መነሻ ገጽአንደበትየማንነት ፖለቲካ ሰብአዊ መብትን መጠቀሚያ ያደርጋል!

የማንነት ፖለቲካ ሰብአዊ መብትን መጠቀሚያ ያደርጋል!

ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ በርካታ ለውጦች አሉ። ይህም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ አስመስግኖ ያቆየ ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆይ ግን በተለይም ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ እዛም እዚም የሚሰሙ አሳሳቢ ጉዳዮች ተስተውለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ለውጡ ወደኋላ እንዳይመለስ የሚል ስጋት የተሰማ ሲሆን፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ካነሱት መካከል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይገኝበታል። አሁንም ላይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እንዲሁም የአማራ ክልልን ማእከል አድርጎ ያወጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ብዙ ውዝግቦችን ያስነሳ ሲሆን፣ ዘገባውን በጥርጣሬ የተመለከቱት ጥቂት አይደሉም። በዚህ ሪፖርትና በጠቅላላው በኢትዮጵያ እየታየ ስላለው የሰብአዊ መብት ጉዳይ በማንሳት የአዲስ ማለዳው ተወዳጅ ስንታየሁ፣ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አጥኚ ፍስኃ ተክሌ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

ከለውጡ ወዲህ ባሉት ኹለት ዓመታት ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ተሻሽሏል ወይስ እየባሰበት ነው የመጣው?
ለውጥ የሚባል ነገር አለ። በኋላ በለውጡ ውስጥ የተደረጉ ብዙ አዎንታዊ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ተለቀዋል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጥተው መንቀሳቀስ ችለዋል፣ ከዛ ውጪ ጨቋኝ የነበሩ ሕጎች እንደ ጸረ ሽብር፣ የሚድያ ሕጉ ተቀይረዋል። በቅርብ ጊዜ ምርጫ ቦርድ ላይ እና ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ላይ የተነሱ ለውጦች አሉ። ማሻሻያ ፕሮግራሞችም አሉ።

ከእነዚህ አንጻር ብዙ ለውጥ አለ። ሚድያም ላይ ለውጥ አለ። የማይነገሩ የነበሩ ጉዳዮች በሚድያ ይነገራሉ፣ ከመሪው ፓርቲው ውጪ የማይነኩ ሐሳቦችም መንጸባረቅ ጀምረዋል። ይህ እንግዲህ ጥሩ ነገር ነው።

በቅርብ ጊዜ ግን ያየናቸው የተወሰኑ ችግሮች አሉ። ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት መታሰር ጀምረዋል፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ግልጽ ባልሆነና በማያሳምን ሁኔታ መታሰር አለ። ታረውም ለረጅም ጊዜ ቆይተው ይወጣሉ፣ ወይ በነጻ ይለቀቃሉ፣ ወይ ምህረት ይደረግላቸዋል። እነዚህ ሁሉ እንደ አዲስ መታየት ጀምረዋል። እነዚህ ያሳስባሉ። ስለዚህ ለውጥም አለ፤ የድሮውን የሚመስሉ ነገሮች አሉ። የተቀላቀለ ነው።

በድምሩስ ግን የባሰ ነው ወይስ መሻሻል የታየበት?
መሻሻል አለ ማለት እንችላለን። ብዙ ለውጦች አሉ። እነርሱን መካድ አንችልም። ግን መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው የሚታየው።

ግንቦት 21 ላይ የወጣ ሪፖርት በጣም አወዛጋቢ ሆኗል፤ ለምን ይመስልዎታል?
አንደኛ አጠቃላይ ጥናቱ ላይም እንደተገለጸው ዋልታ ረገጥ የሆነ ፖለቲካ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው። መርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በቡድን ሐሳብ ላይ የተመሠረተ እንጂ፣ የሐሳቦች ፍጭት አይደለም የምታየው። የቡድኖች ፍጭት ነው። ቡድኖችም የተፈጠሩት በሐሳብ ላይ ሳይሆን በማንነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይህ ደግሞ ኹለት ነገሮችን ይፈልጋል። አንደኛው ራስን ማጉላት፣ ኹለተኛው ደግሞ ሰለባነትን ማንሳት (Victimization) ይፈልጋል። በተፈጥሮው የማንነት ፖለቲካ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ይፈልጋል።

እናም ሰብአዊ መብትን የፖለቲካ መጠቀሚያ ያደርገዋል። እንጂ ሪፖርቱ ላይ የተቀመጡ ነገሮች ከታዩ፣ ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ናቸው። እንደ ዜጋ እንደ ኅብረተሰብንም ሊያሳስቡ የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። ምንአልባት ሊሰጡ የሚችሉ ትችቶች ቢኖሩ ችግር የለውም። ግን ትችቶቹ ይዘቱ ላይ ነው እንጂ መሆን ያለባቸው፣ ምንድን ነው ዓላማው፣ ለምን ይህን አላስገባም የሚሉና አንዳንዴም ወጣ ያሉ ሐሳቦች አሉ፣ በጣም የተፈናጠሩ። ከግብጽ ወይም ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት አለ። እንደዛ የሚሉት ሪፖርቱን ያላነበቡት ሰዎች ይመስላሉ፣ እንጂ ያነበበ ሰው እንደዛ ሊል አይችልም።

ስለዚህ ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ መሣሪያ መወሰዱ፣ አንደኛውነ ማጥቂና ለራስ ጥቅም ማግኛ መሆኑ ይመስለኛል።በአጠቃላይ ዋልታ ረገጥ የሆነው ፖለቲካም ነው።

የሪፖርቱ ስፋት አማራና ኦሮሚያ ላይ ብቻ ያጠነጠነ ነው። እናም ለምን በዛ መልክ ማጥበብ አስፈለገ?
አምነሲቲም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች ኹለት ዓይነት ጥናቶች አላቸው። አንደኛው የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ሌላው ደግሞ ጊዜን መሠረት አድርገው የሚወጡ ናቸው። ለምሳሌ ዓመታዊ ሪፖርት አለ። ባለፈው ሚያዝያ 23 ላይ አውጥተን ነበር። ይህም አጠቃላይ ባለፈው 2019 ኢትዮጵያ ላይ ምን ነበር የሚለውን የሚመለከት ነው። እዛ ላይ ብዙ ነገሮች ከእስር ጀምሮ እስከ እርስ በእርስ ግጭት፣ እስከ ጋዜጠኞች መታሰር፣ ስለኢንተርኔት መቋረጥ፣ በተለያዩ ክልሎች ስላሉ ነገሮች አውርቷል። በአንድ አገር በተወሰነ ጊዜ ምን ተፈጠረ የሚል የሪፖርት ዓይነት ነው።

ይህ ደግሞ በአንድ የተለየ ጉዳይ ላይ ጥልቀት ሰጥቶ የሚወጣ ሪፖርት ነው። እንዲህ ያለ ሪፖርት እንኳ ኢትዮጵያ ላይ በሌላም አገር ሙሉ አገር ወክሎ መሥራት አይቻልም። የተወሰነ አካባቢ መውሰድ ያስፈልጋል። ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት ለምን እነዚህ አካባቢዎች ብቻ ታይተው ሌላው ለምን ቀረ ሳይሆን፣ መስፈርታችሁ ምንድን ነው ነው።

መስፈርታችን ደግሞ እዚህ አካባቢ ያለው ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሪፖርት አልተደረገም። በሚዲያም፣ በሰብአዊ መብት ተቋማትም ሪፖርት ሲደረግ ስላላየንና፣ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ያለው ሁኔታ ብዙ አሳሳቢ የሰብአዊ መብ ሁኔታዎች ስላሉበት ነው። ለረጅም ጊዜም የቆዩ ናቸው። 2016 የጀመረ ነው፣ የጉጂም ከኹለት ዓመት በላይ አልፎታል።

ሪፖርቱን አስመልክቶ ኹለቱም ክልሎች ቅሬታ አቅርበዋል። ከኦሮሚያውን እንነሳና፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያካተተ እኛን ያልተመለከተ ነው ሲሉ እንዲከለስ ጠይቀዋል። መረጃ ከእነርሱ አልጠየቃችሁም ነበር? መረጃስ የተቀበላችሁት እንደተባለው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ነው?
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አይደለም። መረጃውን የሰጡን ጉዳት የደረሰባቸውና የዐይን ምስክሮች ናቸው። የሰብአዊ መብት ጥቃት ሰለባዎች፣ የታሰሩ፣ የተደበደቡ፣ የተንገላቱ ሰዎች እና እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ያዩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል ይሁኑም አይሁኑም ለውጥ አያመጣም። ማንም ሰው ቢሆን ሰብአዊ መብቱ መከበር አለበት። እነዚህ ሰዎች የገጠር ተማሪዎች፣ ከአርብቶ አደር አካባቢ የመጡ ሰዎች፣ በዛ አካባቢ የሚኖሩና በዛ የተሰማራ የመንግሥት ኃይል ይህ ደርሶብናል የሚሉ ናቸው። ከፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር ግንኙነትም የለንም። ከዚህ ጋር የሚገናኝ ሥራም አልሠራንም።

ምንአልባት ከመንግሥት ጋር የማይገናኝ፣ ሌላም ዓይነት አደጋ በዚህ ዓይነት ቢቀርብ፣ የምታረጋገጡበት መንገድ አላችሁ?
እሱን የምናረጋግጥበት መንገድ አለን። ለምሳሌ ብዙ ሰዎች አነጋግረናል፣ በብዙ ሰዎች ምስክርነት የተረጋገጠ ነው። ሰዎቹ የማይተዋወቁ ሊሆኑ ይችላሉ፣ አገላለጻቸው ሊለያይ ይችላል። አንዱ ከአንደኛው ጋር ደተጋግፏል ወይ ብለን የምናይበት መንገድ አለን። ውሸትን የምትይዝበት መንገድ አለ። አንዳንዴ የተሸመደደም አለ። ያንንም አረጋግጠን ነው። የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑም ያልሆኑም ይሆናሉ፣ ግን እንደዚህ ዓይነት የተቀመረ ታሪክ የሰጡን አይመስለኛል፣ አይደለምም። እንዳይሆን የምጠቀመውን መንገድ ተጠቅመናል።

ሌላው የኦሮሚያ መንግሥትን ደጋግመን ተመላልሰን ጠይቀናል። ጸጥታ ቢሮ ጠቃታ ማታ ብለን፣ ከዛ በኋላ ተወያተን መልስ እንሰጣለን ሲሉን አድራሻችንን ሰጥተን አስቀምጠን ሄደናል። ደብዳቤ ደርሷቸው፣ እሱን ተከትሎም በአካል ሄደናል፣ በስልክ አውርተናል። በተለያየ መልኩ ለመድረስ ሞክረናል። ያንን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም።

ያኔ ባገኘነው መረጃ ሪፖርት እንደምናዘጋጅ ነግረናቸዋል። ያውቁ ነበር። እናም በኋላ መጥቶ ሰንካላ ምክንያት ማቅረብ ትክክል አይሆንም። መጀመሪያውኑ ቢሳተፉ፣ የእነርሱንም ወገን ከማካተት ባይከለክሉ ኖሮ ይህ ሁሉ አይሆንም ነበር። በተደጋጋሚ እድል ተሰጥቷቸዋል፣ ግል ሊጠቀሙበት ፈቃደኛ አልነበሩም።

ክልሉ አሁን ላይ መረጃ እንሰጣለን ብሏል። የምንሰጠው መረጃ ተካትቶ ይከለስ የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡት። ያንን ለማድረግ አሠራራችሁ ይፈቅዳል?
አሁን ባለን መረጃ ክለሳ የምናደርግበት ምክንያት አይታየኝም። ተጨማሪ መረጃ ከሰጡን ሌላ ጥናት ነው የሚሆነው። እነዚህ የተረጋገጡ እውነቶች ናቸው። ይህን ከነገሩን ሰዎች ጋር በተለያዩ መልኩ እንከታተላለን። እና አሁን ስላሉበት ሁኔታም እናውቃለን። ታስረው የነበሩ፣ በቅርብ የተፈቱም አሉ። እናም በዛ ባለው ሪፖርት ላይ ምንም የሚቀየር ነገር የለም።

- ይከተሉን -Social Media

ተጨማሪ አለ የሚሉት ካለ፣ በጣም አሪፍ ነገር ነው። እሱ ለተጨማሪ ጥናት ይረዳናል። ግን ይህን ሪፖርት የሚያስከልስ ነገር ከመንግሥት ይመጣል ብዬ አላስብም። የጥቅምት ግርግርና በዛ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ለምን አልተካተተም ከተባለ፣ እሱም ቢሆን በዚህ ጥናት ትኩረት ውስጥ አልወደቀም።

ግን ለምንድን ነው አንድ ነገር ለማድረግ አምነስቲን የሚጠብቁት። ሰብአዊ መብትኮ ስለ ሪፖርት አይደለም፣ እርምጃ የመውሰድ ጉዳይ ነው። እርምጃ የሚወስደው መንግሥት ነው። እስከ አሁን ድረስ ይህ ሁሉ መረጃ ካላቸው፣ ወንጀል እንደተፈጸመ የሚያውቁ ከሆነ ለምን አምነስቲን መጠበቅ አስፈለጋቸው። በዛ ላይ ሒውማን ራይት ወች መረጃ አውጥቷል። እና አምነስቲም መድገም አለበት፣ ሀብት ማባከን አለብን?
መደጋገም አያስፈልግም። ዓመታዊ ሪፖርታችን ላይ አካተነዋል፣ መድሎ እንኳ እንዳይመስል ማለቴ ነው። ግን መንግሥት ለምንድነው አገር ውስጥ ላለ ጉዳይ የውጪ ሪፖርት የሚጠብቀው። ዋናውም ሪፖርት ሳይሆን እርምጃ ነው።

ቅሬታው አንድም ሆነ ተብሎ የመንግሥትን መልክ ለማጠልሸት ነው የተወሰኑት ያልተካተቱት የሚልም ነው፣ በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
ይህ የሰብአዊ መብትን ሕግ ጽንሰ ሐሳብ አለመረዳት ይመስለኛል። የሰብአዊ መብት ሕግ ግዴታን የሚጥለው መንግሥት ላይ ነው። ለምሳሌ እኔ እና አንተ ተጣልተን አንዳችን ሌላችን ላይ ጉዳት ብናደርስ፣ መንግሥት በኹለታችን መካከል ገብቶ ለጉዳቱ አንዳችን በወንጀል የምንጠየቅ ከሆነ፣ መጠየቅ አለብን። ካሳ የሚከፈል ከሆነ ካሳ እንዲከፈል ማድረግ አለበት። ይህ እንግዲህ ኹለት ግለሰቦች የሚያደርጉት የወንጀል ግንኙነት ነው እንጂ፣ የሰብአዊ መብት ጉዳይ አይሆንም። መንግሥት ሲገባ ግን የሰብአዊ መብት ጉዳይ ይሆናል።

ስለዚህ ሰብአዊ መብት ኃላፊነቱ የሚጣለው በግለሰብ ደረጃ ወይም መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ሳይሆን፣ ለመንግሥት ነው። ዓለማቀፍ ግዴታን የሚወስዱት የመንግሥት አካላት ናቸው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ እርስ በእርሳችን እንዳንጎዳዳ የመከላከል ኃላፊነት የወሰደው መንግሥት ነው።

ስለዚህ ማንም አደረገው ማን፣ መጨረሻ ላይ ሰብአዊ መብት ጉዳይ ተጠያቂ የሚያደርገው መንግሥት ነው። እናም እገሌ እገሌ ብሎ ወደዛ መግፋት አይቻልም። የሰብአዊ መብት ጉዳይ መንግሥት ጋር ነው የሚመጣው። መንግሥት አልቻልኩም ካለም ወደሌላ ጉዳይ እንሄዳለን። ግን የሚሠራ መንግሥት እስካለ ድረስ፣ ኃላፊነቱ ወደ መንግሥት ነው።

ኦሮሚያን በሚመለከት፣ በኦሮሚያ ያሉ የአስተዳዳሪዎች ግድያ ሲሆን፣ በዛም የታገቱ ሴቶች ጉዳይም አለ። እነዚህ ነገሮች ይካተታሉ የሚል ግምት ነበር። እነዚህ እንዴት አልተካተቱም?
አንደኛ ዓመታዊ ሪፖርት አይደል። ዓመታዊ ሪፖርታችን ላይ እነዚህ ነገሮች ተካተዋል። ለምሳሌ ስለታገቱ ሴቶች፣ ስለእነርሱ ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለነበሩና ስለሞቱ፣ ስለተገደሉና ስለግጭቱ ሁሉ አካተናል። እሱ ዓመታዊ ሪፖርት ነው። ይህ ግን የጥናት ትኩረቱ በዛ ላይ ስላልሆነ ነው።

ሌላው የአባ ቶርቤ ግድያን በተመለከተ፣ የተሟላ መረጃ ያለውኮ መንግሥት ነው። እድሉንም ሰጥተነዋል። በዚህ ላይ ሪፖርት ልናደርግ ነውና ምን አለ ብለን ጠይቀናል። ያንን እድል ቢጠቀም ኖሮ መረጃ ሊሰጠን ይችል ነበር። ምክንያቱም በሰብአዊ መብት ሦስት ዓይነት ግዴታዎች አሉ። የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት።
የእኛ ሪፖርት የማክበር ግዴታ ላይ ነው ያተኮረው። ሌሎች አካላት የሚፈጽሟቸውን የመከላከል ደግሞ የማስከበር ግዴታ ውስጥ ይመጣል። ያ ደግሞ ትልቅና ሌላ ጥናት ነው። የሚጠይቀው ሀብትና ጊዜም ይለያል። ግን ያለመካተቱ መንግሥትን ነጻ ያወጣኛል የሚለው አይደለም። እንደ መከላከያ ሊጠቀሙትም አይገባም።
አሁን ሌላውንም የሰብአዊ መብት ጥሰት አላካተቱም፣ እባካችሁ ጨምሩ እያሉን ነው የሚመስለው። እና እንዲሁ በሐሳብና ከሰብአዊ መብት ጽንሰ ሐሳብ አንጻር ስታየው፣ መልሱ ራሱ የሚያስኬድ አይደለም።

አማራ ክልልም በተመሳሳይ እንደ ኦሮሚያ ቅሬታ አሰምተዋል። በተለይም ሪፖርቱ በአማራና በቅማንት መካከል ግጭት ይቀሰቅሳል የሚል ነው የእነርሱ ቅሬታ። ይህስ እንዴት ታይቷል?
ሪፖርቱ እንዴት ግጭት እንደሚቀሰቅስ አይገባኝም። እዛ ያሉ ሰዎች ያለውን ነገር ያውቁታል። በዛ ላይ ከኹለቱም ወገን አናግረናል። በተለይ በጎንደር የተወሰኑ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የአማራ ሰዎችን አናግረናል። ሌላው ደግሞ በጎንደር አካባቢ የተፈናቀሉ የቅማንት ሰዎችን አናግረናል። ሪፖርቱም ላይ ይገኛል።
ሪፖርቱ ላይ የቅማንቱ ወገን የበዛበት አንድ ምክንያት አለ። ቅድም አንዳልኩት ይህ ሪፖርት መንግሥት የማክበር ኃላፊነቱን ያልተወጣበት ቦታ ላይ ነው ያተኮረው።
በዚህ ግጭት ውስጥ ደግሞ የመንግሥት አካላት የጥቃቱ አካል ሆነው፣ ለአንድ ወገን ወግነው ጉዳት ያደረሱበትን ወይም ሆነ ብለው ከመግባትና ነገሩን ከማብረድ ወደኋላ ያሉበትን ጊዜ ነው። እንጂ በኹለቱም ወገን አናግረናል። ያሉትን መረጃዎችም በሙሉ አካተናል።
እውነት መውጣቱም ወደግጭት አያመራም። የተፈጠረውን ነገር ነው የተናገርነው፣ ስለዚህ ወደ ግጭት ያመራል ብዬ አላስብም።

- ይከተሉን -Social Media

ግን በአማራ ክልል መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ነበሩ?
አዎን! በተለይ ከማእከላዊ ጎንደር ጸጥታ መምሪያ ጋር ተነጋግረናል። የተወሰኑ መረጃዎችን ከእነርሱ አግኝተናል። እንዲሁም በኋላ ላይ ደግሞ የክልሉን ጸጥታ እና ደኅንነት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አግኝተን፣ ስለተወሰዱ እርምጃዎች፣ ስለታሰሩ ሰዎች ብዛት እና ሌሎችም ነገሮችን፣ ጥናት ውስጥ መግባት የማይችሉ ጉዳዮችንም ነግረውናል።

ምዕራብ ጎንደር ላይ ስላለው ነገር ግን ማንም መረጃ ሊሰጠን አልቻለም። የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በጉዳዩ ላይ መረጃ የለኝም፣ ቆይቷል፣ አላስታውስም እያሉ መረጃ ሊነግሩን አልቻሉም።

ታድያ መረጃ በሚሰጡ ጊዜ የተፈናቀሉ ሰዎችን እንድታናግሩ አልጠቆሙም?
መጠቆም ብቻ ሳይሆን፣ እነርሱ ሳይጠቁሙንም እኛም ሄደን አናግረናቸዋል። ለምሳሌ ቅማንት ከሚበዙባቸው የጎንደር ዙሪያ ቀበሌዎች ሄደን አናግረናል። እርሻ ሰብል የሚባል ቦታ ላይ ነው ተጠልለው የነበሩት። ብዙ ሰዎች አናግረናል። ጥናቱም ላይ ተካቷል።

በሪፖርቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ምክረ ሐሳብ አለ፣ በዛም ላይ ከተባበሩት መንግሥታት ራፖርተር መጥቶ እንዲጎበኝ የሚል ጥያቄ አቅርባችኋል። ፋይዳው ምን ይሆናል በሚል ግምት ነው?
እነዚህ የሰብአዊ መብት የተለዩ ‹‹ሜካኒዝሞች›› ናቸው። በይበልጥ ነጻና ከትምህርት ጋር የተገናኙ ሰዎች ናቸው የሚመደቡት። እነዚህ ሰዎች ካላቸው ልምድና እውቀት አንጻር፣ በጉዳዩች በጥልቀት የሚሠሩና ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ የሚሰጡ ናቸው። ይህ ከሆነ አንደኛ የመንግሥትን መሰጠት ያሳያል። በአንድ ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሠሩ ሰዎች እንዲህ ላለ ሥራ ቢጋበዙ ጥሩ ነው።

ያ ካልሆነ ደግሞ እነሱም ጠይቀው፣ ያለውን ሁኔታውን እንይ ብለው ይጠይቃሉ። ከዛ ለመማር ነው። ምርመራው ተደርጎ ምክረ ሐሳብ ይኖራል። ያንን ለመተግበር ይረዳል። ከአምነስቲ የተሻለ ተቀባይነትና ልምድ ያለው ተቋም ስለሆነ፣ ይረዳል። ብዙ ጊዜ ምክረ ሐሳባችን ላይ እንደየጉዳዩ ዓይነት እነዚህን ነገሮች እናስገባለን። ስለዚህ የተለየ አካሄድ አይደለም።

ባለፈው ዴቪድ ካይ መጥቶ ነበር። እርሱም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽና የሚድያ መብቶች ስፔሻል ራፖርተር ነው። እናም እነዚህ ራፖርተሮች ቢመጡ ችግር ያለ አይመስለኝም። በጣም ጠቃሚ ናቸው። ከመንግሥትም ጋር ይወያያሉ፤ ከምክራቸውም የሰብዓዊ መብት አያያዝን ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዱ ግብዓቶች ሊገኙ ይችላሉ፡፡
ከሪፖርቱ ስንወጣ፣ በትግራይ እየታየ ያለ አለመረጋጋት አለ። የአስተዳደር ጥያቄና ሎሎች ጉዳዮች ይነሳሉ። ያንን ተከትሎ እስር እንዲሁም ግድያ እንዳለ ይሰማል።

በዚህ ላይ የእናንተ ዕይታ ምንድን ነው? ጉዳዩንስ ተከታትላችኋል ወይ?
የተወሰነ ያየናቸው ነበሩ። ለምሳሌ አዲስ አበባ የነበረው፣ ባለፈው ዓመት ሰልፍ ላይ የተገደሉ ሰዎች ነበሩ፣ መከላከያ ሚኒስቴር ፊት ለፊት። በዛ ወቅት ሐሳባችንን ገልጸናል። መገደላቸው ልክ አይደለም፣ ይህን የፈጸሙ የጸጥታ አካል አባላት ምርመራ ተደርጎ ለፍርድ ይቅረቡ ብለን ጠይቀን ነበር። ከዛ ውጪ የሚድያ ሰዎች መታሰርም አለ። ክልሎች ላይ የተወሰኑ ስብሰባ ሲካሄድ መበጥበጥ አለ።

የመንግሥት አካላትም ይሁኑ ሌሎች የሚያደርጓቸው፣ ሰላማዊ የሆኑ፣ መስመራቸውን ጠብቀው የሚደረጉ የመብት ጥያቄዎችን መበተን፣ ማሰር በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም።

- ይከተሉን -Social Media

በቅርቡ ለምሳሌ ቡራዩ ላይ ስብሰባ ሲያደርጉ ተረብሸዋል። የአብን ሰዎች ከሰኔ 15 ጋር በተያያዘ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ታስረው ነበር፣ ተገቢ አይደለም። ባልደራስ የሚባለው የእስክንድር ነጋ ስብሰባ የተለያየ ወከባ ይደረግበታል፣ ልክ አይደለም። ሰሞኑን በትግራይ የምንሰማው ነገር አለ፣ እስከ አሁን አላረጋገጥንም። ከመንግሥት በኩል እርምጃ መወሰዱን አላውቅም። እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎችን እንደውም መንግሥት ማበረታታትና መጠበቅ ነው እንጂ ያለበት፣ ለማስቆም ወይም ለመበተን የሚደረጉ ነገሮች መኖር እንደሌለባው ነው የማስበው። ሐሳብን መግለጽ የሰብአዊ መብት አካል ነው።

የሚመጣውን ምርጫ አስመልክቶ እስከዛ ባለው ጊዜ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚንር ስጋታችሁን ገልጻችኋል። ይህን እንድትሉ ያደረጋችሁ ምንድን ነው?
አንደኛ ከመስከረም ጀምሮ የጨመሩ ነገሮች አሉ። የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ያለው መዋከብ ጨምሯል። ሰልፎች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ይካሄዳሉ። ኹለተኛ የፖለቲካችን ባህሪ ወደ ምርጫ አካባቢ የመጋጋል ነገር አለ። ፖለቲካ ግለት ይጨምራል፣ ሰልፍ ይወጣል። የመንግሥት አካልም አይቀበለውም። ወይም ሰልፍ የሚወጣው ወገን ስሜታዊ ሆኖ ድንጋይ ውርወራ ይጀምራል። እነርሱም ከመጠን በላይ የሆነ ምላሽ መስጠት አለ።

እናም ፖለቲካው የተወጠረ፣ በሐሳብ ለመፋጨት ሳይሆን እርስ በእርስ ለመፋጨት የተዘጋጀ ነው። ጥላቻን መሠረት ያደረጉ ብዙ ነገሮች ይነገራሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ ምርጫ ሲጨመርበት ነገሮች ወደሌላ ነገር ይቀየራሉ።

ይህን የሚቆጣጠረው የጸጥታ ኃይሉ ነው። እንዳየነው ደግሞ የጸጥታ ኃይሉ ሕግ ለማስከበር በሕግ መሠረት ሳይሆን ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ ነው። ያ መቀጠል የለበትም።

ስለዚህ ከምርጫ በፊትና በኋላ የሚኖሩ ግጭቶች ይኖራሉ ብላችሁ እየጠበቃችሁ ነው?
እድሉ አለ ነው፣ የወደፊቱን አናውቅም። በሰላምም ሊያልፍ ይችላል። ግን የመሆን እድል ስላለው፣ እንደዛ የሚሆንና ግጭት የሚኖር ከሆነ፣ የጸጥታ ኃይሉ ገለልተኛ ሆኖ፣ ሕግ ለማስከበር የሚሆኑ በሕጉ ውስጥ የሚወድቁ እርምጃዎችን ብቻ እየወሰደ መቀጠል አለበት።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች