የቤኒሻንጉል ክልል መንግሥት የ20 ባለሀብቶችን የመሬት ፈቃድ ነጠቀ

0
390

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የሥራ እንቅስቃሴ በመገምገም የ20 ባለሀብቶችን ፈቃድና የመሬት ውላቸው መሰረዙን የክልሉ የአካባቢ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአካባቢ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ገለታ ኃይሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የሥራ እንቅስቃሴ በመገምገም የወሰዱትን መሬት ለታለመለት ዓላማ ባለመዋሉና አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ሆነው ስለተገኙ፣ 18 የእርሻና 2 በእጣን ማምረት የተሰማሩ የኢንቨስትመንት ባለሀብቶች ፈቃድና የመሬት ውላቸው እንዲሰረዝ መደረጉን አስታውቀዋል።
በክልሉ አንድ መቶ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው ውል በመግባት 8 ሺሕ 376 ሔክታር መሬት ለእርሻ ኢንቨስትመንት በሚል የተረከቡ ባለሀብቶችም፣ መሬቱን ለታለመለት ዓላማ እያዋሉት ባለመሆኑ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል ተብሏል። መሬቱም በቀጣይ የማልማት አቅም ላላቸውና መስፈርት አሟልተው ለሚቀርቡ እንደሚሰጥም ተጠቅሷል።
11 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ደግሞ በቀጣይ በገቡት ውል መሰረት የታዩባቸውን ክፍተቶች በመቅረፍ እንዲያለሙ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተጠቁሟል። ባለፉት ዓመታት እርምጃ በተወሰደባቸው 13 ፕሮጀክቶች ተይዞ የነበረው 5 ሺሕ 385 ሔክታር መሬት በባንክ እዳ ተይዞ መቆየቱም ተገልጿል።
አሁን ላይ በባንክ ዕዳ ተይዞ የነበረውን መሬት ጨምሮ 10 ሺሕ ሔክታር መሬት የማልማት አቅም ላላቸው ባለሀብቶች ለመስጠት ክልሉ ዝግጁ ማድረጉንም አመላክተዋል።
ክልሉ ከ56 ሺሕ ሔክታር በላይ የእርሻ መሬት በኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ተዘጋጅቶ ያለ በመሆኑ፣ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here