አፍሪካ ‹‹ተኩስ የማይሰማብሽ ምድር?!››

0
1171

አፍሪካ ድህነት፣ ሰላም ማጣት፣ ረሀብና ችግር ተባብረውና ተዳብለው የሚያባዝኗት አኅጉር ናት። የቅኝ ግዛት ያዛለው ጉልበቷን መጠገኛ፣ ለችግሯ መላ መፈለጊያ መድረክ ስትሻ በውስጧ ያሉ በርካታ አገራት ኅብረትን መሠረቱ። ይህም ዘንድሮ ለ57ኛ ጊዜ በአፍሪካ ቀን መታወሱን ያነሱት አብርሐም ፀሐዬ፣ ተኩስ እንዳይሰማባት፣ ኮሮናንም በጽኑ እንድትታገል የሚያበረታ ቃል ከኅብረቱ መሪዎች ተሰምቷል ይላሉ። እአፍሪካን ተኩስ የማይሰማባት አኅጉር ለማድረግ ግን ሊኬድባቸው የሚፈልጉ ከባድ እርምጃዎች እንዳሉ ዘርዝረው ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ክፍሉ የአፍሪካ ቀን ሲከበር ዋና አሰናጅ እሱ ነው። ዘንድሮ አፍሪካ ተኩስ የማይሰማባት ምድር እንድትሆን መሪ ቃሉን እነሆ በረከት ብሏል፤ ለአፍሪካውያን።

ዘንድሮው የአፍሪካ ቀን ግንቦት 18 (ሜይ 25) ሲከበር ኮሮናንም አጀንዳ አድርጎታል። በወረርሽኙ ምክንያት ባይሆን ኖሮ በአፍሪካውያን ብዝኀነት የደመቀ ትውፊት፣ ባህልና የአመጋገብ ስርዓት ማሳያ በይፋ ተዘጋጅቶ ይከበር ነበር። የ2020ው ግን በአመዛኙ በኢንተርኔት ኮንፈረንስ የታለፈ ነው። የዚህ ዓመት የኅብረቱ መሪ ቃል ሙሉ ሐሳቡ ‹ለኮሮና ትኩረት እንስጥ፣ ተኩስም አይሰማብን› የሚል አንድምታ ይዟል። ጥሩ ይመስላል!

አፍሪካ ተኩስ አይሰማብሽ ስትባል ከቅዱሳን አባት አልያም ከሽማግሌ የተሰጠ ምርቃት ይመስላልና፣ ለማንኛውም አሜን እንበል።
እውነቱ ግን ወዲህ ነው። ለአፍሪካ ተኩስ ማለት የባህል ጨዋታዋ እስኪመስል ድረስ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ድረስ የሚከወን የሞት ትርዒት ነው። ቀለል ባለ ጊዜ በተራ በተራ አለያም በዙር፣ የባሰ ሰሞን ደግሞ በመደዳ ምድሪቷን ተኩስ ይንጣታል። ዜጎቿን ደም ያጥባቸዋል። አፈሯም በሬሳ የተሸለመ ነው።
ለባህል የተኩስ ጨዋታዋ ጥሩ የጦር መሣሪያ አቅራቢዎች አሉ። የጦር መሣሪያው ሲያንስም ራሳቸው አፍሪካውያን ጥሩ የባህል መሣሪያ አላቸው። ከዱላ እስከ ድንጋይ፣ ከሴንጢ እስከ ቀስት በአግባቡ ጥቅም ላይ ይውላሉ። የአፍሪካውያን የጦርነት ሜዳ ራሷ አፍሪካ ናት። ገዳይና ተገዳይ ሆነው የሚጫወቱ ተዋንያንም ራሳችን አፍሪካውያን ነን።

የጦርነት ፊልሙ የሚጻፈውና የሚዘጋጀው እንዲሁም ለዝግጅቱ ስኬት መተግበሪያ የሚሆን ጦር መሣሪያ አቅራቢዎች በብዛት አሉ። አዎ! ባህር ማዶ ያሉ አገራት ተግተው ይሠሩበታል። የግጭትና የጦርነት አቀጣጣይ አፍሪካውያን ባንዳዎች በበልቶ አደርነትና በአውርቶ አደርነት ተቀጥረው ያገዳድሉናል። በመካከላችን የተዘራው ‹የመናናቅ› እና ‹ያለመስማማት› እርግማን ደግሞ ዋነኛው ቤንዚን ነው።

የአፍሪካ ኅብረት በልደት ቀኑ ተኩስ የሚቆምባት አኅጉር ለመፍጠር የተመኘው ያለነገር አይደለም። ግጭት የወጠራት፣ ሞት የነገሠባት ምድር ለነገም ተስፋ ማጣቷ ነው። የክብረ በዓል አዘጋጆቹ በአፍሪካችን የሰላምና ልማት ጥምረት እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተውታል። የአፍሪካ ኅብረት ከመሣሪያው በላይ ለግጭት የሚጋብዙ ክስተቶችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

መሪ ቃሉ እንደሚያመለክተውና ኅብረቱም እንዳሰመረበት በእያንዳንዱ አገራት ውስጥ ከግጭቱ ጀርባ ያለውን ችግር ለማወቅ ውስጥ ድረስ በመዝለቅና በማጥናት የጦርነት ገፊ ምክንያቶች ላይ መሥራት ይገባል። እንዲሁም በተጎራባች አገራት መካከል ሰላምና ትብብር አምጪ የድርጊት መርሃ ግብር መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ተናግሮ ይህንንም ኅብረቱ እንደሚያበረታታ አሳውቋል።

የአፍሪካ ቀን አከባበር መነሻ ምክንያት
የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫው አዲስ አበባ ነው። ምሥረታውም እዚሁ ነው። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአንበሳውን ድርሻ ወስደው በመምራት በኛ አቆጣጠር በ1957 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብሎ ተመሠረተ። ይህ ቀን ሲከበር ዘንድሮ 57ኛ ዓመቱ ነው። በነገራችን ላይ በዓሉን እንደ ብሔራዊ ክብረ በዓላቸው አድርገው በይፋ የሚቆጥሩትና የሚያከብሩት እንዳሉ ይታወቃል። ጋና፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ፣ ናሚቢያ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ሌሴቶና ዚምባብዌ ናቸው።

ይህ ቀን በእርግጥም ታላቅ የነጻነት ቀን ነው። ከቅኝ ግዛትነት የተላቀቁ አፍሪካውያን በትክክልም አፍሪካ በራሷ ልትቆም እንደምትችል ያረጋገጡበት ቀን ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ መልካም ብስራት በኋላ ያለው ጊዜ ግን አንዳንዴም ከቅኝ ግዛቱ ዘመን በላይሞ የከፋ የሚመስል እንደሆነ የሚከራከሩ አሉ። የራሳቸው የቅኝ ገዢዎቹ ሴሪ መሆኑንም አንስተው የሚሞግቱ በዚያው ልክ ናቸው። ጦርነቷ የማይበርድባት አኅጉር ናት! ለምን ማለት ተገቢ ይሆናል።

አፍሪካ ንቃት የጎደለው ሕዝብና መሪዎችን የታቀፈች በመሆኑ የመከራ ቀኗ እንደረዘመ አለ። ቀድሞ ቅኝ ገዢዎቿ የነበሩት አገራት መንገዳቸውን ቀይረው ተጠቃሚነታቸውን ለማስከበር ሲሉ እየተቀራመቷት ይገኛል። በተለያየ ጊዜ በእኛም ሆነ በራሳቸው የዜና ዘጋቢዎች የሚወጡ መረጃዎች ይህንን የግፍ ሀቅ ይናገራሉ። ‹ተኩስ የማይሰማብሽ ምድር› የሚለው መሪ ቃል መፈክር ሆኖ ይቀር ይሆን ወይስ? አንድ ሁለት ስጋቶችን እናንሳ።

የሞት ነጋዴዎቹ ግብይት በአፍሪካ
(የ‹ሲ ኤን ኤን ፍሪደም ፕሮጀክት› የምርመራ ዘገባ)
ኮባልት የተባለው ማዕድን ለስማርት ፎን፣ ለላፕ ቶፕና በኤሌክትሪክ ለሚሠሩ መኪኖች በኃይል ምንጭነት የሚጠቅም ንጥረ ነገር የያዘ ነው። ዴሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ በዚህ ሀብት የታደለች ናት። ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱትን ጨምሮ በተፈጥሯቸው ምክንያት በጉልበት ያልዳበሩ ሴቶች በማዕድን ማውጣት ሥራው ላይ ተሰማርተውበታል። በየቀኑ ለረዥም ሰዓት በከባድ የጉልበት ምዝበራ ላይ እንደሚያሳልፉ የምርመራ ዘገባው ይፋ አደረገው።

ሰንሰለቱ እስከመንግሥት ባለሥልጣናት እጆች ድረስ የረዘመ፤ እስከ ምዕራባውያኑ ግዙፍ ኩባንያዎች ድረስ የተዘረጋ ነው። በአካባቢው ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር በዋለው ስፍራ ማዕድኑ እንደጉድ እየወጣ በጥቁር ገበያ ይቸበቸባል። የጉልበት ሠራተኞች በዚህ ትልቅ ጉድጓድ ተጥደው ኑሯቸውን ይገፋሉ። ሴቶቹ ለወሲብ ባርነት ጭምር ይዳረጋሉ። እዚያው ወልደው እዚያው አሳድገው ሕጻኑ ያለዕድሜው በቁፋሮው እስከመሠማራት የሚደርስበት ግፍ ታይቷል።

ይህ ተፈላጊ ማዕድን በዓለም ዙሪያ በተለይም እኛ አፍሪካውያን ጆሯችን ላይ ያለው ስልክ እና የምንነካካው ላፕ ቶፕ በራሳችን በአፍሪካውያን ወገኖች የግፍ ላብ የወረዛ መሆኑን ማሰብ ያማል። የኮንጎ ጦርነት እንዳይቆም ሲባል ለታጣቂዎች በገፍ የሚቀርብ ጦር መሣሪያ አለ። ጦርነቱ ሲቀልጥ፣ የማዕድን ገበያው እየወጣ ወደፈላጊው አካል ይሻገራል።

የምርመራ ዘገባው የማዕድኑ ገዢዎችን ይፋ አድርጎ ነበር። ጎግል፣ ቴስላ፣ ማይክሮ ሶፍት፣ ዴል እና አፕልን የመሳሰሉ ተቋማት ናቸው። አስደንጋጭም አሳፋሪም ነበር። ሥመ ጥሮቹ የግፉ ፊታውራሪ ናቸው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ለፍርድ ይዘው ቀርበዋል። እናቶችና ሕጻናትን ለአላስፈላጊ የጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ለሞት በመዳረግ የሚከወን ግብይት ሕገ ወጥ ነው በሚል ተከሰዋል።

ኩባንያዎቹ እኛ ከሕጋዊ አቅራቢ ነው የምንገዛው የሚል ውሃ የማያነሳ ምክንያት እያቀረቡ ተሟግተዋል፤ ጉዳዩ ግን ሌላ ነው። አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ከእኛ ከአፍሪካውያን በላይ ነጮቹ ያውቁታል። ይጠቀሙበታል። በመሐል ስለሚኖረው ሞት አያገባቸውም። የሞት ነጋዴዎቹ ኩባንያዎች ለአማጺያኑ ድጋፍ ያደርጋሉ። ለገበያቸው የማይመች መንግሥት ያለባትን አገር ለማስወገድ ተጻራሪ ኃይላትን ያግዛሉ። የጦር መሣሪያ መግዣ ዶላር በተዘዋዋሪ ያቀርባሉ።

ዘመን በገንዘብ በሚመራበት ዓለም ለአፍሪካ ትልቁ የቤት ሥራዋ ከዚሁ አቅም ጋር የተያያዘ ነው። ያላትን አንጡራ ሀብት ጠብቃ ዜጎቿን ተጠቃሚ ማድረግ የአፍሪካ ኅብረት ‹ተኩስ አልባ አኅጉር እንፍጠር› ያለውን ለመተግበር ወሳኙ ነው። ነገር ግን የአፍሪካ ኅብረት የዘንድሮ ቃል እሱ እንዳለው ምን ያህል ለመተግበር ይቀል ይሆን?

የተረሳው ጦርነት በአፍሪካ
የየመንን ጦርነት ዓለም ረስቶታል ይባላል። ዜናው ራሱ አልፎ አልፎ ካልሆነ አባ ከና የሚለው የለም። ሞቱ ግን ትላንትም ነበር፣ ዛሬም አለ። ተፋላሚዎቹ ሌላ ናቸው፤ ሟቾቹ ግን አፍሪካውያን! አፍሪካ እንዲህ ናት። የዝሆኖቹ ጥል የሚያደቃት ሳር።

ሬውተርስ ከሦስት ዓመታት በፊት ይዞት በወጣው ዜና ላይ ኹለት የእንግሊዝ የጦር መሣሪያ ሻጮች ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የእንግሊዝ መንግሥት ከሷቸዋል ይል ነበር። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ለሳዑዲ አረቢያ በሸጡት የጦር መሣሪያ ወደ ስድስት ቢሊየን ዩሮ ገቢ አግኝተው ከዚያ ላይ የሚጠበቅባቸውን ባለመክፈላቸው የተፈጠረ ነው። ሽያጩ የተከናወነው ደግሞ ሳዑዲ የመን ላይ ለከፈተችው ጦርነት የሚውል የጦር መሣሪያ አቅርቦትና ሥልጠና ነው።

እንደተለመደው ሰብዓዊነት ይመለከተናል የሚሉት ተቋማት እነዚህ የእንግሊዝ የግል ድርጅቶች በንጹህ ሕጻናት ሞት ያገኙት ብር አንድ ነገር ሊባል ይገባዋል ሲሉ የዚያ ሰሞን ጮኸዋል። የአፍሪካ ጩኸት ግን ሁሌም ይቀጥላል።

መደምደሚያ
ለጊዜው ተመስገን ነው። በንጽጽር የኮሮና ወረርሽኙ ጉዳት የከፋ እንዳልሆነ ተነግሯል። ከዚያ በኋላ ግን የሚጋረጥ አደጋ አለ። በኮሮና ምክንያት የምጣኔ ሀብቱ እንቅስቃሴ የሚፈጥረው መድቀቅ የሚያስከትለው ጣጣ አዘቅቱ ከባድ እንደሚሆን ተተንብይዋል። ወገብ ጠበቅ የሚያደርግ ሌላ ከባድ ሥራ አለ ማለት ነው።
ያም ሆነ ይህ የአፍሪካችን ምጣኔ ሀብት የሚበለጽገውና ፖለቲካዊ መረጋጋት የሚመጣው በንቃት እንጂ በሌላ አይደለም። በአፍሪካዊነት እውቀት የዳበረ፣ በተቀናጀ አብሮነት የደረጀ ኅብረት ለአፍሪካ ያስፈልጋታል። ባላት የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ምጣኔ ሀብቷ አብልቶ ከማሳደር በላይ ለዓለም ገበያ ይተርፋል። ለዚህ ደሞ ሰላምና አብሮነት ግድ ይላል።

አፍሪካችንና አፍሪካውያን ወደራሳችን ተመልሰን ልናይ ይገባል። እንደምናውቀው ባህር ተሻግረው የሚመጡ ክፉ ቀመሮች አሉብን፤ የርዕዮተ ዓለም መርዝ በየብልቃጡ ያቀምሱናል። ስለሆነም ረጃጅሞቹ የምዕራባውያንና የሩቅ ምሥራቅ እጆች በልኩ እስካልሆኑ ድረስ ለአፍሪካ ራሷ አልማ በራሴ እሠራለሁ ማለት ዘበት ነው። የተኩስ ድምጹም አይቆምም። በተለይም በድጋሚ ማስታወስ የሚያስፈልገው የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትን እንዲሁም ግጭት ቀስቃሽ ጉዳዮችን ከስሩ መፈተሽና መነጋገር በአግባቡ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው።

አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here