በአማራ ክልል በ2011 በመምህርነት ሙያ የሠለጠኑ እጩ መምህራን ቅጥር አልተፈጸመልንም አሉ

0
571

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2010 በተለያዩ ትምህርት መስኮች የተመርቁ ተማሪዎችን በ2011 በመምህርነት ሙያ አሠልጥኖ ቢያጠናቅቅም እስከ አሁን ቅጥር እንዳልተፈጸመላቸው እጩ መምህራኑ አስታውቀዋል።

ሥልጠና ያገኙ አስተያየት ሰጪ እጩ መምህራኑ፣ ትምህርት ቢሮው ከሥልጠና በኋላ እንደሚቀጥረን ቢገልጽልንም እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ባለመቀጠራችን ለእንግልት ተዳርገናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ‹ጠብቁ ቦታ ሲገኝ እንመድባለን› እንደተባሉና አንዳንዶቹ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች ደግሞ ‹በጀት የለም› እንዲሁም ‹ምደባ መሥራት የቢሮው ግዴታ አይደለም› እያሉ መፍትሔ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ከክልሉ ምለሽ በማጣታቸውም ወደ ፌዴራል መንግሥት በመምጣት ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ጉዳያቻው እንዲታይደላቸው ጠይቀው እንደነበር ጠቅሰዋል።

በዚህም ‹‹የክልሉ ችግር ነው። ሊመድቧችሁ ይገባል። መንግሥት በጀት ወጪ አድርጎባችኋል፣ እናተም አንድ ዓመት ሙሉ ጊዜአችሁን አባክናችኋል። ስለዚህ ክልሉን ክሰሱ›› በማለት የኢፌዴሪ የመምህራንና ትምህርት አመራር ዳይሬክተር አሰፋሽ ተካልኝ ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የክልሉን የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢዘንን አናግራ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዲህ አይነት ቅሬታ አልቀረበለትም እንዲያውም መረጃውም የለውም በማለት አስተባብለዋል። ምንም እንኳን ቅሬታው አንዳልቀረበላቸው ቢገልጹም፣ ቅጥር ያልተፈጸመላቸው ያሉ ቢኖሩ እንኳን በክልሉ መምህራን የሚፈልጉ ክፍት ቦታዎች ባለመኖራቸውና ከበጀት እጥረት ጋር የተያያዘ እንደሚሆን አንስተዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የሕዘብ ግንኙነት ኃላፊ ሀረጓ ማሞ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያውቀው የክልሉ ትምህርት ቢሮ እጩ መምህራኑን ምደባ እንዳከናወነ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም ከዚህ በፊት በክልሉ ክፍት ቦታ ሲጠፋ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ወደ አጎራባች ክልሎች ሄደው እንዲቀጠሩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ነገር ግን እንደዚህ መቀጠል እንደሌለበትና ያልተቀጠሩ ካሉ ተለይተው፣ የበጀት እጥረትም ከሆነ ተጨማሪ በጀት ተመድቦ መቀጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል። በጉዳዩ ላይ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር እንደሚነጋገሩም ተናግረዋል።

ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ቅሬታ አቅራቢዎች የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ በ2010 በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተመረቁትን በመምህርነት ሙያ በ2011 መሠልጠን የምትፈልጉ ብሎ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን አወዳድሯል። ተወዳድረው ካለፉ በኋላ ምንም አይነት የኪስ ክፍያ እንደሌለው፣ ነገር ግን ሥልጠናውን ያጠናቀቁትን በሙሉ በክልሉ ባሉ ክፍት ቦታ ምደባ እንደሚያከናውን በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸላቸው አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ሥልጠናውን ያጠናቀቁትን የተወሰኑትን እጩ መምህራንን በመመደብ የተወሰኑትን ደግሞ ከምደባ ውጭ ተደርገው እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን፤ በሌሎች ክልል ያሉ ባልደረቦቻቸው ክልሎች በገቡት ቃል መሰረት ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ቅጥር ተሠረቶላቸው በሥራ ላይ መሆናቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ጠቅሰዋል። ‹‹የአማራ ክልል ግን የገባውን ቃል ሳይፈፅም በመቅረቱ እጩ መምህራን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን›› ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ።

አዲስ ማለዳ በአገሪቱ ስላለው የመምህራን ብዛትና ምጣኔ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲን (ዶ/ር) አነጋግራ በኢትዮጵያ የመምህራን እጥረት እንዳለ ተናግረዋል። ዮሐንስ ለዚህ ማሳያ የሚሉት ደግሞ ለትምህርት ጥራት ማነቆ የሆነው መምህራንን ከተማሩት የትምህርት መስክ (ባልተመረቁበት ትምህርት) ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን ደርበው እንዲያስተምሩ ማድረግ በአገሪቱ የተለመደው ተግባር አንደኛው ማሳያ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here