‹‹ብልህ ከሞኝ ውድቀት ይማራል››

0
324

በበርካታ የዓለም አገራት የወራት ዕድሜ ቢያስቆጥርም ቅሉ በርካቶችን ሕይወት በአጭር አስቀርቶ ያለፈው እና አሁንም ከባድ ጉዳት እያደረሰ ሚገኘው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የዓለም ስጋት ከሆነ ዋል አደር ብሏል። ይህንም ተከትሎ በበርካታ አገራት ከቅድመጥንቃቄ ጉድለትም ሆነ ከፍተኛ ጥደንቃቄ ባደረጉት ላይ በሚፈጠር አነስተኛ ንዝህላልነት ወይም ደግሞ ጥቃቅን ስህተት በርካታ ዋጋ የከፈሉ አገራት ጥቂት አይደሉም።

በጥንቃቄ በኩል ቅድሚያ የምትጠቀሰው ወረርሽኙ የጀመረባት አገር ቻይና ከወረርሽኙ የትውልድ መንደር በሆነችው ውሃን ከተማ ከፍተኛ የሆነ ቅድመ ጥንቃቄ ያደረገች ሲሆን በዚህም ረገድ ጥንቃቄው ውሃን ከተማን ሙሉ በሙሉ ከቀሪው የቻይና ግዛቶች ጋር እንዳትገናኝ መዝጋት ነበር። በዚህም መሰረት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወረርሽኙ አለምን ባዳረሰበት ከፍጥነት እና ስፋት በቻይና ውስጥ ግን ያልደረሰባቸው ግዛቶች እንደነበሩ እና አሁንም ድረስ መኖራቸው ተገልጿል። በቻይና መንግስት የተወሰደው ይኸው ጥብቅ እርምጃ ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ከመግታቱ በተጨማሪ እንደ ወረርሽኙ መገኛ አገር እና እንቅስቃሴ ግዝፈት ወረርሽኙ የከፋ አደጋ ሳያስከትል በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወቃል።

የቻይና ጥንቃቄ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ወረርሽኙ በጀመረበት ወቅት ፈጥነው በረራቸውን ያገዱ አገራት መኖራቸው የሚታወስ ሲሆን ቻይናም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወደ አገሯ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ለማገድ መገደዷ የሚታወስ ሲሆን እንደ ምክንያትም ያስቀመጠችው ነገር ከአገር ውስጥ ወረርሽኙ ስርጭት ይልቅ ከውጭ አገራት የሚገቡ ሰዎች የሚያሰራጩት ይበልጣል የሚል ነበር። ይህ ታዲያ ቻይና ወረርሽኙን ለመግታት ሔደችበት ፍጥነት ከስርጭቱ አያሌ ጊዜ በላይ መቅደሙን የሚያሳይ ነው።

ሌላው ቀርቶ ጎረቤት አገር ኤርትራ በማይታመን ፍጥነት ወረርሽኙን በመቆጣጠር 39 የሚሆኑ ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት ቢሆንም ከመንግስት በተወሰደ አፋጣኝ እርምጃ የዜጊች እንቅስቃሴ እና የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዲገታ በመደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙም ሳይዛመት የተያዙትም አገግመው ባሳለፍነው ሳምንት ምንም ሞት ሳይመዘገብ 39ኙም አገግመው መውጣታቸው ይፋ ተደርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአውሮፓዊቷ አገር ኢጣሊያ የተደረገው ከዚህ የተለየ ነበር። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ካለችው አገር ውስጥ ኢጣሊያ ግንባር ቀደም አገር ነበረች። በዚህ ወቅት ታዲያ ወረርሽ በኢጣሊያ የተለያዩ ክፍሎች ተሰራጭቶ እስኪስፋፋ ድረስ ምንም አይነት ከዜጎችም ሆነ ከመንግስት እርምጃ ወይም ጥንቃቄ አልተወሰደም ነበር። እንዲያውም የተገላቢጦሽ በሆነ መንገድ በቡድን መዝናናት፣ በደቦ መኖር እና የእለት ተዕለት ተግባርን ማከናወን በኢጣሊያ የተለመደ ነበር።

ይህንም ተከትሎ ሰዎች መሞት እና በቫይረሱ ተይዘው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ሲገቡ እንኳን ከመንግስት እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም ነበር። ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በኹሉም አካባቢዎች ተሰራችቶ ኢጣሊያ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰች ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ወረርሽኙ በአስፈሪ ሁኔታ በተዳረሰበት ወቅት መንግስት ኹሉም ዜጎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ እና የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ እንዲገደብ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። ነገር ግን በሽታው አስቀድሞ በሰዎች ዘንድ ደርሶ ነበርና ዜጎች እንደያዙት በቤታቸው ገብተው ተቀመጡ በዚህመሳቢያ ከአንድ ቤት የከፋ አደጋ ደርሶ በርካታ ሰዎች ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሕይወታቸውን አጥተው ለቀባሪ ሲያስቸግሩ ተመልክተናል። በመጨረሻም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ወደ ሕዝብ ብቅ በማለት ከሰማይ በታች ያለውን አማራቾች በሙሉ መሞከራቸውን እና ከዚህ በኋላ ከፈጣሪ የሚጠብቁት መፍትሔብቻ የኢጣሊያን ዕጣ ፋንታ ይወስናል እስከ ማለት ደርሰው ነበር።

ከመዘናጋት እና ለወረርሽኙ ትኩረት አለመስጠት ወይም የሚወሰደው እርምጃ የሚያደርሰውም ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትርፎችን እና ኪሳራዎችን አስልቶ ለእርምጃ መዘግየት ማንወጣው ደረጃ ላይ እንደሚያደርሰን ከአገራት ልምድ መውሰድ ይገባናል።

በቅርቡ በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት ወደ ሕዝቡ የደረሱ በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎችን በሚመለከት የወረርሽኙን ስርጭት በወፍ በረር የተቀመጠበት አጋጣሚ ነበር። በዚህ ወቅት ታዲያ የልደታ ክፍለ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረርሽኙ ከሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎች በተለየ በስፋት የተስተዋለባቸው እንደሆነ ተገልጿል። በተለይም ደግሞ በልደታ ክፍለ ከተማ ከኹሉም የባሰ እንደሆነ እና በአንድ ፖሊስ ጣቢያ በሚገኙ ታራሚዎች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ደግሞ የክፍለ ከተማውን ወረርሽኝ ስርጭት ከፍ ያደርገዋል።

ይህን የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ እና ሪፖርቶች ታሳቢ በማድረግ መንግስት አስፈላጊውን እና ጥብቅ እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ምናልባትም ስርጭቱ የበዛበትን የከተማዋ አካባቢ እስከ መዝጋት እና ከልሎ እስከ ማቆየት የሚደርስ እርምጃ እንዲወሰድም አዲስ ማለዳ ትወተውታለች። ምክንያቱም ደግሞ ዛሬ በቸልታ ያለፍነው ሪፖርት ነገ ከአደጉት አገራት ያልተማርን እና ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈሉት አገራት እኛም እንዳንከፍል አዲስ ማለዳ ስጋቷን ከጥቆማ ጋር ትገልጻለች። ‹‹ብልህ ከሞኝ ውድቀት ይማራል›› እንዲሉ በነበራቸው ንዝህላል እርምጃ በርካታ ዜጎቻቸውን እንደ ዋዛ ወደ መቃብር ከሸኙ አገራት ተርታ እንዳንመደብ በአስቸኳይ ከእስካሁኑ የሚበልጥ እና በጥንቃቄ የተሞላ እርምጃ ከመንግስት ወገን እንዲወሰድ አዲስ ማለዳ አበክራ ታሳስባለች። እንደ አደጉት አገራት ይህ ነው የማይባል የምጣኔ ሀብት ክምችት የሌላት አገራችን ኢትዮጵያ የሚሰራውን እና አምራቹን ወጣት ወደ አፈር ከሚወስደው ወረርሽኝ ልንታደገው የሚገባው አስቀድመን ቁርጠኛ እርምጃዎችን በመውሰድ እንጂ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ በመገታቱ ሊታጣ የሚችለውን ኪሳራ በማሰብ እና በማስላት እርምጃን ከመውሰድ እንዳንቆጠብ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

አንድን አካባቢ ወይም መንደር ለይቶ ወረርሽኙ በምን ያህል ግዝፈት እንደሚሰራጭ ማወቅ ከባዱ ነገር ሆኖ ሳለ ይህ በመንግስት አካላት እና ባለ ድርሻ አካላት ዘንድ ከታወቀ ቀጣዩን እርምጃ ለመውሰድ ምንም ያህል አዳጋች እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ወረርሽኙ በርትቶባቸው ነዋሪዎቹን በሚያጠቃበት አካባቢ በሙሉ አካባቢውን ከውጭ አካባቢ ግንኙነት መከለል እና ወረርሽኙን መግታት በኋላ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ እና በኹሉም ሰው ውስጥ ከተገኘ በኋላ ቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ማስገደድ የኢጣሊያ አይነት ዕጣ ፋንታ የማይገጥምበት ምንም አይነት ምክንያት የለም።

በዚህም መሰረት መንግስት የትኛውንም አይነት አስቸጋሪ ውሳኔዎች በመውሰድ ወረርሽኙን ስርጭት መግታት ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ሊመጣ የሚችለው ጫና በድህነታችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ድቀት እና ምናልባትም ተመልሰን ለማንሰራራት በርካታ አመታትም ላይበቁን ይችላሉ። በመሆኑም አዲስ ማለዳ ለሚመለከታቸው መንግስት እና ባለድርሻ አካላት ጥብቅ እረምጃ በተለይም ደግሞ ቫይረሱ በስፋት ተሰራጭቶባቸዋል በሚባሉ ስፍራዎች ላይ ሊወስድ እንደሚገባ ታስገነዝባለች። በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የወረርሽኙ ማፈትለክ አካባቢውን ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያን ለማዳረስ ጥቂት ቀናት በቂው ስለሚሆን አካባቢን በጠቅላላው ከልሎ ማስቀመጥ እና ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here