ለአዲስ አበባ የመጀመሪያ የሆነው ሐያት ሆስፒታል 95 በመቶ ድርሻ ለታዋቂው ኢትዮጵያዊው ባለሀብት ድንቁ ደያስ በ130 ሚሊየን ብር ገደማ መሸጡን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ምንጮች አረጋገጠች።
በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ሆስፒታሉ ወደ 208 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ከተመሠረተ ሁለት ዐሥርት ዓመታት ይሆናል።
የድርጅቱ ባለቤት የሆኑት ኢብራሒም ናውድ የሆስፒታሉ የተከፈለ ካፒታል ከ32 ሚሊየን ብር ወደ 132 ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ማደጉን ተከትሎ 95 በመቶ ድርሻቸውን ለድንቁ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለመሸጥ የመጨረሻ ሥምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ አልጋዎች ያሉት ሆስፒታሉ ከ200 በላይ ተማሪዎች አሉት። ግዢውንም ተከትሎ የመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል እንደማይፈጠር በድንቁ የተሾሙት የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ረታ በቀለ ገልጸዋል።
በያዝነው ወር መጨረሻም፤ 118 ተማሪዎችን ከዚህ ቀደም የተመዘገቡና ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትው ውጤታማ የሆኑ 118 ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ ኃላፊው ገልጸዋል።
ከቀድሞ ባለቤቱ ኢብራሂም እጅ ከወጣ በኋላም ሆስፒታሉ የአሁን ሥሙን ይዞ እንደሚቀጥል በፊርማው ሥነ ስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚያ ባሻገር ሆስፒታሉ በአዲሱ ባለቤቱ የማስፋፋት ስራ እንደሚያከናውን ተገልጿል። የሆስፒታሉ አስተዳደር በቀለ ታደሰ ከ 60 እስከ 70 ተጨማሪ አልጋዎች ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጨምሩ ገልጸዋል።
በሥሩ 5 ድርጅቶችን ያቀፈው ‹‹ሶሩማ ፋን ቢዝነስ ግሩፕ›› ባለቤት የሆኑት ባለሀብቱ ድንቁ አዳማ የሚገኘው ሪፍት ቫሊ ሆስፒታልን ጨምሮ በሕክምና ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ በግዢው ተፅዕኗቸውን ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።
ባለሀብቱ በአሁኑ ወቅት ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ፣ ሪፍት ቫሊ ሆስፒታል፣ ናፍያድ ት/ቤት፣ ቀርሺ ማይክሮፋይናንስ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ናቸው።
በተጨማሪ፤ ባለፈው ዓመት ባለሀብቱ ሶደሬ ሪዞርትን ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት መግዛታቸው አይዘነጋም። ቀደም ብሎ ሴንትራል የጤና ኮሌጅን ከቀድሞው ባለቤቱ አብነት ግርማይ መግዛታቸው አይዘነጋም።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011