ለሕዳሴ ግድብ በዐሥር ወራት እንዲሰበሰብ ከታሰበው ገቢ ግማሹ ብቻ መሳካቱ ተገለጸ

0
602

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማካሔጃ ከሕዝብ ከሚሰበሰበው ገቢ በበጀት ዓመቱ ለማሳካት ከታቀደው የገንዘብ መጠን በዐስር ወራት ውስጥ ማሳካት የተቻለው ግማሹን ብቻ እንደሆነ ተገለጸ።

እየተጠናቀቀ ባለው 2012 በጀት ዓመት የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ለመሰብሰብ ካሰበው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በዐስር ወራት ውስጥ መሰብሰብ የቻለው 605 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ምክር ቤቱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታሰበውን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ እንቅስቃሴዎች በመገታታቸው ምክር ቤቱ ለማዘጋጀት ያሰባቸውን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ማከናወን አልቻለም። በመሆኑም የታሰበውን ያህል ገቢ ለማሳካት አስቸጋሪ ሆኗል።

የታሰበውን ገቢ ለማሳካት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴ መገታት ባሻገር እንቅፋት የሆነው የባለሀብቱ ተሳትፎ በእጅጉ በመቀነሱ እና ለህዳሴ ግድቡ በድርጅቶችና በባለሀብቶች የተገቡ ቃሎች መፈጸም ባለመቻላቸው እንደሆነም ኃይሉ ጨምረው ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የግድቡን ዘጠነኛ ዓመት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ሊያዘጋጀው የነበረው ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማከናወን ባለመቻሉ ትልቁን ገቢ እንዳጣ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው አውስተዋል።

ለግድቡ አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያ በሆነው በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት በበጀት ዓመቱ ለህዳሴ ግድቡ በቀን አንድ ብር ለመለገስ ከ500 ሺሕ በላይ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ባለፉት ኹለት ወራት ውስጥ በ8100 ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል። እንደ ኃይሉ ገለጻ፣ አሁን ላይ ለህዳሴ ግድቡ በስፋት ገቢ ማሰባሰብ የሚቻልበት መንገድ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ በ8100 በቀን አንድ ብር ለግድቡ በማበርከት አለኝታነቱን ማሳየት አለበት።

በተፈጠረው ድንገታዊ ወረርሽኝ እቅዱን ማሳካት ባይቻል እንኳን ወደ እቅዱ ለመቅረብ ኅብረተሰቡ ወደ 8100 በቀን አንድ ብር ለግድቡ የሚለግሰውን ኹሉም የሚችለው ስለሆነ በስፋት መሳተፍ አለበትም ብለዋል። እስከ አሁን ለህዳሴ ግድቡ ቦንድ ያልገዙ አዲስ ወደ ሥራ ዓለም የተቀላቀሉም ግድቡ ሳይጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን በማሳረፍ ሊደግፉ እንደሚገባ ኃይሉ አመላክተዋል።

በተጨማሪም ቦንድ ገዝተው የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሰ ሰዎች እና ድርጅቶች የቦንድ ግዥውን እንደ አዲስ በማደስ ለግድቡ መጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደረጉ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

በበጀት ዓመቱ የተያዘውን እቅድ ማሳካት ባይቻል እንኳ፣ ኅብረተሰቡ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ኃይሉ አስገንዝበዋል። በአሁኑ ሰዓት እንቅስቃሴ ከመገደቡ ጋር ተያይዞ ያለው የተሻለ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ 8100 በመሆኑ ምንም እንኳን ያለው ድጋፍ ከመጀመሪያው ወር የተሻለ ቢሆንም፣ ሁሉም ኅብረተሰብ 8100 ላይ <A> ብሎ በመላክ ድጋፉን ማሳየት አለበት ሲል ማስተባበሪያው መልእክቱን አስተላልፏል።

በሌላ በኩል ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ጉዳይ በግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት እስከ አሁን መቋጫ ያላገኘ ጉዳይ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ‹ግድቡ የእኔ እንጂ የግብጽ ወይም የሱዳን አይደለም፣ አባይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ነው›› በማለት በ2012 መገባደጃ ኹለት ወራት ሐምሌ እና ነሐሴ ላይ ውሃ ሙሌት ሥራ እንደሚጀመር በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ውሳኔ ላይ መድረሱ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here