርት እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረት እየተከታተሉ አይደለም። እና ሌላ አማራጭ ወደ መውሰድ ቢኬድ ጥሩ ነው፣ ልጆች እውቀቱንም እያገኙ ለውጤትም መሥራት እንደሚችሉ›› በማለት ጠቁመዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012



