መች…መች…መች?

0
704

ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች፣ በዜግነት አሜሪካዊ ሆነውም በአሜሪካ በሚደርስባቸው መከራ የተሰማቸውን ምሬት ለመረዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። ሰልችተዋል፣ ተማርረዋል። ነጻነት ማጣት፣ ተወልደው ባደጉበት አገር ላይ በፍርሃት መንቀሳቀስ፣ ከነጭ አሜሪካውያን በተለየ በየድርጊታቸው ተጨማሪ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መገደድ…ብዙ ብዙ ነገር አሰልችቷቸዋል።

የእነዚህ ሰዎች መሰልቸት፣ መማረር፣ በሰዎች ዘረኝነት መዛል፣ ነጻነት መነፈግ፣ መገፋት፣ መረሳት፣ ከሰው አለመቆጠር፣ ፍትህ መነፈግ እንዴትስ አይሰማን? ይልቁንም ሴቶች ሕመሙ እንዴት ከልብ አይደርሰን? ምነው ለሴቶች ጥቃትም እንዲህ ሰልፍ ብንወጣ? እንዲህ ፍርድ ብናስቀይር? እንዲህ ባለግብረገብ ነኝ የሚልን ማኅበረሰብ ገበና ብልገልጥ?

በገዛ አገሯ ላይ አይደለም፣ አንዲት ሴት በገዛ ቤቷስ መች ሰላሟን አገኘች? በገዛ አባቷ ስትደፈር፣ ይጠብቀኛል በምትለው ቤተሰቤ ባለችው በገዛ ወንድምና አጎቷ ጥቃት ሲደርስባት፣ በባሏ ሕይወቷን ስትቀማ፣ በ‹ወታደር› ስትደበደብ አላየንም? የእኔ ባለችው መች አረፈች? የእኔ ያለችው ማን አስጠጋት? ማን ከለላት? ማን ጠበቃት?
ብዙዎች ይጠይቃሉ፣ ‹‹የጥቁር አሜሪካዊው ሞት እንዲህ ነውጥ የፈጠረው ሞቱ በአሰቃቂ ሁኔታና እየታየ ስለሆነ ነው? ብዙ ጥቁሮች ከዚህ ቀደም በአስከፊ ሁኔታ የዘረኝነት ሲሳይ አልሆኑም ወይ?›› ይላሉ። አዎን! የዚህ ሰው አሰቃቂ ሞት በፊታችን መገለጡ፣ ‹ዘረኝነት በቃ!› የሚል ድምጽ በዓለም ሁሉ እንዲያስተጋባ ትልቅ ድርሻ አለው።

እንግዲያው አንዲት ታግላ የማትጥል፣ ተቆጥታ የማታስደነግጥ፣ ጮኻ ድምጿ የማይሰማ ትንሽ ልጅ፣ ከደፋሪዋ ለማምለጥ ስትፍጨረጨር፣ ስትዝል፣ ስትደክም፣ በሚንቀሳቀስ ስጋ ውስጥ መንፈሷ ሲሰበር ቀርጸን እናሳይ? መደፈሯ፣ መደብደቧ፣ ሞቷ ምስክር ፊት ይሁን? በምስል ተቀርጾ በማኅበራዊ ሚድያ ይለቀቅ? በዛ ነው ለውጥ የሚመጣው?

መች ነው የሚበቃው? አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ሰዉን በየቤቱ ማስቀመጡ በቫይረሱ ሊያዝ የሚችለውን ሰው ይቀንስ እንጂ፣ የሴቷን መከራ ምንኛ እንዳበዛው ተመልከቱ? እውነት ለመናገር ይደክማል። እንዴት ልንሆን ነው? አባት ልጁን ከደፈረ፣ እንግዲህ ምን መሆን ነው የቀረን? ፖለቲካ ፓርቲ የሌላቸው፣ መንግሥትን ተቃውመው ቀልብ የማይገዙ፣ አክቲቪስት ያልወከላቸው፣ በክርክር የማይረቱ ጨቅላ ሕጻናት፣ ወንድና ሴት ልጆች ሲደፈሩ እየሰማን፣ እንግዲህ ምን ሊተርፈን ነው?
ሰው ከእንስሳ ማነስ ላይ ከደረሰ ከዛ በኋላ ወዴት ዝቅ ሊል ይችላል? ምነው ጉዳዩ የአንድ ቢሮ፣ የአንድ ማኅበር፣ የአንድ ተቋም፣ የአንድ ሰሞን ብቻ መሰለ? መች ነው መርሮን ገፍተን የምንወጣው? መች ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመረጡ ቃሎቻቸው ለውጥን የሚያስጠሩት? መች ነው ጉዳዬ እንዳሉት የሚነግሩን? ነው በፊት የአገር ሰላም ነበር፣ አሁንስ ኮሮና ይቅደም?

ጥቁር አሜሪካውያን ቢቸግራቸው ነጮቹን ‹ትግላችንን ተቀላቀሉ› ብለው እንደጠሩ፣ ወንዶችን እንጠራለን። በሰውነት የሚያምኑ፣ ከሴት በእናትነቷ፣ በእህትነቷ፣ በሚስትነቷ ስለሚያገኙት ጥቅም ሳይሆን እንደሰው የሚያከብሩ፣ ሰው የሆኑ ወንዶችን እንጠራለን። በሴቶች እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዲቆም፣ ሕግ ኮስተር እንዲል፣ ያጠፉ ቅጣታቸው በአደባባይ እንዲታይ፣ እነርሱ እንዲያፍሩ እንጂ መከራ ያደረሱባት ሴት አንገቷን ቀና እንድታደርግ፣ አቤት እንበል!
ይብቃ! ኢትዮጵያ ሴት ወልዶ ማሳደግ፣ ሴትም መሆን፣ ከአባትና ከወንድም ጋር መሆን፣ ከትዳር አጋር ጋር መሆን የሚያስፈራበት አገር አትሁን!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here