የማስታወቂያ ገቢ ዕጦትና የመገናኛ ብዙኀኑ ሕልውና

0
1024

ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይስ ወረርሽኝ መከሰት አስቀድሞ የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ በመከልከሉ ጥቂት የማይባሉ የመገናኛ ብዙኀን በማስታወቂያ የሚያገኙት ገቢ ቀንሶባቸዋል። ይህም አንዳንዶች መርሃ ግብሮቻቸውን እንዲያጥፉ፣ አንዳንዶችም የመዘጋት ስጋት እንዲደቀንባቸው አድርጓል። ይህን የሚያወሱት አብርሐም ፀሐዬ፣ መገናኛ ብዙኀን አማራጭ የስርጭት መንገዶችን መጠቀምና አካሄዳቸውን ማጠናከር አለባቸው ሲሉ ያለውን አማራጭና በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ልምዶችን ጠቃቅሰዋል።

ማስታወቂያ ከማግባቢያ መንገዶች አንዱ ሲሆን ለመገናኛ ብዙኀኑ ክፍያ በመፈጸም ሐሳቦችን፣ ቁሶችንና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ በሰፊው ተደራሽ አድርጎ ለማስተዋወቅ የሚጠቅም መሣሪያ ነው። እንደሚታወቀውም ጋዜጣ፣ ሬድዮ፣ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት ዋና ዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኀን መሣሪያዎች ናቸው።

በዚህ በዘመናዊው ዓለም ሕዝቡ ከሚገኝባቸውና ከሚጠቀማቸው ዋነኛ ስፍራዎች መካከል እነዚህ መገናኛ ብዙኀን ቀዳሚ ሆነዋል። አስተዋዋቂ ድርጅቶች እንደምርቶቻቸው ባህሪ የሚፈልጉትን ሚዲያ ወይም መገናኛ ብዙኀን በመምረጥ ወደ ተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆንላቸው በክፍያ ያስተዋውቁባቸዋል። በመሆኑም በተከታታዮች ዘንድ በይበልጥ ትኩረት ሳቢ የሆኑ ሚዲያዎችና በሚዲያው ውስጥ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን መምረጥ የአስተዋዋቂ ድርጅቶች ድርሻ ይሆናል። ብዙኀን መገናኛዎቹም ተከታዮቻቸውን ለማብዛት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ በመገኘት አስተዋዋቂ ድርጅቶችን መሳብ ይጠበቅባቸዋል።

የማስታወቂያ ዘርፍ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት በመሆኑ፣ በርካታና የተለያዩ አካላትን ያስተሳስራል። በማስታወቂያ የሚገኘው ገቢ ለሚዲያዎቹ የጀርባ አጥንት ከመሆኑም ባሻገር ሕዝቡም በተዘዋዋሪ መረጃዎችን በማግኘት ተጠቃሚ ይሆናል። ራሳቸው አስተዋዋቂ ድርጅቶችም አዳዲስ ተጠቃሚዎችን በማፍራትና የነበሩትንም በማቆየት በኩል በገበያው ላይ አሸናፊ ሆኖ ለመቆየትና ሕልውናቸውን ለማስቀጠል ይጠቀሙበታል።

የአዲስ ሚዲያ መፈጠር በነባሮቹ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ
የኢንተርኔት አብዮት የዓለምን አካሄድ በእጅጉ ያፈጠነና የቀየረ የአዲሱ ዘመን አዲስ የመገናኛ አውታር ሆኗል። ለምሳሌ ብንመለከት ከኹለት ቢሊዮን በላይ የዓለማችን ሕዝብ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሆኗል። በመሆኑም ኢንተርኔት የወረቀት ህትመቶችንና እንደ ሬድዮና ቴሌቪዥን ያሉት ነባሮቹ የኤሌክትሮኒክስ ብዙኀን መገናኛዎች ላይ ተገዳዳሪ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ብዙኀኑ የማኅበረሰብ ክፍል በዚህ ለአጠቃቀም ምቹ በሆነው የኢንተርኔት የመገናኛ አውታር ላይ መገኘቱ ወይም ዘርፉን መምረጡ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ጭምር ሥራዎቻቸውን ከኢንተርኔት ጋር በማቆራኘት አብረው ለመሥራት ተገደዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢንተርኔቱ ራሱ የሕትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የሚሠሩትን ሥራ ተክቶ መሥራት የሚችል በመሆኑ የእርስ በእርስ ውድድሩ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመሣሪያና የባለሙያ አቅም ይጠይቁ የነበሩት ሚዲያዎች ኢንተርኔቱ በአንድ የቴክኖሎጂ ቁስና ሰው ብቻ መሥራት እንዲቻል በማድረግ ዘርፉን አቅልሎታል። ኢንተርኔት ከኤሌክትሮኒክስና ሕትመት መገናኛ ብዙኀን ጋር ተሳስሮ መሠራጨቱ ለተደራሽነት ያለው ፋይዳ ጥሩ ቢሆንም፣ ኢንተርኔቱ ግን እምብዛም የሙያን ከፍታ የማይፈልግ፣ ፈጣንና በቀላሉ የሚከወን ሆኖ መገኘቱ ለነባሮቹ ሚዲያዎች ራሱን የቻለ ፈተና ሆኗል።

አስተዋዋቂ ድርጅቶችም በተለይ ወጣቶችን ለማግኘት የሚፈልጉ ኩባንያዎች ኢንተርኔትን ተመራጭ ወደማድረግ እየመጡ ነው። የማስታወቂያ ሥራ የሚዲያዎች ዋና መተዳደርያ ገቢ እስከሆነ ድረስ ነባሮቹ ሚዲያዎች ጥራት ባላቸው ፕሮግራሞች የተለየ፣ ሳቢና ተመራጭ ሆኖ በመገኘት ሕዝቡንና አስተዋዋቂ ድርጅቶችን ሊይዙ ግድ እያላቸው መጥቷል። በተለይ ትኩስ መረጃ አሰጣጥ ላይ አቀራረቡን ወይም በዝርዝር ጉዳይ አሻሽሎና በማኅበራዊ ትስስሩ ያልተነገሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ካልሠሩ በቀር፣ የ”ሰበር ዜና” አጓጊ መረጃ በኢንተርኔት አማካይነት እየከሸፈባቸው ነው።

የግል ሚዲያዎችና የማስታወቂያ ግኝት ፈተናቸው
በቅርቡ እየሆነ ያለውን ብንመለከት እንኳን ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በርካታ ጋዜጠኞች ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። በጠቅላላው 127 የሚሆኑ ጋዜጠኞች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳጡ ተዘግቧል። ጄኔቫ ያለው የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ቡድን ከሠላሳ አንድ አገራት እነዚህ ጋዜጠኞች ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሕይወታቸው ማለፉን አሳውቋል። ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ በቂ የመከላከያ መሣሪያዎችን ባለማግኘታቸው የተነሳ ሕይወታቸውን ለማጣት እንዳጡ ነው የተጠቀሰው።

የዚህ ዓይነት መስዋዕትነት የሚከፈልበት ሙያ ለማኅበረሰብ ተደራሽ የሚሆኑ አስፈላጊ መረጃዎችን እንዲያቀርብ ሲባል በቂ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገዋል። የጋዜጠኝነት ጥቅም በተለይ ለሕዝብ ነው። የተሸፋፈኑ መረጃዎችን ይፋ በማድረግ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ የምዝበራ፣ የግድያ እና በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ በኩልም ትልቅ አስተዋጽኦ አድራጊ ነው።

በተለይ በአፍሪካና በአገራችን ያለው የፕሬስ ነጻነት ደካማ በመሆኑ የማስታወቂያ ገቢ ዕጦት ከተጨመረበት ሚዲያውን በገንዘባቸው መቆጣጠር በሚችሉ ቡድኖች ቁጥጥር ስር መዋሉ አይቀርም። ይህ ደግሞ እጅግ አደገኛና የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ጽንፈኝነት እንዲስፋፋ የተመቻቸ ዕድል ይፈጠራል። የጥቂት ቡድኖች ንግሥና ይፈጠራል። በሥልጣን መባለግና አምባገነንነት እንዲሁም ጭቆና መታየት ይጀምራል።

ከኮሮና ወረረሽኝ ጋር ተያይዞ የንግድ እንቅስቃሴው መቀዛቀዙ ለማስታወቂያ ገቢ መጥፋት ሌላው ፈተና ሆኗል። በዚህ የተነሳም ጋዜጠኝነቱ ፈተና ላይ ወድቆ በስተመጨረሻም ከመርሁ ውጪ እንዲሄድ ያደርገዋል። የሚዲያ ሥራው የገንዘብ ጉልበት ባላቸው ጽንፈኛ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ከመዋሉም ባሻገር፣ ገንዘብ እንደፈለጉ መመደብ በሚችሉ መንግሥታት የሚደገፉ ሚዲያዎች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ የመንግሥትና የተለየ ጥቅም ፈላጊ ለሆኑ ኃይሎች ቃል አቀባይ የሆነ ጋዜጠኝነት መፈጠሩ አይቀሬ ነው።

በሚዲያው ዘርፍ የተደቀነው ስጋትና ውጤቱ
እንደሚታወቀው በአገራችን የሚዲያው ዋነኛ ምንጭ የሆኑት የአልኮል አምራች ድርጅቶች ከማስታወቂያ መታገዳቸው የመገናኛ ብዙኀኑን ዘርፍ ከገበያ እያስወጣው ጋዜጠኝነቱም እየቀጨጨ ይገኛል። ከዚህ የኮሮና ስርጭት ጋር ተያይዞም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ተጨማሪ ችግር በመሆኑ፣ የመገናኛ ብዙኀኑ ህልውና እና የፕሬስ ነጻነቱን ጉዳይ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጎታል።

ከአቅም ማጣት አንጻር የተዘጉ ሚዲያዎችን አስመልክቶ ለጊዜው በሥራ ላይ ያሉት ሚዲያዎች ነገም በእነርሱ ላይ ሊመጣ እንደሚችል አስልተው የሰጡት ትኩረት እዚህ ግባ አይባልም። ከገቢ ዕጦት አንጻር የተሰላ ጥያቄ ለመንግሥት አቤት ቢባልም፣ ችግሩ ግን ከዚህ የላቀ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
ትክክለኛ መረጃ ያጣ ሕዝብ ወደተሳሳተ አቅጣጫ ወይም የጥቂት ቡድኖች ሰለባ መሆኑ አይቀሬ ነው። ኃላፊነትን በማይጠይቀው በኢንተርኔት ለሚሰራጩ አደገኛ ዜናዎች መጋለጥ ይኖራል። ይህ ለአገርም ይሁን ለመንግሥት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሕዝብ መፍጠሩ አይቀርም። ስለሆነም ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለባቸውን የመገናኛ አውታሮች በሥራ ላይ እንዲቆዩ ማድረግ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

የአስተዋዋቂ ድርጅቶች አዲስ መንገድ መልመድ
የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝ ድርጅቶችን ለተወሰነ ጊዜ ከማስታወቂያ እንዲርቁ ያደረገ ክስተት ነው። በአገራት ውስጥ የሚፈጠሩ አዳዲስ የስርዓት ለውጦች የሚወልዷቸው አዳዲስ መንገዶች ይኖራሉ። ከዚህ ቀደም እንደሚታየው ዓለም እንደዚህ ዓይነት ትላልቅ አደጋዎችን ስታስተናግድ እግረ መንገዷን የምትለምዳቸው ለየት ያሉ ለውጦች ይኖራሉ።

ለምሳሌ በአገራችን የአልኮል ድርጅቶች ከማስታወቂያ መታገድ ያመጣው ለውጥ ምርታቸው ተደራሽ እንዲሆን የራሳቸውን አዲስ መንገድ መከተላቸው እንደማይቀር ነው። ምናልባትም የሚጀምሩትን አዲስ ስልት እንዲያስተዋውቁ ቢፈቀድ እንኳን ተመልሰው ላይመጡ የሚችሉበት መላ ሊያገኙበት ይችላሉ።
ይህ ደግሞ ለሚዲያዎች ምን ማለት እንደሆነ መገመት አያዳግትም። በነገራችን ላይ ምንም ዓይነት ማስታወቂያን የማይጠቀሙ የዓለማችን ግዙፍ የንግድ ተቋማት አሉ። ባለማስተዋወቃቸው ከሚቆጥቡት የገንዘብ መጠን አንጻር ሲያስተያዩ ሌሎች አስተዋዋቂ ድርጅቶች የእነዚህን መንገድ ስለመከተል ሊያስቡ ይችላል። የቴስላ ኩባንያን ብንመለከት ዘንድሮም ባለማስተዋወቅ እንደቀጠለ ቢዝነስ ኢንሳይደር የዘገበውን እንመልከት።

ቴስላ ያለማስታወቂያ የቆመ የባለቢሊዮን ዶላር ኩባንያ
ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው በአመዛኙ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖችን በማምረት የሚታወቀው የቴስላ ኩባንያ ያለማስታወቂያ መጓዙን ዘንድሮም ቀጥሎበታል ተብሏል። የኦቶሞቲቭ አምራቾች ከፍተኛ ቢሊዮን ዶላር መድበው በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች እንደሚያስተዋውቁ ይታወቃል። የቴስላ ኩባንያ ግን አሁንም ባለማስተዋወቅ አቋሙ እንደጸና መቆየቱ አስገራሚ አድርጎታል ሲል አክሏል።

የቴስላ ኩባንያ መሥራች የሆነውና ከፍተኛ ባለድርሻ እንዲሁም ተቋሙን በኃላፊነት እየመሩ ካሉት መካከል ግንባር ቀደም የሆነው ኤሎን ማስክ ማስታወቂያ ለሚዲያ ዘርፉ ጥቅም የቆመ እንጂ በማስታወቂያ አማካይነት ወደ ድርጅት ገበያ ይመጣል ለሚለው አስተሳሰብ አይጨነቅም። ማስታወቂያ ለትርፍ ለተቋቋሙ ድርጅቶች እንደመስጠት የሚቆጠር ነው የሚል ዕምነት አለው።

ኤሎን ማስክ የምጠቀምበት የራሴ የማስታወቂያ ስልት አለኝ ባይ ባለሀብት ነው። ይኸውም ‹‹በምርቱ ዙሪያ ጥሩ ሥም እንዲፈጠር በማድረግ ደንበኞችን እጅግ በተሻለ እንክብካቤ በማገልገል እንዲሁም ሰዎች የቴስላን ምርት በራሳቸው ፈቅደው በየኢንስታግራማቸው የሚለጥፉት ተወዳጅና ተፈላጊ ምርት በማድረግ ገበያው ላይ ትርፋማ ሆኖ መቆየት ይቻላል።›› ይላል። የሆነለትም ይመስላል።

በእርግጥ ከቴስላ ኩባንያ ባለድርሻዎች መካከል አንዱ የሆነው ጀምስ ዳንፎርዝ ወደ ማስታወቂያ መግባት እንደሚያስፈልግ ሐሳብ አቅርቧል። የተቋሙ ቦርድም ሐምሌ ላይ እንደሚወያይበት ቢገለጽም፣ ከወዲሁ እንደተገመተው ግን ድርጅቱ ምርቱን ወደ ማስተዋወቅ ይገባል ተብሎ አይጠበቅም።

እንደቴስላ ዓይነት ከፍሎ ከማስተዋወቅ የራቁ በርካታ ድርጅቶች በዓለም ላይ ያሉ ሲሆን፣ ይህ ዓይነት አካሄድ ወደተቀሩት ኩባንያዎች እየተዛመተ የመገናኛ ብዙኀኑን ከማስታወቂያ ገቢ ውጪ ሊያደርግ እንደሚችል ይሰጋል። ከዚህ በተጨማሪ በተለይም ነባሮቹ ሚዲያዎች አስተዋዋቂዎች ወደ ኢንተርኔት እያዘነበሉ ከሄዱ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እንደ ዘመኑ ሁኔታ የለውጥ ዕርምጃ በመውሰድ የተሻለ መንገድ ሊከተሉ ይገባል።

የአገራችን ሚዲያዎች – ትብብርና የየራሳቸው አዳዲስ የገበያ ዕቅዶች
የአገራችን ሚዲያዎች ዓለም ላይ ያለው ለውጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይመለከታቸዋል። አሁን ያለውን ችግር አስመልክቶ ሚዲያዎቻችን በመተጋገዝ የተራጀና የተባበረ ጉልበት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። በመንግሥት የሚወሰዱ ዕርምጃዎችንም የሚፈጥሩትን አደጋዎች አስቀድሞ በመመርመር ሊታገሉት ይገባል። ከማስታወቂያ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ችግርና ወደፊትም ቶሎ ለማይቀረፈው ችግር ግን አስተማማኝ የመፍትሄ ዕርምጃው በራስ ለመቆም የሚደረግ ጥረት ላይ ማተኮር ነው።

ይህም ማለት መገናኛ ብዙኀኑ አዳዲስ የገበያ ዕቅዶችን በመንደፍ መንቀሳቀስ ይሆናል። በዚህም ወደ መገናኛ ብዙኀኑ ያልገቡ የነበሩ ተቋማትን እንዲያስተዋውቁ ማሳመን ለምርታቸው የሚስማማ ማስታወቂያ በባለሙያዎች የታገዘ ናሙና ሠርቶ ማሳየት፣ በዓይነቱ ለየት ያለ ፕሮግራም በመንደፍ ይበልጥ ወደ ሕዝቡ ስሜት የቀረበ መሠናዶ በማዘጋጀት አስተዋዋቂዎችን መሳብ፣ የመገናኛ ብዙኀኑን ሥራቸው በማስፋፋት ተያያዥ የቢዝነስ ሥራዎችን መዘርጋትና ተቋሙ በገቢ ራሱን እንዲችል የሚያደርግ ስልት ነድፎ ለተግባራዊነታቸው መንቀሳቀስ እንዲሁም የበለጸጉ አገራት የሚጠቀሙትን የሚዲያ አመራር መርህ ተሞክሮውን በማየት የተከሰተውን ተግዳሮት ለመቋቋምና ለማሸነፍ ከፍ ያለ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው።
አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here