ኢትዮ ቴሌኮም ለዐሥር ዓመታት ባለቤት ‘አልባ’ ሕንፃዎች መከራየቱ ታወቀ

0
437

ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ቸርችል ጎዳና አካባቢ በሚገኙ ባለቤታቸው በውል የማይታወቁ ሁለት ሕንፃዎች በካሬ ከ300 እስከ 400 ብር እየከፈለ ለዐሥር ዓመታት መከራየቱ ታወቀ። አዲስ ማለዳ ሕንፃዎቹ በሚገኙበት አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በአካል በመገኘት ሁለቱ ባለ አራትና ስምንት ፎቅ ሕንፃዎች በአንድ ግለሰብ ባለቤትነት ሥር እንደሆኑና ባለቤቱም በውል እንደማይታወቁ አረጋግጣለች።
ኢትዮ ቴሌኮም ባለ አራት ፎቁን ሕንፃ ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊት በጊዜው ለነበረው “ትርንስፎርሜሽን ፕሮግራም ኦፊስ” እንዲሁም ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃውን ደግሞ ከአምስት ዓመት በፊት ለጥሪ ማዕከልነት እንደተከራየው ለማወቅ ተችሏል።
የሕንፃዎቹን ባለቤት ኃይለሥላሴ እንደሚባሉ እና ከሥማቸው ውጭ በፎቶም ሆነ በአካል አይተዋቸው እንደማያውቁ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሕንፃዎቹን ኢትዮ ቴሌኮም ከተከራያቸው ረጅም ጊዜ ስለሆነው እና ሕንፃዎቹንም የሚያስተዳድረው ኢትዮ ቴሌኮም ስለሆነ ኢትዩ ቴሌኮም ገዝቷቸዋል እስከማለትም ደርሰው እንደነበር አክለዋል።
አዲስ ማለዳ ለኢትዮ ቴሌኮም በጽሑፍ እና በቃል መረጃ እንዲሰጣት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም መሥሪያ ቤቱ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርቷል። የመሥሪያ ቤቱን ሕንፃዎችን የሚያስተዳድረውን “ፋሲሊቲ” የተባለውን ክፍል እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደተባሉት የድርጅቱ “ኮንትራት” ክፍል እና ቺፍ ኦፍ ስታፍ ጨረር አክሊሉ ቢሮ በተደጋጋሚ ብንመላለስም አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም። በተጨማሪም የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ብንሔድም መረጃ የሚሰጥ ኃላፊ ማግኘት አልተቻለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here