የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አስነሳ

0
665

በውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ እና በሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቃውሞ ገጥሞታል። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከማንነት እና ወሰን ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና ይህንንም ተከትሎ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በማሰብ ጥናት አካሒዶ ያገኘውን የመፍትሔ ሐሳብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብ ኮሚሽን በባለ ድርሻ አካላት ተቋቁሞ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
ታኅሣሥ 11 ቀን በውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተስፋዬ ዳባ ለምክር ቤቱ በንባብ የቀረበው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ በርካታ አስተያየቶችን ከምክር ቤቱ አባላት አስተናግዷል። በዚሁ ዕለት የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ሲል ይጀምራል። መግለጫው በርካታ አንቀጾችን ከሕገ መንግሥቱ በመጥቀስ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጣረስ ገልጿል። የኮሚዩኒኬሽን ቢሮው መግለጫ በመከራከሪያነት በርካታ አንቀፆችን ቢጠቅስም በዋናነት ግን አንቀጽ 39፣ 52(2)ሀ፣ 62 እና 48 ተጥሰዋል ሲል አቅርቦ የሚንስትሮች ምክር ቤትም ሕገ መንግሥቱን ጥሷል ካለ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ባለማፅደቅ ሕገ መንግሥቱን ማስከበር እንዳለበት ተናግሯል።
በቀረበው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ ላይ ከቀረቡት ተቃውሞዎች መካከል አፅብሃ አረጋዊ “የአዋጁ መመሪያ ሒደት ትክክል መሆን ነበረበት” ሲሉ ይጀምራሉ። የሕዝብ መድረክ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ እና አጠቃላይ ባለ ድርሻ አካላት ባልተሳተፉበት ሒደት ኮሚሽን ሊቋቋም አይችልም ብለዋል። ይህ ዓይነት አካሔድ ደግሞ የክልሎችን በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን ከመግፈፉም በላይ ሕዝብን ሥጋት ላይ ይጥላል ብለዋል።
የአፅብሃን ሐሳብ የሚጋሩት የምክር ቤቱ አባል ማና አብረሃ የክልሎችን ችግር ክልሎች ራሳቸው ነው የሚፈቱት ከዛም ካለፈ በፌደሬሽን ምክር ቤት ይወሰናል እንጂ የዚህ ኮሚሽን መቋቋም አላስፈላጊ እና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብለዋል። ሌላም አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ የብሔር ብሔረሰቦችን ራስን በራስ ማስተዳደር መብት የሚፃረር ነውም ብለዋል። ሌሎች አስተያየት ሰጭዎችም እንደተናገሩት ክልሎች ከአቅማችን በላይ ሆኗል ብለው ሪፖርት ባላደረጉበት ሁኔታ የኮሚሽኑ መቋቋም የክልሎችን ሉዓላዊነት መድፈር ነው ብለዋል።
በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ላይ እንደተገለፀው ከአስተዳደራዊ ወሰኖች ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶች ተፈተው በአጎራባች ክልሎች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚታደስበትና የሚጠናከርበትን መንገድ ያመቻቻል ቢልም የትግራይ ክልል ኮምዩኒኬሽን መግለጫ ግን “ለሦስት ዓመት የሚቆይ ኮሚሽን እንደዚህ ዓይነት ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠበቅ የለየለት የዋህነት ነው” ብሎ በመግለጫው አስፍሯል።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ከምክር ቤቱ የተነሱት ሐሳቦች እንደሚያመለክቱት የኮሚሽኑ መቋቋም ኢትዮጵያ ካጋጠማት የወሰን እና ማንነት ችግሮች ለመውጣት ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለዋል። የፌደሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣን በምንም ዓይነት አይነካም ምክንያቱም ኮሚሽኑ ጥናት ካካሔደ በኋላ ይበጃል ያለውን የምፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል እንጂ ራሱ የመወሰን ሥልጣን የለውም። አያይዘውም እንደተናገሩት ሰው ሲደበደብ ሕገ መንግሥት ተጣሰ አላልንም፣ በሕገ መንግሥት ሽፋን የተካለሉ ቦታዎች አሁንም ድረስ ስላሉ የኮሚሽኑ መቋቋም ወቅታዊ ነው ብለዋል። “ብሔር ብሔረሰቦች በሠላም እንዲኖሩ መሥራት ጉዳት ያለው አይመስለኝም” ያሉት ደግሞ ሻምበል ነጋሳ ናቸው። ሕዝብን ያሳተፈ አይደለም ለሚለው ሐሳብ ደግሞ ከአንድም ሁለት ቋሚ ኮሚቴ ያሳተፈ ነውም ብለዋል። ሌላም የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ያነሱት አስተያየት “ሕገ መንግሥቱን ከለላ አድርገን ከሠራነው ሀጢያት የምንነፃበት ይሔ አዋጅ ነው” ብለዋል ። የኮሚሽኑ መቋቋም ይጥሳቸዋል የተባሉትን የሕገ መንግሥት አንቀፆች እያነሱ አስተያየት የሰጡት የምክር ቤት አባል ጌታቸው መለሰ እንደተናገሩት አንቀጽ 82 በምንም ግንኙነት እንደሌለው እና የዜጎች መብት ሲጣስ ደግሞ ኮሚሽን ማቋቋም እንደሚቻል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(7) ላይ እንደተደነገገ ገልፀዋል።
ከምክር ቤቱ ለተነሱት አስተያየቶች ጠቅለል አድርገው ምላሽ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተስፋዬ ዳባ እንደተናገሩት ሕዝብ ሳይወያይበት አዋጅ ይፅደቅ የሚል ሕግ የለም፣ ምንም አይነት አንቀጽ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጋጭም። ጥናት ለማጥናት ብቻ ከሆነ ለምን ተቋቋመ ለሚል ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ተስፋዬ ኮሚሽኑ ጥናት አጥንቶ እንዲወስን ካደረግነው ሕገ መንግሥት ይጣሳል ምክኒያቱም የመወሰን ሥልጣኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ብለዋል።
ስለማንነት እና ወሰን አስተዳደር ጋር በተያያዘ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህሩ መኮንን ፍሰሐ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእንደዚህ ዓይነት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ አዋጆች ላይ ድምፅ አለመስጠት ብቻ ሳይሆን በጉባኤውም ላይ አለመገኘት ነበረባቸው ይላሉ። አያይዘውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ አዋጅ በግዴታ ለማስፈፀም በሚሞክሩበት ጊዜ የክልል መንግሥታት መተባበር የለባቸውም ብለዋል። ይህ ደግሞ የክልል መንግሥት የፌደራል መንግሥትን ማክበር እንዳለበት የተደነገገውን ሕግ የሚጣረስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከሁለት ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በተካሔደዉ ሰልፍ ላይ የተደረጉት ንግግሮች እና እስከ አሁንም ድረስ እልባት ያልተገኘለት ከራያ እና ወልቃይት ማንነት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ግጭት ባልተለየው የትግራይ እና የአማራ ክልል ድንበሮች የበርካታ ንፁኃን ደም በከንቱ ያፈሰሰ እና ብዙዎችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው ክስተት ይህን የሚያመላክት ነበር ብለዋል። የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዩች ኮሚሽን ማቋቋሚያ ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 6/2011 በተካሔደው ድምፅ አሰጣጥ በሰላሳ ሦስት ተቃውሞ በአራት ድምፀ ተዕቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታሪክ ከ2010ሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውሳኔ ወዲህ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥም የመጀመሪያዉ ነዉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here